ደብረ ታቦር

ይኽ በዓል ከጌታችን 9 ዐበይት በዓላት አንደኛው ሲኾን በዓሉ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ላይ በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ ታሪኩ 3 ወንጌላት ላይ የተጻፈ ሲኾን ክብር ይግባውና ጌታችን አምላችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስምንቱን ሐዋርያትን ከእግረ ደብር (ከተራራው ሥር) ትቶ ሦስቱን (ጴጥሮን፣ ያዕቆብን፣ ዮሐንስን) ይዟቸው ወደ ታቦር ተራራ በመውጣት የሞተውን ሙሴን 1644 ዓመታት በኋላ አሥነስቶ የተሰወረውን ኤልያስንም ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ የሕያዋን አምላክና የሙታን አሥነሺያቸው ርሱ መኾኑን ብርሃኑ የገለጸበት ታላቅ ምስጢር የተከናወነበት ነው፡፡ (ማቴ 171-9)

ጌታ 8ቱን ሐዋርያት ይዟቸው ያልወጣበት በይሁዳ ምክንያት ነው ምክያቱም ከምሥጢረ መንግሥቱ ቢለየኝ ከሞቱ ገባኹበት ባለ ነበርና ነው፤ ነገር ግን በተራራው ላይ 3 የተገለጸው ምስጢር ከተራራው ሥር ላሉት ከይሁዳ በስተቀር ተገልጾላቸዋል፤ ለእኛም እንደ ሐዋርያት ምስጢሩን ጥበቡን ይግለጽልን፡፡

ብዙ ተራሮች ሳሉ የታቦር ተራራን የመረጠበት
1)
አስቀድሞ የጌትነት ክብሩ በዚያ ተራራ ላይ እንደሚገልጽ ነቢዩ ዳዊት በመዝ 8812 ላይታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚኣከ ይትፌሥሑ(ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ይደሰታሉ) በማለት ጌታ በዚያ ተራራ ላይ ብርሃኑን ሲገልጽ የብርሃኑ ነጸብራቅ እስከ አርሞንኤም ተራራ ድረስ እንደሚታይ የተናገረውን ትንቢት ለመፈጸም ነው፡፡

ሌላው ታቦር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ 12 ጊዜያት ሲጠቀስ በተለይ በመሳ 4 እና 5 ላይ እንደተጻፈው አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን የእስራኤል ጠላት የነበረው ሲሳራን መስፍኑ ባርቅ በተራራው ላይ ድል ነሥቶበት ነቢይቱ ዲቦራም በተራራው ላይ በደስታ አመስግናበታለች ዘምራበታለች፤ በተመሳሳይ መልኩ የእስራኤል ዘነፍስ የክርስቲያኖችን ጠላት የኾነውን ዲያብሎስን የኹላችን ፈጣሪ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነቱን ገልጦ ድል ስለነሣው ነቢያት ሐዋርያት ምእመናን የሚያመሰግኑት ስለኾነ ለምሳሌነቱ ተስማሚነት ያለውን የታቦርን ተራራን መርጦታል፡፡

ለምን ሙሴንና ኤልያስን ከነቢያት መኻከል መረጠ? ቢሉ
) በማቴ 1613 ላይ ሐዋርያትን ስለማንነቱ እንደጠያቃቸው እንደመለሱለት ኹሉ በእውነት የሙሴና የኤልያስ ፈጣሪ መኾኑን ሲገልጽላቸው ሲኾን ሙሴና ኤልያስም ጌታቸው ፈጣሪያቸው ርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ መኾኑን በተራራው ላይ መስክረዋል፡፡

) በዘፀ 3317-23 ላይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ካለው ጥልቅ ግንኙነት የተነሣእባክኽ ክብርኽን አሳየኝብሎ ልመናን አቀረበ፤ እግዚአብሔርምእኔ መልካምነቴን ኹሉ በፊትኽ አሳልፋለኊ፤ ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አልቻልኽምብሎታል፤ ይኸውም ፈጣሬ ዓለማት ጌታን በአምላካዊ ባሕርዩ፤ በመለኮታዊ ክብሩ ማንም ሊያየው አለመቻሉን ሲገልጽለት ነው፤ ይኽነን ካለው በኋላ ይገለጽ ዘንድ ስላለው ምስጢር ሲገልጽለት ‹‹ናሁ መካን ኀቤየ ሀሎ›› (እንሆ ስፍራ በኔ ዘንድ አለ) ‹‹ወትቀውም ውስተ ኰኲሕ›› (በዐለቱም ላይ ትቆማለኽ) ‹‹ወአነብረከ ውስተ ስቊረተ ኰኲሕ ወእከድን እዴየ በላዕሌከ እስከ አኃልፍ›› (በሰንጣቃው ዐለት አኖርሃለኍ፤ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይኽ እጋርዳለኍ፤ ካለፍኍ በኋላ እጄን አንሥቼልኽ ዠርባዬን ታያለኽ፤ ፊቴ ግን አይታይም) ብሎታል (ዘፀ ፴፫፥፲፯፳፫)፡፡

ይኸውም ዠርባ በስተኋላ እንደሚገኝ ኹሉ በኋላ ዘመን አካላዊ ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በታቦር ተራራ ላይ እንደሚገለጽለት ሲያመለክተው ነው፤ ይኸውም ጌታ ለሙሴ ‹‹እንሆ ስፍራ በኔ ዘንድ አለ›› ማለቱ የሞት፣ የመቃብር ሥልጣን በኔ ፈቃድ ነውና ሲለው ነው፤ ‹‹በዐለቱም ላይ ትቆማለኽ›› ማለቱ ፭ሺሕ ፭፻ ዘመን ሲፈጸም ሰው ኾኜ ሥጋ ተውሕጄ በደብረ ታቦር እስክገልጽልኽ ድረስ አንተ በመቃብር ትኖራለኽ ማለቱ ሲኾን ‹‹እስካልፍ ድረስ እጄን በላይኽ እጋርዳለኍ›› ያለው በታቦር ተራራ የባሕርይ ልጅነቴን እስክገልጽ ድረስ ሥልጣኔን በአንተ ላይ አጸናለኍ ማለቱን ሲያመለክት ‹‹እጄንም ፈቀቅ አደርጋለኍ›› ማለቱ ሰው ኾኜ ሥጋን ተውሕጄ በዚኽ ዓለም በተገለጽኍ ጊዜ የሞትን ሥልጣን ከአንተ አርቃለኍ ሲለው ነው፤ ‹‹ዠርባዬንም ታያለኽ›› ማለቱ ያን ጊዜ በደብረ ታቦር በክበበ ትስብእት ታየኛለኽ ሲለው ነበር፤ ይኽም ያለው አልቀረም አካላዊ ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በዚኽ ዓለም ከተገለጸ በኋላ የሰጠውን ቃል ሊፈጽምለት ከሦስቱ ባለሟሎች (ከጴጥሮስ፣ ከያዕቆብ፣ ከዮሐንስ) ጋር በመኾን በደብረ ታቦር ላይ ተገልጾለታል (ማቴ ፲፯፥፩)

ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብም ስለ ታቦር በሚተነትነው መጽሐፉ ሙሴ በቃዴስ ባለው በመሪባ ውሃ ከእስራኤል ጋር በበደለው በደል ምክንያት ምድረ ርስት ኢየሩሳሌም እንዳይገባ አይቷት ብቻ በናባው ተራራ ላይ እንዲያርፍ ኾኗል (ዘፀ ፴፪፥፶፪፤ ዘፀ ፴፬፥፩)፡፡ ይኽ ለሙሴ አሳዛኝ ቢኾንም በኋላ ዘመን አካላዊ ቃል ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ሙሴ በፊት በሩቁ ያያት ግን ያልገባባት በምድረ ርስት በኢየሩሳሌም ያለች ታቦር ተራራ ላይ አምጥቶት በዘመነ ብሉይ በአካለ ሥጋ ያልገባባትን ርስት እንዲገባባት አድርጎታል፤ ይኸውም አዳምና ልጆቹ በአካለ ሥጋ ያጡትን ርስታቸው ገነትን በአካለ ነፍሳቸው ዳግመኛ ሊያገባቸው እንደመጣ የሚያመለክት መኾኑን በስፋት አስተምሯል፡፡

ጌታችን በብሉይ ኪዳን ከነበሩት ከነቢያት ሙሴንና ኤልያስን በሐዲስ ኪዳን ከነበሩት ከሐዋርያት ሦስቱን በታቦር ተራራ ላይ ማውጣቱ
1)
የታቦር ተራራ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ በመኾኗ ሲኾን በቤተ ክርስቲያናችን ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን እንደሚነገሩ ለማመልከት
2)
ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት በማመን የነቢያትንና የሐዋርያትን ክብርና ምልጃ እንደምታስተምር ለማሳየት ነው፡፡

ሌላው የታቦር ተራራ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ስትኾን ይኸውም ጌታ ነቢያትንና ሐዋርያትን በተራራዋ ላይ መሰብሰቡ

1)መንግሥተ ሰማያትን ነቢያትም ሐዋርያትም እንደሚወርሷን ለማመልከት

2) ሙሴ ያገባ ሲኾን ኤልያስ ድንግል ነውና መንግሥተ ሰማያትን ደናግልም ያገቡም እንደሚወርሷት ለማጠየቅ ነው፡፡

3) ሙሴ ኦሪት ዘፍጥረትን ሲጽፍበመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ(ዘፍ 11) እንዳለ፤ ዮሐንስምበመጀመሪያ ቃል ነበር(ዮሐ 11) ብሎ እንደ ሙሴ አምላክነቱን የሚመሰክር ነውና ሙሴ አስቀድሞ የጻፈልኝ፤ አኹንም ዮሐንስ አምላክነቴን የሚጽፍልኝ እኔ ነኝ ሲል ነው፡፡ ዳግመኛም ሰማይኑን ዝናብ እንዳያዘንም በተሰጠው ሥልጣን ባሰረውና 3ዓመት 6ወር ቆይታ በኋላ እንዲዘንብ በፈታው ኤልያስን እንዳመጣ ኹሉ የማሰር የመፍታት ሥልጣን ሥልጣነ ተሰጥቶትእኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል(ማቴ 1618-19) ላለው ለጴጥሮስን ታላቅ ሰማያዊ ሥልጣን መስጠቱን ለማመልከት አምጥቷቸዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያንና በሀገራችን ያለው መንፈሳዊ አከባበር ደማቅ ነው፤ ይኽ በዓል በቤተ ክርስቲያን በማሕሌት በቅዳሴ በትምህርት የሚከበር በዓል ሲኾን በሀገርኛ የቡሄ በዓል ይባላል፡፡ ቡሔ ማለት ሊቁ ደስታ ተክለ ወልድ በመዝገበ ቃላት ላይ ሲገልጹት ብሎ በደብረ ታቦር የተገለጠው የጌታችንን የፊቱን ብርሃን ጸዳል የልብሱን እንደ በረዶ ነጭ መኾን ያስረዳል ስለዚኽ የብርሃን፣ ብርሃናዊ ማለት ነው፡፡ ሌላውብሑዕማለት የቦካ ማለትን ሲያመላክት በዚኽ ቀን የሚጋገረውን ሙሉሙል ዳቦ የሚያመለከክት ነው፡፡
በዚህ በዓል የብርሃኑ ምሳሌ የሚሆን ችቦ ነሐሴ 12 ማታ ይበራል፤ ሌላው በዚኽ በዓል ሰሞን በገጠር ከተራራ ላይ እረኞች ሕጻናት ዥራፍ እየገመዱ ማስጮኻቸው ጌታ በተራራ ላይ ብርሃኑን በገለጸ ጊዜ አብ በደመና ኾኖእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙትባለ ጊዜ ሐዋርያት በድምፁ ደንግጸው መውደቃቸውን ለማመለክት ነው፡፡

ሌላው ሙሉሙሉ ዳቦ መጋገሩ በትውፊት እንደምንረዳው ጌታ ብርሃኑን ሲገልጽ ብርሃኑ እስከ አርሞንኤም ተራራ ድረስ ያበራ ስለነበር እረኞች ሌሊቱ ኹሉ ቀን መስሏቸው እዛው ስለዋሉ ቤተሰቦቻቸውኅብስትይዘውላቸው ሄደዋልና የዚያ ምሳሌ ነው፡፡

ሌላው የበዓሉ ጭፈራ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ሲኾን ብዙ ምስጢርም በውስጡ ይዟል ይኸውም

….“ሆያ ሆዬ
….“
እዛ ማዶ ጭስ ይጨሳል ……
…..
አጋፋሪ ይደግሳል ……..
…..
ያችን ድግስ ውጬ ውጬ …….
…..
ከድንክ አልጋ ተገልብጬ ……..
…..
ያቺ ድንክ አልጋ አመለኛ …….
…..
አላንድ ሰው አታስተኛ” …….
ተብሎ ይጨፈራል፡፡ ይኸውም የእስራኤልን ታሪክ ያዘለ ሲኾንሆያ ሆዬ ማለት ጌታው ሆዬ እሜቴ ሆዬ ብሎ አክብሮትን መግለጽ ነው፡፡

እዛ ማዶ ጭስ ይጨሳል …… አጋፋሪ ይደግሳል …….. ማለት እስራኤል ከግብጽ ባርነት በወጡ ጊዜ በጭስ የተመሰለ ጉምና ደመና እየመራቸው ቅዱስ ሚካኤል መና እያወረደላቸው ስለወጡ ጭስ የተባለው የደመናው ምሳሌ፤ አጋፋሪ የተባለው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡

ያችን ድግስ ውጬ ውጬ ……. ከድንክ አልጋ ተገልብጬ …….. ማለት በድግስ የተመሰለውን መና እስራኤል 40 ዘመን በአጋፋሪ በተመሰለው በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት እየተመገቡ በድንክ አልጋ የተመሰለችውን ኢየሩሳሌምን መውረሳቸውን የሚያመለክት ነው፡፡

ያቺ ድንክ አልጋ አመለኛ ……. አላንድ ሰው አታስተኛ” …….መባሉ እስራኤል ከግብጽ ሲወጡ 600,000 ሆነው ሲሆን ነገር ግን ሁሉም በምድረ በዳ አልቀው ኢየሩሳሌምን የወረሳት አንድ ኢያሱና አንድ ካሌብ ነው ለማለት ነው፡፡


በደብረ ታቦር ላይ ብርሃኑን የገለጠው አምላካችን ክርስቶስ ምስጋና ይግባው፡፡
መልካም በዓል
መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ