መፃጉዕ (የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት)

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የማዳኑ ጉዳይ ጎልቶ ከሚነገርባቸው ጊዜያት አንዱ ይህ “መጻጉ’’ የተሰኘው ሳምንት ነው፡፡ “መጻጉ” ማለት በሽተኛ ማለት ነው፡፡ አምላካችን በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በዚህች ምድር ሲመላለስ ከደዌ ዳኛ ከአልጋ ቁራኛ የገላገላቸው መኾኑን የሚያሰረዱ የምስክርነት ቃሎች የሚሰሙበትን ጊዜ ቅዱስ ያሬድ “መጻጉ” በማለት ጠርቶታል፡፡

«ተንስዕ ንሳዕ ዐራተከ ወሑር፤ ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ» /ዮሐ.5፡8/ «ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ» ያለው ሠላሳ ስምንት ዓመት በአልጋ ላይ ሰውነቱ ልምሾ ሆኖ ታሞ የነበረውን ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው የህመሙ ዘመን ስለረዘመ ዘመዶቹ ሁሉ እየሰለቹ የማስታመሙን ነገር ችላ ብለው ጥለውት ሄደዋል፡፡ ህመምተኛው ዘመዶቹ በተውት ቦታ በቤተሳይዳ መጠመቂያ ፀበል አጠገብ ተኝቶ ነበር፡፡

በመጻጉ ሳምንት የሚሰበከው ምስባክ፡- ‹‹እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፤ ወይመይጥ ሎቱ ኵሎ ምስካቤሁ እም ደዌሁ፤ አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ›› የሚለው ነው ፡፡ በመዝሙር 40 ላይ የሚገኘውን ይህንን ቃል ዲያቆኑ ከፍ ባለ ዜማ ከሰበከ በኋላ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 5 ላይ ያለው ይነበባል፤ ይተረጎማል ፡፡ በደዌ ሥጋም ኾነ በደዌ ነፍስ የተያዝን የሰው ልጆች የፈጣሪያችንን ምሕረትና ቸርነቱን እንደምናገኝ ተሰፋ የምናደርግባቸው ገቢረ ተአምራት ይሰማሉ፡፡

ጌታችን መጻጉን በፀበሉ ዳር ባገኘው ጊዜ እርሱ የሁሉም መድኃኒት በመሆኑ ወዲያው «ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ» ሲለው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፡፡ አይሁድ ማን አልጋውን ተሸክሞ እንዲሄድ እንደፈቀደለት ቢጠይቁት ለጊዜው ጌታችንን ባያውቀውም፤ በሌላ ጊዜ ጌታችን ሲያገኘው «እነሆ! ድነሃል ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ዕወቅ» የተባለውን ዘንግቶ ለአይሁድ ሊጠቁመው ሮጦ ሄደ፡፡ እንዳሰበውም ነገራቸው እነሱም ሊያሳድዱት ሊገሉትም ይሹ ነበር፡፡ ከዚህ የፈውስ ታሪክ ሁለት ቁም ነገሮችን እንማራለን ። እነርሱም

  1. እግዚአብሔር ሕሙማንን በምሕረቱ ይጐበኛቸዋል፤ ከደዌአቸውም ፈውሶ ጤንነታቸውን ሊመልስላቸው ይችላል፡፡ ከታሪኩ እንደተመለከትነው ሠላሳ ስምንት ዓመት የተኛውን ከደዌው፣ ከእናቱ ማህፀን ያለዓይን የተወለደውን ከዓይነ ስውርነት፣ አስራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበረችውን ከሕመሟ፣ ከሞተ አራት ቀን የሆነውን አልአዛርን ከሞት፣ የመቶ አለቃውን ልጅ ባለበት ሆኖ ከሞት ወዘተ አድኗቸዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው እምነታችን ካለንና እግዚአብሔር ከፈለገ ማዳን እንደሚቻለው ነው፡፡
  2. የዳነ ሰውም ያዳነው አምላኩን በማወቅ፤ ውለታውን በሃይማኖት ጸንቶ በደግ ሥራ መመለስ ይገባዋል፡፡ በመጻጉ ታሪክ ላይ ግን የምናገኘው እንዲህ አይደለም፡፡ ከተጣበቀበት የአልጋ ቁራኛነት እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ቢያድነው፤ ለአይሁድ አለቆች ባዳነው ሰውነቱና እግሮቹ ሮጦ ሄዶ ሰብቅ ሠራ፡፡ ምስክር ይሆንበት ዘንድ «እነሆ ድነሃል ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ» በማለት እየተናገረው ሳለ «በሰንበት ያዳነኝ ኢየሱስ ነው» በማለት ያዳነውን በመክሰስ አሳልፎ ሰጠው፡፡ የሰውየውን ማንነት ስንመለከት ልቡ ያልዳነ፤ ያዳነውን ሊረዳ ያልቻለ፣ ክፉና ደጉን ማገናዘብ የተሳነው ሰው ነው፡፡ ዛሬስ ለተደረገልን መልካም ነገር ተገቢውን መልካም ምላሽ በበጐነት የመለሰን ስንቶቻችን ነን?

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስረዳን አምላክ ላደረገላቸው ፈውስ ዘመናቸውን በበጐ ምግባር የፈፀሙ አያሌ ቅዱሳን አሉ፡፡ ለምሳሌ ክፉ መናፍስት አደረውባት የነበረችና በኋላ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምህረት እጁ የጎበኛትን መግደላዊት ማርያምን መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡ ይህች ሴት ሰባት አጋንንት የወጣላት ሴት ስትሆን ጌታችን በሚያስተምርበት እየዞረች ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን በጉልበቷና በገንዘቧ ለጌታችንና ለሐዋርያት የሚያስፈልጋቸውን በማቅረብ ታገለግል ነበር፡፡ /ሉቃ. 8÷2-3/ ፡፡ በትንሣኤው ቀን ማለዳ ከሁሉ ቀድማ ተገኝታለች፤እያለቀሰችም ጌታችንን ትሻው ነበር፡፡ ለዚህም ልዩ ትጋቷ ጌታችን ከሌሎቹ ይልቅ ትንሣኤውን ለማየት የመጀመሪያዋ አድርጓታል፡፡ የምስራቹን ለሐዋርያት በማድረስ በኩል የክብር መልእክተኛ ሆናለች ከዚህ የበለጠ ምን መታደል አለ፡፡ /ዮሐ. 10.1-18/

ከነቢያት አንዱ ነቢዩ ኢሳይያስን ብንመለከት ሐብተ ትንቢቱ ተነስቶት ከንፈሮቹ በለምፅ ነደው እያዘነ ይኖር ነበር፡፡ ኦዝያን በሞተበት ወራት እግዚአብሔር በታላቅ ዙፋን ተቀምጦ ታይቶት፤ ምስጋና ከሚያቀርቡት መላእክት አንዱ ሱራፌል እየበረረ መጥቶ በጉጠት ፍም አፉን ዳሶት «በደልህ ከአንተ ተወገደ፣ ኃጢአትህም ተሰረየልህ» ብሎት ከለምጹ አንጽቶት ኃጢአቱ እንደተሰረየለት ነግሮት ሄዷል፡፡ ነቢዩ ስለተደረገለት ፈውስ የጌታ ድምፅ ማንን እልካለሁ? ሲል እነሆ እኔ አለሁ ብሎ ትንቢት በመናገር፣ ሕዝቡን በማስተማር በመጋዝ እስከ መሠንጠቅ ድረስ እራሱን ለእግዚአብሔር ሰጥቷል፡፡ ከላይ ያየናቸውን ሠላሳ ስምንት ዓመት በአልጋ ላይ የተኛውን መፃጉንና መግደላዊት ማርያምን እንዲሁም ነቢዩ ኢሳይያስን ስናወዳድር በተገቢው ምላሽ ያልሰጠው መፃጉዕ ነው፡፡/ት.ኢሳ.6÷1-8/፡፡

እኛም በየደቂቃው በኃጢአት ሳለን እንኳ ጥበቃው የማይለየን እግዚአብሔር ያደረገልንን በማሰብ አሁን በዚህ ሰዓት ምን እየሰራን ይሆን ? ወደፊትስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ምን ለመሥራት አስበናል? ለባሮቹ ፈውስን ሰጥቶ በጐ ምላሽን በማከናወን ያፀናቸው አምላክ እኛንም ይረዳን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

 

ምንጭ   ተዋህዶ ብሎግ

ማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባኤያት ትምህርት