ደብረ ዘይት (የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

በዓለ ደብረ ዘይት

  1. የደብረ ዘይት ትርጉም

ከትርጉሙ ለመነሣት ደበረ ዘይት ማለት ትርጉሙ የወራ መብቀያ፣ በወይራ ደን የተሸፈነ ተራራ ማለት ነው። ወይም «ደብር» ማለት «ተራራ» ማለት ሲሆን «ዘይት» ማለት ደግሞ «ወይራ»  ማለት ነው። በተገናኝ «ደብረ ዘይት» ማለት የወይራ ዛፍ የሞላበት፣ የበዛበት፣ በይወራ ዛፍ ደን የተሸፈነ ተራራ ማለት ይሆናል።

መልክአ ምድር

አቅጣጫው ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ  የሚገኝ ተራራ ሲሆን በመካከል የቄድሮን ሸለቆ ብቻ ነው ያለው። ከግርጌው ጌቴ ሴማኒ የተባለው የአትክልት ስፍራ ይገኛል። የጸሎተ ሐሙስ ማታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተያዘበትና በኋላም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ሥጋዋ ያረፈበት ወይም የድንግል ማርያም መካነ መቃብር በዚህ ተራራ ግርጌ ይገኛል።  ቤተ ፋጌ እና ቢታንያ በኮረብታው ጫፍ እና በምስራቅ ዳገት ላይ ይገኛሉ። ይህ ተራራ በመፅሐፍ ቅዱስ የሚገኙ ብዙ ድርጊቶች የተደረጉበት ቦታ ነው። ጌታችን ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ፣ ስለ ዓለም ፍጻሜ፣ ስለ ዳግም ምጽአት፣ ስለ ትንሣኤ ዘጉባዔና ሰለ ፍርድ ቀን በዚህ ተራራ ላይ በትንቢት መልክ ተናገረ። (ማቴ.24፥3)። በዚሁ ተራራ ላይ ወደ ሰማይ ዐረገ። (ሉቃ. 24፥50)። በዚሁ ተራራ ላይ ቀን በከታማና በገጠር ሲያስተምር ውሎ ሌሊት የሚያድርበት የኤሌዎን ዋሻ ይገኛል። በኋለኛው ምጽአቱም በዚሁ ቦታ እንደሚገለጥ ትንቢት ተነግሯል። (ዘካ. 14፥3–5)።

ስያሜው

የዓቢይ ጾም እኩሌታ ላይ ያለው ሰንበት በዚህ ተራራ ስም ተጠርቷል። ይህንን ዕለት የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ የዳግም ምጽአት መታሰቢያ አድርጎ መዝሙሩን ጽፏል። በዚህ ተራራ ላይ «እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት» (ማቴ.24፥3)። ተብሎ እንደተጻፈው ለደቀ መዛሙርቱ የደግም ምጽአቱን፣ የዓለምን ፈጻሜ፣ የትንሣኤ ሙታንን፣ ትምህርት በሰፊው ስላስተማረበት ይህን የተመለከተው ትምህርትና ምስጋና ሁሉ በስፋት የሚነገርበት፣ የሚዘመርበት፣ የሚሰበክበትና የሚዘከርበት አምስተኛው የዓቢይ ጾም ሳምንት ከእሑድ ጀምሮ አንዱ ሳምንት የነገረ ምጽአት መታሰቢያ በዓል መጀመሪያ ትምህርቱ በስፋት በተሰጠበት ደብረ ዘይት በተባለው ተራራው ስም ተሰይሟል።

ይህ የደብረ ዘይት በዓል ወይም አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት ሌሎች ስያሜዎችም አሉት። ዳግም ምጽዐት፣ የፍርድ ቀን፣ የጌታ ቀን፣ ሕልቀተ/ሕልፈተ ዓለም፣ ዕለተ ፍዳ፣ ዕለተ ደይን፣ ዳግመኛ ልደትና ትንሣኤ ዘጉባዔ በመባል በመጽሐፍ ቅዱስና በቅዱስ ያረድ የዜማ መጽሕፍት ይጠራል።

የደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ

ከዕለታት አንድ ቀን ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ሥነ ሕንፃ በትኩረት እያንዳንዱን ነገር በመመልከት አደነቁ። ጧት በጸሎት ጊዜ ጸሎታቸውን አድረሰው ሲጨርሱ የጧት ፀሐይ አርፎበት ያሸበረቀውን ቤተ መቅደስ ውበቱን አስተውለው ምን ጥበበኛ እንደሠራው እየተነጋገሩ እና እያደነቁ ነበር፤ ጌታችንንም አብሮ አድናቆትቻውን እንደሚጋራ ያስቡ ነበር፤ እርሱ ግን ያልጠብቁትን አስደንጋጭ ነገር ተናጋረ። ያ የሚያደንቁት ቤተ መቅደሱ እንደሚፈርስ፤ አያይዞም ከሞት በኋላ ተነሥቶ እንደሚያርግና ነገር ግን ዓለምን ለማሳለፍ ዳግም እንደሚመጣ፤ ወደፊት የሚሆኑ ሚሥጢራትን እና በቤተ መቅደሱና በሕዝቡ ላይ ወደፊት ሊደርስ የሚችለውን መከራና ስደት ሁሉ በትንሹ ጥቆማቸው። ከቤተ መቅደስ ተነሥተው ወደ ደብረ ዘይት ከተሻገሩ በኋላ እነዚህ ባጭሩ የጠቆማቸው  የማይቀሩ አስደንጋጭ ኩነታት ጉዳይ አእምሯቸውን ዕረፍት ነሳቸውና በሰፊው እንዲገልጽላቸው ጠየቁት። ጥያቄውም «እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት» (ማቴ.24፥3) የሚል ነው። በዚህ የጥያቄያቸው ክፍል እንደምናየው ጥያቄያቸው ዕለትና ምልክት ነው። ወይም «መቼ» እና «ምን» የሚል ነው። የቤተ መቅደሱ መፍረስ መቼ ይሆናል? የዓለም መጨረሻና የመምጣትህስ ምልክቱ ምንድን ነው? የሚል ነው። ጌታችንም በቀኙ ያቁመንና ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳይል በጥያቄያቸው ላይ ብቻ አተኩሮ ሰፊ ትምህርት ሰጥቷቸዋል።

መቼ ይሆናል ላሉት የመጀመሪያው ጥያቄ «ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም [ሰውም] ቢሆን የሚያውቅ የለም» (ማቴ.24፥36)። ሲል አጭር መልስ ሲሰጥ።ስለ ሁለተኛው የምልክት ጥያቄ ጉዳይ ግን መሸከም እስኪያቅታቸው ድረስ አስተምሯቸዋል። በሁለተኛው ጥያቄ ዙሪያ ማስጠንቀቂያዎች፣ ምክሮች፣ ማጽናኛዎችና ምሳሌዎች በስፋት የቀረቡበት ትምህርት በጥልቀት ተሰጥቷቸዋል።

ምልክቶቹ

1/ ሐሰተኞች ክርስቶሶች

ጌታችን በአንደኛ ደረጃ የተናገረው ምልክት በተለያየ ጊዜ በተለያየ ሀገር ብዙ ሐሰተኞች ክርስቶሶች እንደሚነሡ ነው። የጌታ ቃል አይቀርምና ከዚህ ቀደም ብዙ ሰዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ተነሥተው ነበር። የሐሰተኞች ክርስቶሶች ትምህርት ሲነሣ ዋናቸው ወይም አለቃቸው በዮሐንስ ራእይ ምዕራፍ 13 አውሬ ተብሎ የተጠቀሰውና  በቅዱስ ጳውሎስ «የዐመፅ ሰው እርሱም የየጥፋት ልጅ»  የተባለው ብዙ ጥፋትና መከራ የሚያደርሰው  ባለ 666 መለያ ምልክቱ ሐሳተኛ ክርስቶስ ነው። በሐዋርያት ሥራ 5፥36 ላይ ታላቁ የአይሁድ ሊቅ ገማልያል እንደተናገረው ከምጅመሪያ ምጽአቱ አስቀድሞም ቴዎዳስና ይሁዳ ዘገሊላ የተባሉ ሐሰተኞች መሲሆች ከእውነተኛው መሲሕ ከአምላካችን ክርስቶስ በፊት ተነሥተው ነበር እንዳለው አሁንም በዘመነ ክርስትና ከመጭራሻው ወይም ከዳግም ምጽአቱ አስቀድመው ብዙዎች ተነሥተዋል። ለዚህ ነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋጋችንን ይዞ እስኪመጣ ድረስ እናዳንሰናከል  «ብዙዎች፦ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ … በዚያን ጊዜ ማንም፦ እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም፦ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ» (ቁጥ. 5 እና 23)  ሲል አስቀድሞ ያስጠነቀቀን።

በሀገራችንም በኢትዮጵያ በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንገሥት እኔ ክርስቶስ ነኝ የሚል ሐሳዊ/ሐሰተኛ ክርስቶስ ተነሥቶ እንደነበር በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቧል። ይህ በሀገራችን ተንሥቶ የነበረው  ሐሳዊ ክርስቶስ  ልክ እንደ እውነተኛው ክርስቶስ 12 ሐዋርያት፣ 72 አርድእትና 36 ቅዱሳት አንስት አስከትሎ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያለ ሲንቀሳቀስ ንጉሡ አስቀርበው አንተ ማን ነህ? ቢሉት በድፍረት እኔ ክርስቶስ ነኝ አላቸው። ንጉሡም ክርስቶስማ ከደንግል ማርያም ተወልዶ አስተምሮ፣ ተሰቅሎ፣ ዓለምን አድኖ ከሞት ተንሥቶ ዐርጓል ዳግም ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል አንተ ግን ማነህ? ቢሉት አዎ ትክክል ነው። ከዚህ ቀደም ከቤተ እሥራኤል ከምትሆን ከድንግል ማርያም ተወልጀ፣ አስተምሬ ተሰቅየ ሙቼ ተነሥቼ ዐርጌ ነበር፤ አሁን ድግሞ ጥቁሮች አፍርካውያን ባይታወር አደረገን እንዳይሉኝ ከእናቴ ከድንግል መርዐተ ወንጌል ለጥቁሮቹ ዳግም ተወልጀ ነው አላቸው። ንጉሡም ሰይጣን በሰው እያደረ እንዴት ይጫወታል ብለው በሰይፍ አስቀጡት ተካታዮቹም ተበተኑ ይባላል።

2/ ጦርነት

ጦርነት ዱሮም ነበረ። የዚህ ዘመን ጦርነት ግን የበዛና በብዙ ሀገራት የሚካሄድ ነው፣ የዱሮ ጦርነት ሴቶችን፣ አቅመ ደካማ ሺማግሌዎችንና ሕፃናትን ለእልቂት የማያጋልጥ ነበር። የዘመናችን ጦርነት ግን ማንንም የማይለይ ለማንም የማይራራ ከባድ መሣሪያ ከሩቅ እየተላከ ሳይመርጥ ሁሉን የሚደፈጥጥበት፣ የሁሉን ሴት ወንድ ሕፃን አዋቂ ሳይለይ በጅምላ የሁሉን ደም የሚያፈስ አስቃቂነቱ ከመግለጫ ቋንቋ በላይ ሆኖ ይታያል። ይህንንም ጌታችን የዳግም ምጽአቱን ምልክት ለጠየቁት ለደቀ መዛሙርቱ ሁለተኛ ምልክት አድርጎ «ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ  ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና» (ማቴ. 24፥6-7) ሲል ተናግሮታል።

3/ ረሀብ እና ቸንፈር

የረሀብ ወሬ ላሉፉት ዓመታት ወደ ሌላ ሀገር መሄድ ሳያስፈልገን በገዛ ሀገራችን ስናየው ስንዳሳሰው የቆየጉዳይ ነው። አሁንም በቅጡ ሁነኛ መፍትሔ ያገኘ አይመስልም። ከ1983 ዓ/ም ወዲህ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ አንገቷን ስትደፋበት የቆየች ማታወቂያዋ ሁኖ ቆይቷል። ሌላ ምሳሌ ቢያስፈልግ ለመጨመሪያ ብቻ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ችግር ሳያጋጥማት በሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት ከ7 – 8 000 000 አንዳንድ ጊዜም እስከ 13 000 000 ሕዝብ ለአስቸኳይ ምግብ ርዳታ የተጋለጠባት ለማኝ እየተባለች የቆየች ሲሆን ይህም ሰው ሰራሽ ችግር ለጠላቶቻችን ማሣለቂያ አድርጎን ከርሟል። ይህም ዓይነት የኢትዮጵያ ህዝብ ሆነ ሌላው የሦስተኛው ዓለም ህዝብ ከሆዱ ውጪ እንዳያስብ፣ እንዳይፈላሰፍና እንዳይመራመር፣ ራሱን እንዳይችል፣ ስለሀገሩ እንዳይቆርቆር፣ እንዳያድግ ለሐላፊ የበላይነትና ሥልጣን ማሰንበቻ፣ በጥል፣ በተንኮልና በጭካኔ ሰዎች የሚፈጥሩት ችግር የምጽአት ሦስተኛ ምልክት ሆኖ በጌታችን ለደቀ መዛሙርት ተነግሯል «ረሀብም ቸነፈርም በልዩ ልዩ ሥፍራ ይሆናል» (ማቴ. 24፥7) ተብሎ እንደተጻፈ። በጌታችን ከተጠቀሱት የመጨረሻው ዘመን አስከፊ ምልክቶች አንዱ ረሀብ የተባለው ምልክት ነው ብለናል። አዎ የረሀብን አስከፊነት ነቢታም ቀደም ብለው ገለጽውታል፤ ከነቢያት አንዱ በረሀብ ከመሞት በሰይፍ ከመሞት የተሻለ እንደሆነ ተናግሯል።  «በሰይፍ የሞቱ በራብ ከሞቱት ይሻላሉ፤ እነዚህ የምድርን ፍሬ አጥተው ተወግተውም ቀጥነዋል» (ሠ/ኤር. 4፥9)። ይላል።

ቸነፍር፦ ትርጉሙ ተላላፊ በሺታ ወረርሺኝ ማለት ሲሆን በኀጢአትና በበደል ብዛት ምክንያት በእግዚአብሔር ከሚታዘዘ መቅሠፍት ጋር የተያያዘ መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ  በዘፀ. 5፥3። 2ኛ/ሳሙ. 24፥13-15። ሕዝ. 6፥11 ላይ እና ከዚህ በታች በተጠቀሱት ጥቅሶች እንረዳለን። በጌታችን ከተነገሩት የዕለተ ምጽ አት ምልክቶች አንዱ እንግዲህ ይህ ክፉ ነገር ነው። ረሀብና ቸነፈር በመጽሐፍ ቅዱስ ተደጋጋፊ ሁኖው ተነግረዋል (ት/ኤር. 14፥12፤21፥9። ሕዝ. 5፥12)። ረሀብ ባለበት ቸነፈር መንገሱና አቅም ማገኘቱ የታወቀ ነው። ሰው ምግብ ካላገኝ ትንንሹ በሺታ ሁሉ እንደሚገንበት የታወቀ ጉዳይ ነው። በመሆኑም ቸነፈር ባለበት ረሀብ እንዲሁም ረሀብ ባለበት ቸነፈር አይታጣም። ሰው ከታመመ ሥራ አይሠራም ሥራ መሥራት ካልቻለ ምግቡን አያገኛም ቢያገኝም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ራሱ ቸነፈሩ ወይም በሺታው ምግብ ስለምያስጠላው እየራበውና እየደከመውም እንኳ አይመገብም። በሌላ መልኩ ደግሞ መመገብ እየፈለገ ችነፈሩን በመፍራት የቅርብ አስታማሚ ስለማያገኝ ኃይሉና ሞራሉ ሲዳከም ቸነፈር በበሺተኛው ላይ ይሠልጥናል።

ከላይ እንዳየነው ጌታችን ቸነፈር በልዩ-ልዩ ቦታ ይሆናል ነው ያለው አሁን በዘመናችን በዚህ ሰሞን የተነሳው ኮሮና የሚል መጠሪያ የተሰጠው ወረርሺኝ ግን በመላ ዓለም ማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ተከሥቷል።

በዚህ ሰሞን ዓለምን እያስጨነቀ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወይም የወረርሺኝ መቅሠፍት መነሻውና ምንጩ መግብ ነው መድኃኒቱም ከምግብ እነዚህ እነዚህ አይነቶች ናቸው እያሉ በምግብ ዙሪያ የሚሽከረከሩ እና የሚንሸራሸሩ መል እክቶች በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት ይታያሉ። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ግን የኮሮና ዓይነት ወረርሺኝ መነሻው ምግብ ብቻ ሳይሆን ከምግባ ውጪ የፈጸመው አመፅና ኀጢአት ሁሉ እንደሚሆን መጋረድና መሸፈን የለበትም። ስለሆነም ፍቱን መድኀኒቱ እውነተኛ ዓለም አቀፋዊ ንስሐ ብቻ ነው።

4/ የምድር መንቀጥቀጥ

የመሬት መንቀጥቀጥ ባለፉት ዓመታት በርካታ ጉዳት በተለያዩ ሀገሮች እንዳደረሰ የሚዘንጋ አይደለም። በ1999፣ ጀምሮ እስከ ዛሬ በተለያዩ ሀገሮች በተለያየ ጊዜ የበዙዎችን ሕይወት የቀጠፈ አያሌዎችን ቤት ንብረት አልባ ያደረገ የመሬት መቀጥቀጥ ተከሥቷል። በሄይቲ፣ በታይዋን፣ በቱርክ፣ በፊልፕንስ፣  ወዘተ ተከሥቷል። ይህም ለደቀ መዛሙርቱ የዓለም ፍጻሜ ምልክት የማግኘት ጥያቄ የተሰጠው «የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል» (ማቴ. 24፥7) ተብሎ  በጌታ የዓለም ፍጻሜ ምልክት ተደርጎ የተነገረው ቃል አይቀርምና እየሆነ ነው።

5/ የክርስቲያኖች መከራ

ክርስቲያኖች መከራ ተለይቷቸው ባያውቅም በመጨረሻው ዘመን የከፋ መከራ ይጋረጥባቸዋል። እየጀመረም ይመስላል። ኢቴስቶች፣ ኢ ክርስቲያናዊ ሃይማኖት አለን የሚሉ ሁሉ በክርስቲያኖች ላይ ከምን ጊዜውም በላይ ችግር መፍጠር የጀመሩበት ጊዜ ነው። በአውሮፓ የክርስቲያኖች ጥያቄ ተገቢ መልስ የማያገኝበት፣ የቤተ ክርስቲያንን ጥያቄ ለማስተናገድም መንግስታዊ መሥሪያ ቤቶች ፈቃደኛነታችውን እያጡና ይህንን ወንጀላቸውን ለመሸፈንም በሕግ አንቀጽ እየፈጠሩለት ይታያሉ። «በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል ይገድሏችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ» (ማቴ. 24 ቁጥ.9)። ተብሎ እንደተጻፈው ሃይማኖተኛነት እንደ ኋላ ቀርነት ከሐዲነት እንደተራማጂነትና ሥልጡንነት የሚታይበት ዘመን ላይ እንዳለን ግልጽ ነው። ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ክርስቲያኖችን ወደ ማግለልና ወደ መወንጀልና ማሳደድ የሚያድግ መሆኑ ከሚታዩት ፍንጮች መረዳት ይቻላል።

በእንዲህ አይነት የመከራ ዘመን የክርስቶስ ተቃዋሚዎች በክርስቲያኖች ላይ ከሚያመጡት መከራ የበለጠ የክርስቲያኖች እርስ በእርስ መከዳዳት ጭንቁን ያከፋዋል፣ መከራውን መራራ ያደርገዋል «በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ» (ማቴ.24፥10) ተብሎ በጌታ እንደተነገረ ከሐድያኑ ሆነ ብለው በእቅድ በክርስቲያኖች መካከል መከዳዳትን በመፍጠር ለዚህ ነው ክርስቲአኖች ክርስትናን መተው ያለባቸው ፍቅርና መተማመንን፣ ሰላምና ጸጥታን ለማሰፈን ነው ክርስትናን የምንቃወመው እያሉ ድጋፍ ያሰባስባሉ። ክርስቲያኖች ከላይ እስከ ታች ልንኖረው የሚገባውን ክርስቲያናዊ ሕይወት መኖር ስላቃተን እውነት አማኞች ከሆኑ ለምን ይለያያሉ፣ለምን ይጣላሉ፣ ለምን ይናናቃሉ ለምን ይጨካከናሉ፣ ወዘተ የሚል ጥያቄ በማስነሣት ክርስቶስን በማሰደብና የራሳችን መከራ በማብዛት በከሐዲው ዓለም ውስጥ ከክርስትና ትምህርት ውጭ የምንኖረውን ሕይወት ከምር ልንፈትሽ እና ልንታረም ልንዘጋጅም ይገባናል።

6/ ሐሰተኞች ነቢያት

በዲያብሎስ መንፈስ ምትሐታዊ አሠራርን እያሳዩ አይቻላቸው እንጂ ቢቻላቸው የተመረጡትን ሳይቀር የሚያስቱ  ነቢያት ነን የሚሉ ብዙዎች ደፋሮች እንዲመነሡ ጌታችን ስድስተኛው የዳግም ምጽአቱ ምልክት አድርጎ ጠቅሷቸዋል። በነቢዩ ኤልያስ፣ በነቢዩ ኤልሣዕ ስም እያጭበረበሩና እየዋሹ በምትሐታዊ አሠራር የሚያስቱ ሐሰተኞች እንደሚነሡ «ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ …ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ … እንግዲህ፦ እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ » (ማቴ 24 ቁጥ.11፥ 24 እና 26) ተብሎ በግልጽ ተነግሯል። እንግዲህ በዘመናችን በሀገራችን ሆነ በሌላው ዓለም በነቢይነትና በሰባኪነት ስም የሚደረገውን የንግድና የርኩሰት እንቅስቃሴ በማስተዋል መከታተልና መጠበቅ ያስፈልጋል።

7/ የፍቅር ማጥፋት

ሌላውና አሳዛኙ ጉዳይ የፍቅር መቀዝቀዝ ነው። ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው። የሰው ልጅ ፍቅርን ማጥፋት እና ማጣት የሌለበት ሰፊ ሀብቱ ነው። አሁንም «ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች» (ማቴ.24፥12) የሚለው ትንቢት እንዳይፈጸምብን ፍቅርን መንከባከብ፣ ማልማትና ማስፈት ይገባል። ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው። ፍቅር የመልካምና በጎ ንገር ሁሉ መገኛና ምንጭ ነው። ፍቅር ምዕራገ ጸሎታችን፣ መሥዋዕታችን እና ዕጣናችን ነው። የመንግሥተ ሰማያት ቁልፋችን ነው። የኀጢአት መሸፋኛችን ነው። የእግዚአብሔርን ፊት የምናይበት ብርሃናችን የዓይናችን ዓይን ነው። «እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ» (ዮሐ. 13፥35) በዚህ መለኮታዊ ቃል መሠረት የክርስቲያኖች መታወቂያችንም ፍቅር ሊሆን ይገባ ነበር። አንድም ነገር ዓለም እኛን በፍቅር ከሌላው የለየበትና ያወቀበት ሥራ አላሳየንም። መቼ ይሆን ፍቅር የክርስቲያኖች መታወቂያ የሚሆን? አሁኑኑ በያለንበት ልንጀምረውና ልናለማው የምንችለው ቢሆንም ፈቃደኛ ልብና ትሑት ሰብእና በማጣታችን ምክንያት ያ ጊዜ ይናፍቃል።

8/ የወንጌል መዳረስ

የወንጌል ለዓለም መዳረስ ለደቀ መዛሙርቱ የዳግም ምጽአቱ ምልክቶች ሁነው ከተሰጡት አንዱ ነው። በፍርድ ቀን በመጫረሻው ጊዜ በክርስቶስ አምኖ እና እምነቱን በሥራ ግልጾ ስለመኖር የት ነበር ምን ሥራህ ተብሎ ሲጠየቅ አልሰማሁም አላየሁም አላወኩም የሚል አያመልጥም። በጌታችን «ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል» (ማቴ. 24፥ 14) ተብሎ እንደተነገረው በሁሉም ቤት ወንጌል ይሰበካል። ከሁሉም ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስ ይገኛል። እግዚአብሔር ሳያስተምር፣ ሳያስጠነቅቅ፣ ሳይመክርና ሳይገሥፅ አፈርድምና ሁሉም ወንጌልን ሊሰማ ግድ ይሆናል፤ አሁንም ሆኗል። በዚህ ዘመን አንድ መምህር ያስተማረው መንፈሳዊ ትምህርት፣ አንድ ሰባኪ የሰበከው ስብከት በአንድ ጊዜ በመላው ዓለም ከሚደመጥበት፣ ያም ባይሆን በመላው ዓለም በአንድ ቀን ተዳርሶ የሚውልበት የቴክኖሎጂ ዘመን ላይ እንገኛለን።

የምጽአቱ ምሳሌዎች

/ መብረቅ

የአመጣጡ ፍጥነት እንደ መብረቅ ነው። «መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥  የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናል» (ማቴ 24፥ 27):: ተብሏል።

/ ሌባ/ ሰራቂ

ቀኑ አለመታዎቁ እንደ ሌባ ነው። ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር … የሰው ልጅም በማታስቡበት ሰዓት ይመጣል (ቁጥ. 43-44)። ለታሪካዊ ማስገንዘቢያ የኖህ ዘመንም እንደዚሁ ባልታሰበ ሠዓት እንደሚመጣ ማስገንዚያ ሆኖ በጌታችን ቀርቧል። (ከቁጥ. 37-39)።

/ በለስ

ከበለስ ምሳሌነት ወስደን እንድንማር ሌላ አስደናቂ ሥነ ፍጥረታዊ ምሳሌ ጊታችን ሰጥቶናል። «ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ» ቁጥር  32። በመጀመሪያ የበለስን ነገር መናገር ይገባል። በለስ በክረምት የምትደርቅ በበጋ የምትለመልም ወይም ክርምት ከማይስማማቸው ዕፀዋት አንዷ በመሆኗ ስትለመልም የክረምቱ ጊዜ ማለፉን የበጋ ጊዜ መተካቱን ሰው እሷን ተመልክቶ መረዳት ይችላል። እንደዚህም ሁሉ እናንተም ከላይ የተዘረዘሩት ምልክቶች ሁሉ ሲከሠቱ የመጨረሻው የፍርድ ቀን፣ የዓለም ፍጻሜና የጌታ ዳግም መምጣት ጊዘው እንደቀረብ እወቁ። ቅርበቱም ከዳጃችሁ የደቻችሁን ያህል እንደሆነ እወቁ ብሎ የጊዜ ማወቂያ ምሳሌ አደርጎ ነው የጠቃሳት።

በሌላ በኩል በሊቃውንት አተረጓጎም ከዚህም ያለፈ ምሥጢር እንዳለው ይናገራሉ። ጌታችን በቁሙ በዕለተ ሠሉስ ከተፈጠሩት ዕፀዋት መካከል አንዷ ስለሆነችው ስለ በለስ ዛፍ ሳይሆን በበለስ የመሰላት እሥራኤልን ነው። «ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ» ማለቱ እሥራኤል ከዝርወት ተመልሳና ተሰባስባ መንግሥት ስታቋቋም፣ በዓለም ታውቃና እና ተደራጅታ ስትታይ ማለቱ ነው ይላሉ።

የደብረ ዘይት በዓል አከባበር በገጠሪቱ ኢትዮጵያ

ባዓለ ደብረ ዘይት እንግዲህ ተጽፎና ተተርጉሞ የማያልቅ ሰፊ፣ ጥልቅና ምጡቅ ትምህርትን የያዘ በዓል ነው። በደቀ መዛሙርቱ ሁለት ብቻ  ጥያቄዎች ተነሥቶ ያስተማረው የዕለተ ምጽአቱ ነገር በአጭር ጽሑፍ የሚካተት ስላልሆነ በሀገር ቤት የታላቋ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ኦርቶዶክሳውያን ይህንን በዓል በየዓመቱ እንዴት እንደሚያዘክሩት በማሳየት እናቆየዋለን።

በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ይህ በዓል በሀብታሙም በድሀውም በትልቁም በትንሹም ዘንድ በበጎ ሥራ በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ተከብሮና ታስቦ ይውላል። ሕዝበ ክርስቲያኑ ያለውም የሌለውም ቤት ያፈራውን ምግብ ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣና ከመንፈሳዊ አገልግሎት በኋላ አስቀድሞ ድሆችን በመጎብኘት፣ በመመገብና በማጽናናት ከደሆች የተረፈውን እርስ በእርስ በመገባበዝ፣ የተጣላ በማስታረቅ በቅፅረ ቤተ ክርስቲያን ከወይራውና ከፅዱ ሥር አርፎ ይውላል።

ክርስቲያኑ ሕዝብ ይህንን የሚያደርግበትን ምክንያትም ሲገልጽ  ዓለምን ለማሳለፍ ጌታችን የሚመጣ በዚህ ዕለት ስለሆነ ሲመጣም እንዲህ ያለ ደግ ሥራ የሠሩትን ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ  መጥታችኋልና። እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ብሎ መንግሥቱን እንዲያወርሰን ነው ይላሉ። ሁለተኛው ምእመናኑ ለምን ይህን እንደሚያደርጉ ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ ደግሞ የሞቱት ነፍሳት በዚህ ዕለት ይሰበሰባሉ ወይም ይመጣሉ ዘመዳቸው የሆነ ጥሬ ወይም እንጀራ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስዶ ለነዳያን የሰጠ እንደሆነ ደስ ይላቸዋል። የሞተ ዘመድ ያለው አንድ ሰው በደብረ ዘይት ዕለት ጥሬ ወይም እንጀራ ወደ ቤተ ክርስቲያን አምጥቶ ካልመጸወተ የዘመዱ ነፍስ መጥታ የኔስ ዘመዶች አልቀዋል ብላ አዝና ትመለሳለች ይላሉ። ምስጢሩ ከላይኛው አይርቅም።

በአዲስ አበባና በአንዳንድ ታላላቅ ከተሞች ደግሞ ምእመናን የቤተ ስብ መንፈሳዊ አባት አድረገው ወደያዟቸው ካህናት ቤት ሂደው ይጠይቋቸዋል። ወደየ መምህረ ንስሐዎቻቸው ቤት በመሄድ ተሰብስበው ስለነገረ ምጽአት ሲማሩ ይውላሉ።

ሦስተኛ የሰው ዘር የጋራ ልደት እና ዕድገት

በታላላቅ ድንጋዮች የታተሙ መቃብሮች በውስጣቸው የያዙአቸውን ሙታን ይሰጣሉ፣ የሙታን ሥጋ ከረጅም የእንቅልፍ ዓለም ይባንንና ሁሉም በአንድ ቀን ከመቃብር ተወልደው በአንድ ቀን አድገው ወደ ፍርድ አደባባይ ይሰበሰባሉ። ታላቁ ዘንዶ ለብዙዎች ስሕተት ምክንያት የሆነው ዲያብሎስ ከነሠራዊቱ ለዘላለም በማይፈታ በእሳት ሰንሰለት ታስሮ ወደ ገሃነመ እሳት ይጣላል፡፡ ፊተኞቹ ሰማይና ምድር ከፍጡራን ፊት እንደወረቀት ተጠቅልለው ያልፋሉ፣ ስፍራም አይገኝላቸውም ለዘለዓለምም ያልፋሉ፡፡ (ኢሳ. 13፥ 6-13፤ መክ. 12፥ 17፤ 1ኛ ተሰ. 4፥ 13-18፤ 2ኛ ጴጥ. 3፥ 10)፡፡

ሦስተኛ ልደት መባሉ ለክርስቲያኖች ከዚህኛው በፊት የምንወለዳቸው ከሥጋ እናትና አባት የምንወለደው የሥጋ ልደትና በውሃና በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በ፵ና በ፹ ቀን ከመንፈሳዊ አባት ከእግዚአብሔር የምንወልደው  እነዚህ  ሁለት ልደታት ስላሉ ነው።

ከዚህ ሁሉ በኋላ በእግዚአብሔር ዘንድ ቀነ ቀጠሮ የተያዘላት በሰው ዘንድ የማታልፍ መስላ የምትታየው ይህች አታላዋ ዓለም እንደ መጋረጃ  በሕልፈት መጠቅለያ ተጠቅልላ እንዳልነበረች ትሆናለች። ጣዕሟ፣ ለዛዋ ሁሉ ይሟጠጣል፣ ተስፋ ያደረጓትም ሁሉ ያፍሩባታል። ፍጻሜ ዓለም ይሆናል፡፡ ምድር ከመሠረቷ ትናጋለች፣ ፀሐይ ትጨልማለች፣ ከዋክብትም እንደ ቃርያ ፍሬ ከሰማይ ይረግፋሉ፡፡ (መዝ. 12፥ 2፤ ኢሳ. 13፥ 6-13፤ ኢዩ. 2፥ 10-11፣ 30-32፤ ማቴ. 24፥ 29-41፤ ራዕይ 6፥12-17)፡፡

በበጉ ደም የተዋጁና ሃይማኖታቸውን የጠበቁ ታማኝ የክርስቶስ ልጆች ገናናውንና ታላቁን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን ሊቀበሉ በታላቅ ክብር በደመና ወደ ሰማይ ይነጠቃሉ፡፡ በተዋሕዶ የከበረ ወልደ አብ ወልደ ማርያም የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስም በታላቅና እጅግ አስፈሪ በሆነ መለኮታዊ ግርማ የብዙ ብዙ በሚሆኑ እልፍ አእላፋት ቅዱሳን መላእክት ታጅቦ ይመጣል፡፡ (ዘካ. 14፥ 6፤ ማቴ. 25፥ 31፤ 1ኛ ተሰ. 4፥ 16)፡፡

በዚያን ጊዜ የእሱንና የመላእክቱን ግርማ ችሎ በፊቱ የሚቆም ማን ይሆን? (ኢዩ. 2፥ 11) አመጣጡም እንደቀደመው ከሐና ወደ ቀያፋ ከዚያም ወደ ጲላጦስ ከዚያም ወደ ሔሮድስ አደባባይ ሲያንገላቱት ዝም እንዳለ በዚህ ዓይነት አመጣጥ አይደለም፡፡ የሚመጣው በሚያስፈራና በሚያስደነግጥ መለኮታዊ ግርማና ክብር ነው፡፡ (መዝ. 49፥ 2)፡፡ መጥቶም ዝም አይልም እሳት በፊቱ ይነዳል ኃጥአንን ከፊቱ ጠራርጎ ወደ ገሃነመ እሳት የሚጨምር አውሎ ነፋስም አለ፡፡ (ማቴ. 24፥ 30፤ ራዕይ 1፥ 7)። ይህም በፊቱ የሚነድ እሳትና አውሎ ነፋስ ሐጥዓንን ከጻድቃን የሚለይበትን ሥልጣኑንና እውነተኛ ፍርዱን ያመለክታል።

እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ጻድቃንን በቀኙ ኃጥአንን በግራው ለይቶ ያቆማቸዋል፡፡ በቀኙ ያሉትን “እናንተ የአባቴ ቡሩካን ወደ እኔ ኑ ወደ አባታችሁ መንግስተ ሰማያት ግቡ፡፡” ብሎ ለዘለዓለም ሕይወት ይጠራቸዋል፡፡ በግራው ያሉትን ደግሞ እጅግ በሚያስፈራና በሚያስደነግጥ የቁጣ ቃል “እናን ርጉማን ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀው ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ” ይላቸዋል፡፡

ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ትወርዳለች ማለት ለምእመናን ትሰጣለች፡፡ ምእመናንም ርስት መንግስተ ሰማያትን ይወርሳሉ ብርሃን ለብሰው ብርሃንን ተጎናጽፈው ለዘለዓለም በደስታ ይኖራሉ፡፡ (ማቴ. 25፥ 31-46፤ ራዕይ 21፥ 1-2)፡፡

ኦርቶዶክሳውያን! ነቢዩ ኤርምያስ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡-በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች እወቁ በእርስዋም ላይ ሂዱ ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ” (ት.ኤር. 6፥16)፡፡ በማለት እንደተናገረው በቀደመችው በመልካሚቱ የሕይወትና የጽድቅ መንገድ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ እምነታችን እስከ መጨረሻው ድረስ ጸንተን ልንኖር ይገባል፡፡

ማጠቃልያ

የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ሃያ ዐራትን (24) ወይም የነገረ ምጽአትን ትምህርት የሚከተሉትን  ዋና ዋና መልእክቶች በማስጨበጥ ልናጠቃለልው እንችላለን።

ተጠንቀቁ፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ (ቁጥ.4)።

ንቁ፦ጌታችሁ በምን ሠዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ (ቁጥ. 42) ።

ተማሩ እወቁ፦ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ [ከላይ የተናገራቸውን ምልክቶች ሁሉ] ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ (ቁጥ. 33)።

አትደንግጡ፦ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ (6)።

ትጉና ጸልዩ፦ ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ (20)።

ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፦ ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።(44)።

ጽኑ፦ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል (ቁጥ.13)።

እነዚህን ሁሉ ምክሮች፣ ማስጠንቀቂያዎችና ማፅናኛዎች በአእምሮ ጽላት ቀርፆ በማስተዋል በሃይማኖት እና በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ጸንቶ የኖረ የሕይወትን ቃል ሰምቶ የክብር፣ የድልና የጽድቅ አክሊልን ተሸልሞ በዘላለማዊ ሕይወት በደስታ ይኖራል።

የእግዚአብሔር ጥሪ ሁሉም የአዳም ዘር መንግሥቱን እንዲወርሱ ቢሆንም የሰይጣንን ወጥመድና አሸከላ ሁሉ አልፈው፤ በሐሰተኞች ክርስቶሶችና በሐሰተኞች ነቢያት ምትሐታዊ ተአምራት ሳይሳቡና ሳይሰናከሉ እስከ መጨረሻው በቀናች ሃይማኖታቸው ፀንተው  በዚያ በዳግመኛ ልደት እና የመጨረሻ የዋጋ ቀን በጌታቸው ቀኝ የሚቆሙ የታደሉ ናቸው።

እንግዲህ እኛን በቀኙ ያቆመን ዘንድ፣ የአባቴ ቡሩካን ኑ ወደ ጌታችሁ ደስታ ግቡ የሚለውን የሕይወት ቃሉንም ያሰማን ዘንድ የአምላካችን የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። ስለ እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም  ብሎ ልጇ መድኃኔዓለም በዚያ በሚያስፈራ የፍርድና የዋጋ መቀብያ ቀን ይራራልን። በዕለተ ዐርብ የፈሰሰው ክቡር ደሙ ከትንሣዔ ዘጉባዔ ክብርና ከዘላለም ሕይወት የሚለየንን ዕድፋችንን ይጠብልን አሜን።

አባ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ

መጋቢት ፳፻፲፪ ዓ/ም