ምኩራብ ( የዐቢይ ጾም ሶስተኛ ሳምንት )

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን የበዓላት ቀኖና መሰረት የዐቢይ ፆም ሦስተኛ ሳምንት “ምኩራብ” ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ ሳምንት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ መሄዱን፣ በቤተመቅደሱ የማይገባ ንግድ ያደርጉ የነበሩትን “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ” ብሎ መገሰፁን፣ የሚሸጡ የሚለውጡትንም መገለባበጡን፣ ደቀ መዛሙርቱም ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት አስቀድሞ በትንቢት “የቤትህ ቅናት በላኝ” በማለት የተናገረው እንደተፈጸመ ማስተዋላቸው የሚታሰብበትና የሚተነተንበት ነው (ዮሐ. 2፡13-17)፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍት መልእክት እስከ ዓለም ፍፃሜ ለሚመጡ ምዕመናን በሙሉ ትርጉም ያላቸው ናቸውና ቅድስት ቤተክርስቲያን ከየዘመኑ ሁኔታ አንፃር ከቃለ እግዚአብሔር እንዳንርቅ ታሪኩን መነሻ በማድረግ ታስተምራለች፡፡ በዚህች አጭር ጽሁፍም የሳምንቱ (የዕለቱ) የወንጌል ንባብ ተብራርቷል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱና በቃና ዘገሊላ ተዓምራቱ አምላክነቱን ገልጦ ህዝቡን ማስተማር ከመጀመሩ በፊት በነበሩት ሠላሳ ዓመታት በተደጋጋሚ ወደ ቤተመቅደስ መጥቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉት በሥርዓተ ኦሪት መሰረት በተወለደ በአርባኛው ቀን ወደ ቤተመቅደስ መምጣቱ (ሉቃስ 2፡22-40)፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ ከዮሴፍና ከእመቤታችን ጋር ለበዓል ወደ ኢየሩሳሌም በሄዱ ጊዜ ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ቤተመቅደስ በመሄድ የኦሪት ሊቃውንትን ሲጠይቃቸውና ሲሰማቸው የነበረ መሆኑ (ሉቃ 2፡41-47) ናቸው፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ወደ ቤተ መቅደስ ሲመጣ አገልጋዮቹ በሥጋዊ ፍላጎታቸው ምክንያት በቤተመቅደሱ የማይገባ ሥራ እየሰሩ ቢያይም አምላክነቱን ገልጦ የሚያስተምርበት፣ የሚገስጽበት ጊዜ አልደረሰምና በዝምታ አልፏቸው ነበር፡፡

ጊዜው በደረሰ ጊዜ ሊቃናተ አይሁድ ባለመታዘዝ ያረከሱትን መቅደሱን ያነጻ ዘንድ መጣ፡፡ መስዋእተ ኦሪት ይሰዋበት የነበረውን ቤተመቅደስ ያነፃው ጌታ ራሱን የሐዲስ ኪዳን መስዋእት አድርጎ አቅርቧልና ኃላፊ ጠፊ የሆኑትን የብሉይ ኪዳን የመስዋእት እንስሳት ከቤተ መቅደስ አስወጣ፡፡ አባታችን አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ አማናዊ የሐዲስ ኪዳን መስዋእት የሆነ የጌታችንን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ከብሉይ ኪዳን መስዋእት ጋር በማነፃፀር “በበግ በጊደርና በላም ደም እነደነበረው እንደ ቀደሙት አባቶች መስዋእት አይደለም፤ እሳት ነው እንጂ፡፡ ፈቃዱን ለሚሰሩ ልቦናቸውን ላቀኑ ሰዎች የሚያድን እሳት ነው፡፡ ስሙን ለሚክዱ ለዐመፀኞች ሰዎች የሚበላ እሳት ነው፡፡” እንዳለ የብሉይ ኪዳንን መስዋእት አሳልፎ ራሱን ለዓለም ቤዛ አድርጎ የሰጠ ጌታ የአይሁድ አለቆች በገንዘብ ወዳድነት መስዋእቱን ወዳቃለሉበት ቤተ መቅደስ በመምጣት ቤተ መቅደስን አነፃ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ለሁለት ጊዜያት ቤተመቅደሱን አንጽቷል፡፡ ከእነዚህ ቀዳሚው በመጀመሪያው ፋሲካ ከጥምቀቱ በኋላ አገልግሎቱን ሲጀምር ያደረገውና በምኩራብ ሣምንት የሚነበበው፣ የሚተረጎመው ነው፡፡ ጌታችን ለሁለተኛ ጊዜ ቤተመቅደሱን ሊያነፃ የሄደው ለመከራና ለሞት ተላልፎ ከመሰጠቱ አስቀድሞ በዕለተ ሆሳዕና፣ ማለትም በአራተኛውና የመጨረሻው ፋሲካ ነው (ማቴ 21፡12-17)፡፡  በዚህም ወቅት በተመሳሳይ ገዥዎችንና ለዋጮችን፣ እንዲሁም የቤተመቅደስ አለቆችን “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፣ እናንተ ግን የሌቦችና የወንበዴዎች፣ ቀማኞች ዋሻ አደረጋችኋት” በማለት ገሰፃቸው፡፡ ስለሆነም ትንቢተ ነቢያትን የፈጸመ ጌታ በአገልግሎቱ መጀመሪያና ፍፃሜ ላይ ወደ ቤተመቅደስ የመጣው ቤተመቅደሱን ለማንፃት ነበር፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተመቅደስ የሄደው “የአይሁድ የፋሲካቸው በዓል” በደረሰ ጊዜ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡  እግዚአብሔር ባያዝንባቸውና ይህ የፋሲካ በዓል በትክክል ቢከበር ኖሮ  “የእግዚአብሔር ፋሲካ” (ዘፀ 12፡11) ይባል ነበር፡፡  እግዚአብሔር ለሙሴ የበዓላትን ሥርዓት ሲነግረው በዓላቱን “በዓላቴ፣ የእግዚአብሔር በዓላት” በማለት ጠርቷቸዋል (ዘሌ 23፡2)፡፡ ይሁንና እነዚህን ቅዱሳት ጉባኤያትና በዓላት ሥርዓቱን የሚያቃልሉ፣ በሃይማኖታዊ ህግጋት የማይመሩ “አገልጋዮች” በሚያበላሿቸው ጊዜያት ጌታ በህዝቡና በአገልጋዮቹ አዝኖ “የእኔ” ያላቸውን በዓላትና ጉባኤያት “የእናንተ” ብሎ ይገልፃቸዋል፤ ከፈቃዱ ወጥተዋልና፡፡  “መባቻዎቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች…(ኢሳ 1፡14)” እንዲል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ጌታችን በመጀመሪያው ፋሲካ  ቤተመቅደስን ለማንፃት በሄደ ጊዜ የህዝቡና የአገልጋዮቹ ኃጢአት አሳዛኝ ስለነበር ቅዱስ ዮሐንስ በዓሉን “የአይሁድ” በዓል መሆኑን ጠቀሰ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተመቅደስ ሲመጣ በቤተመቅደሱ የሚሸጡ የሚለውጡ ሰዎችንና የሚሸጡ የሚለወጡ እንስሳትን አገኘ፡፡ የሚሸጡት እንስሳት እንደ ብሉይ ኪዳን ሥርዓት ለኃጢአት ማስተስረያ መስዋእትነት የሚቀርቡ ነበሩ፡፡ የካህናት አለቆችና ግብር አበሮቻቸውም በቤተመቅደሱ የሚሸጡትን እንስሳት ለመስዋእት ብቁ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ በመስጠት በምትኩ ገንዘብ እየተቀበሉ አገልግሎቱ መልኩን ቀይሮ ንግድ ሆኖ ነበር፡፡ ለመስዋእት የሚሆኑትን እንስሳት የሚሸጡት ሰዎችም ስለሚያገኙት ትርፍ እንጅ ስለ መስዋእቱ ንጽህና አልነበረም፤ ከጌታ የሚገኝ ሰማያዊ ጸጋን በመሸጥና በመለወጥ በሚያገኙት ትርፍ የቀየሩ ነበሩ፡፡ ሊቁ ቅዱስ አምብሮስ በትርጓሜው እንደገለጠው በሬዎችን ይሸጡ የነበሩት ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ለሥጋዊ ክብርና ጥቅም ሲሉ “የሚያስተምሩ” ምንደኛ አገልጋዮችን ይመስላሉ፡፡ በጎችን ይሸጡ የነበሩት ሰዎች መልካም ነገርን ለውዳሴ ከንቱ ሲሉ የሚያደርጉ ጌታችን “ዋጋቸውን በምድር ተቀብለዋል” ያላቸውን ከንቱ ውዳሴ ፈላጊዎች ይመስላሉ፡፡ ርግቦችን የሚሸጡትም የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በገንዘብ መሸጥና መግዛት የሚፈልጉትን ሲሞናውያን ይመስላሉ፡፡ የእኛስ አገልግሎት ምን ይመስል ይሆን?

ጌታችን ቤተመቅደስን ሲያነፃ እንደ ምልክት ከተፈጸሙት ተግባራት መካከል  በቤተመቅደስ ግቢ ይሸጡ (ሸ ጠብቆ ይነበብ) የነበሩትን በጎችንና በሬዎችን ከቤተመቅደስ ማስወጣቱ፣ የገንዘብ ለዋጮችን ገንዘብ መበተኑ፣ ገበታቸውንም መገልበጡ፣ ርግብ ሻጮችንም ርግቦቻቸውን እንዲያወጡ ማዘዙ ይጠቀሳሉ፡፡ ሲያስወጣቸውም የገመድ ጅራፍ አበጅቶ (ሰርቶ) ከቤተመቅደስ አስወጣቸው፡፡ አባቶቻችን በትርጓሜ ሲያብራሩ ጅራፉን የሰሩት ሐዋርያት እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡ የጭፍራውን ሥራ ለአለቃው ሰጥቶ መናገር ልማድ ነውና ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ጌታ ጅራፍ መስራቱን ገለጠ፡፡ ሊቃውንት እንደሚያስተምሩት ጌታችን ወደ ቤተመቅደስ የመጣው ለፍርድ ሳይሆን ለማንፃት ነበርና ሻጮችና ለዋጮችን ሰዎች ሳይሆን የሚሸጡትንና የሚለወጡትን ርግቦችን፣ በጎችን፣ በሬዎችን፣ የሰዎቹን የሚለወጥ ገንዘብ ከቤተ መቅደስ አስወጣ፡፡ ይህን ያደርጉ የነበሩትን ሰዎች ግን በመገሰጽ አለፋቸው እንጅ ፈርዶ አላባረራቸውም፤ የመጣው ለፍርድ አልነበረምና፡፡ በዳግም ምጽዓት ሲገለጥ ግን ለፍርድ ይመጣል፤ በቤተመቅደስ ያልተገባ ስራ የሰሩትንና የሚሰሩትንም ይቀጣል፡፡

ከላይ በተገለጸው መልኩ ቤተመቅደሱ የንግድ ቦታ ሆኖ ነበር፡፡ ሊቃነ ካህናቱም የጥቅም ተካፋይ ስለነበሩ የሚመክርና የሚገስጽ አልነበረም፡፡ ስለሆነም ጌታችን የሚሸጡና የሚለወጡትን ካስወጣ በኋላ  “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ አላቸው“፡፡ በዚህም አምላክ፣ ወልደ አምላክነቱን ገለጠ፡፡ “የአባታችሁን” ወይም “የአባታችንን” ሳይሆን “የአባቴን” ቤት በማለቱ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሌሎች ሰዎች በጸጋ ሳይሆን በባህርይ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን፣ እግዚአብሔርነቱን፣ አምላክነቱን ገለጠ፡፡ ጌታችን ቤተ መቅደስን እንዳነፃ ባዩ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “የቤትህ ቅናት በልቶኛልና፣ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና” (መዝ. 68፡9) በማለት የተናገረው ትንቢት መፈጸሙን አስተዋሉ፡፡

ሊቃናተ አይሁድ በቤተመቅደሱ ሲሸጡና ሲለውጡ፣ ሥጋዊ የገንዘብ ትርፍና ዝና በማሳደድ የቤተመቅደሱን ክብር ሲያቃልሉ ያደረጉትን ሁሉ ለመንፈሳዊ ዓላማ ያደረጉት ለማስመሰል በቤተመቅደስ ለሚሸጡትና ለሚለወጡት የመስዋእት እንስሳትና ገንዘብ የትክክለኛነት ማረጋገጫ ይሰጡ ነበር፡፡ ዛሬም ተረፈ አይሁድ የሆኑ ምንደኛ አገልጋዮች አሉ፡፡ ንፁሁን መስዋዕት መዝሙሩን፣ ንዋየ ቅድሳቱን፣ በዓለ ንግሱን፣ ጸበሉንና ሌሎችንም መንፈሳውያን እሴቶቻችንን ለገንዘብ ማግኛነት ሲጠቀሙባቸው ዓላማቸውን መንፈሳዊ ለማስመሰል ይሞክራሉ፤ የዋሀንንም ያሳስታሉ፡፡በቤተመቅደሱ ንግድ ሲደረግ፣ አገልጋዮች በቤተመቅደስ የሚቀርበውን መስዋዕት ለሥጋዊ ጥቅም ሲያውሉት፣ በዚያም ምክንያት የከበሩ መንፈሳውያን አገልግሎቶች ሲቃለሉ አርዓያ የሆነን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዝምታ አላለፈውም፡፡

ጌታችን “ከእኔ ተማሩ” ብሎናልና በዘመናችን ባሉ ምንደኛ አገልጋዮች መዝሙርን፣ በዓለ ንግስን፣ በጸበል ማጥመቅን፣ ትምህርተ ወንጌልን ለገንዘብ ማግኛነትና ለንግድ ሲያውሏቸው፣ በበዓላት ላይ ከመንፈሳዊ ሥርዓት ይልቅ ሥጋዊ ንግድና ደስታ ሲበዛ፣ የቤተክርስቲያን የከበሩ ንዋየ ቅድሳት በገዛ አገልጋዮቻችን እንደ ሸቀጥ ሲታዩ፣ ጸሎት ለማድረስ ገንዘብ የሚተምኑ ምናምንቴ ሰዎች ሲመጡ በቃለ እግዚአብሔርና በሥርዓተ ቤተክርስቲያን ጋሻነት ልንቃወማቸው ይገባል፡፡ እኛ ዝም ብንልም የቤተ መቅደሱ ባለቤት ዳግም ይመጣል፡፡ የሚመጣው ግን እንደቀደመው ለማንፃት ሳይሆን ለፍርድ ነው፡፡ ስለሆነም ከሚፈረድላቸው እንጅ ከሚፈረድባቸው ወገን እንዳንሆን አገልግሎታችን ለጽድቅና ለበረከት እንጅ ለገንዘብ፣ ለዝና፣ ለታይታ፣ ለከንቱ ውዳሴ አይሁን፡፡ እያንዳንዳችንም የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን እንደ አይሁድ ሊቃናት ለገንዘብና ለዝና ማግኛነት የሚጠቀሙትን ምንደኛ “አገልጋዮች” ለይተን ልናውቅ፣ አውቀንም ልንርቃቸው ይገባል፡፡

ስብሃት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፡፡ አሜን፡

ምንጭ አትሮንስ ተዋህዶ