አቡነ ተክለ ሃይማኖት

<< የፃድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው >> ምሳሌ ፲፥፯

ኢትዮጵያ የብዙ ቅዱሳን ሀገር ነች።ከእነኝህ ቅዱሳን ውስጥ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንዱ ናቸው።አቡነ ተክለ ሃይማኖት በእግዚአብሔር ድንቅ ጥበብ፣ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ብሥራት፤ በኢትዮጵያ ምድር በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ልዩ ስሙ ኢቲሳ በሚባል ቦታ ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን እሑድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ፤ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤ አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው፤›› በማለት ሥላሴን አመስግነዋል፡፡

አቡነ ተክለሃይማኖት በሰባት ዓመታቸው ከግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ ዲቁናን ከተቀበሉ በኋላ እግዚአብሔር በክህነት ሕዝቡን እንዲያገለግሉ መረጣቸው፡፡ዮዲት ጉዲት መንግሥቱን ይዛ በክርስትናው ላይ ከዘመተች በኋላ ሰሜኑ እና ደቡቡ ተቆራርጧል፡፡ የሃሳብን ልዕልና የሚያመጣው የመንፈስ ልዕልና ተዳክሟል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያን የሚዋጅ ኢትዮጵያዊ የሃይማኖት አባት ያስፈልግ ነበር፡፡አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከአባታቸው ዕረፍት በኋላ ቅስናን ከአቡነ ቄርሎስ ተቀብለው በጽላልሽ አካባቢ በክህነት ከአባታቸው ጋር አገልግለዋል፡፡ አባታቸው ሲያርፉ በወንጌሉ ማንም ሊከተለኝ የሚወድድ ቢኖር ያለውን ሁሉ ትቶ መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ ያለውን ቃል በመከተል ሀብታቸውን ለድኾች መጽውተው ለወንጌል ስብከት ወጡ፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዳሞት እና በሸዋ ካገለገሉ በኋላ መጀመርያ ደቡብ ወሎ ቦረና ወደ ነበረው ወደ ደብረ ጎል ገዳም ገብተው አሥር ዓመት በትምህርት እና በሥራ አሳልፈዋል፡፡ በዚያም ዋሻ ፈልፍለው አስደናቂ ሕንፃ ሠርተው ነበር፡፡ገድለ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ እንደሚለው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ ሐይቅ የገቡት በሠላሳ ዓመታቸው ነው፡፡ ይህም የሚያሳየን በሸዋ እና በወላይታ ያገለገሉት ገና በወጣትነታቸው ጊዜ መሆኑን ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በሐይቅ ከመመንኮሳቸው በፊት ሰባት ዓመት፣ ከመነኮሱም በኋላ ሦስት ዓመት በትምህርት ፣ በሥራ እና በአገልግሎት ቆይተዋል፡፡ከሐይቅ ወጥተው በዘመኑ በሥርዓተ ምንኩስና እና በትምህርት ብሎም በጥበበ እድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ወደ ነበረው ወደ ደብረ ዳሞ ሄዱ፡፡ በዚያም ከአቡነ ዮሐኒ ዘንድ መንፈሳዊ ትምህርት፣ ሥርዓተ ምንኩስና እና ጥበበ እድ ሲማሩ ሰባት ዓመት አሳለፉ፡፡ ያነጹት ፍልፍል ድንጋይ ዋሻ፣ መጻሕፍት ሲጽፉ ቀለማቸውን ያስቀምጡባቸው የነበሩትን ሽንቁሮች ዛሬም በደብረ ዳሞ ማየት ይቻላል፡፡ቀሪዎቹን አምስት ዓመታት ሌሎችን የትግራይ ገዳማት እየተዘዋወሩ ሲመለከቱ ቆይተው ከሸዋ በወጡ በሃያ ሁለት ዓመት፣ እድሜያቸው ሃምሳ ሁለት ሲሆን ለበለጠው ክብር እና ርእይ በግብጽ በኩል ወደ ኢየሩሳሌም ተሻገሩ፡፡ ከኢየሩሳሌም ሲመለሱ በሐይቅ በኩል አድርገው ደብረ ጎልን ተሳልመው በሚዳ እና በመርሐ ቤቴ በኩል ወደ ሸዋ በመምጣት ከዮዲት ዘመን በኋላ በመንፈሳዊ ሕይወት የተጎዳውን ሸዋን እና ደቡብ ኢትዮጵያን በመዘዋወር ለአሥር ዓመታት ያህል አስተምረዋል፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተግተው በማስተማራቸው የተኛው ሁሉ ነቃ፣ የደከመው በረታ፣ የጠፋውም ተገኘ፡፡ በስብከታቸው እንደገና ለነቃው ለመካከለኛው እና ለደቡብ ኢትዮጵያ ሐዋርያትን ለማፍራት እንዲችሉ አንድ ገዳም ለመመሥረትና ደቀ መዛሙርትን ለማስተማር አሰቡ፡፡ እናም ወደ ደብረ አስቦ ገዳም ገቡ፡፡ ቦታውን አስተካክለው እና ከደብረ ዳሞ እና ከሐይቅ የተከተሏቸውን ጥቂት ደቀ መዛሙርት ይዘው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ልክ እንደ ሐይቅ እስጢፋኖስ አገልግሎት ጀመሩ፡፡

አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም አንጸዋል፡፡ ሐዲስ ሐዋርያየተባሉትም በዚህ ተልእኳቸው ሲሆን፣ ትርጕሙም ሐዲስ ኪዳንን ወይም ሕገ ወንጌልን እየተዘዋወረ የሚያስተምር ሰባኬ ወንጌል፤ በክርስቶስ ስም ድንቅ ድንቅ ተአምራትን የሚደርግ የክርስቶስ ተከታይ (ሐዋርያ) ማለት ነው፡፡

አባታችን ተክለ ሃይማኖት ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው፣ በብሕትውና ኖረዋል፡፡በተጨማሪም እንደቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፣ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሚታወሱባቸው በዓላት መካከልም ታኅሣሥ ፳፬ ቀን የሚከብረው በዓለ ልደታቸው አንደኛው ነው፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር ዜና ልደታቸውን ሲናገር ‹‹ሐዲስ ሐዋርያ›› በማለት በክብር ጠርቷቸዋል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፡፡ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል፡፡ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኃለሁ፤ ዋጋ አይጠፋበተም፤››(ማቴ. ፲፥፵-፵፪) በማለት የተናገረውን መለኮታዊ ቃል ኪዳን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መሠረት አድርጋ የአባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖትን በዓላት መጋቢት ፳፬ ቀን ፅንሰታቸውን፣ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ልደታቸውን፣ ጥር ፳፬ ቀን ስባረ ዐፅማቸውን፣ ግንቦት ፲፪ ቀን ፍልሰተ ዐፅማቸውን፣ ነሐሴ ፳፬ ቀን ደግሞ ዕለተ ዕረፍታቸውን በመንፈሳዊ ሥርዓት በደስታ ታከብራለች፡፡ “ የፃድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው” ምሳሌ ፲፥፯ እንዲል እኛም ነሐሴ ፳፬ የሚከበረውን የአባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዓለ እረፍት እናከብራለን።የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጸሎት፣ በረከት፣ ረድኤትና ምልጃ ከሁላችንም ጋር ለዘለዓለሙ ጸንቶ ይኑር፡፡አሜን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር