በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ሰሙነ ሕማማት
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከትንሣኤ በፊት ያለው አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት /የሕማማት ሳምንት/ በማለት ትዘክረዋለች። ሕማማት የሚለው ቃል ሐመ፣ ታመመ ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማሙና ሞቱ የሚዘከርበት ሳምንት ነው።ሰሙነ ሕማማት በላቲን Hebdomas Sancta or Hebdomas Maior፣ በግሪክ ደግሞ Ἁγία καὶ Μεγάλη Ἑβδομάς, Hagia kai Megale Hebdomas (ታላቁ ሳምንት) ተብሎ ይጠራል፡፡ በኛ ደግሞ ሰሙነ ሕማማት ይባላል። ሰሙነ ሕማማት ከሆሣእና እስከ ትንሣኤ ባሉት ቀናት ጌታችንን ለመያዝ አይሁድ የመከሩበት፣ ምክራቸውን ያፀኑበት፣ ጌታችንን ሳይዙ እህል ላለመቅመስ ክፉ መሐላ የተማማሉበት፣ጌታችንን የያዙበት፣ የገረፉበት እና በዕለተ ዐርብ በቀራንዮ የሰቀሉበት ሳምንት ይህ ሰሙነ ሕማማት ተብሎ ይጠራል። ሰሙነ ሕማማት እስከ ዐራተኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ከጾሙ ተለይቶ ለብቻው ይከበር ነበር። በኋላ ግን በባሕረ ሐሳብ ቀመር መሠረት ጾሙም፣ ሕማማቱም፣ ትንሣኤውም ተያይዘው እንዲከበሩ ተደረገ። ምዕራባውያን ከዐርባ ጾም ውስጥ የመጨረሻውን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ያደርጉታል። የምሥራቃውያን /ኦርየንታል/ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ግን አርባውን ጾም ጨርሰን ከሆሣእና ቀጥሎ ያለ አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት አድርገን እናከብራለን።
በሌላ በኩል ሰሙነ ሕማማት የኦሪት ዘመን ምሳሌም ነው። በዘመነ ኦሪት (አዳም ከገነት ከተባረረበት እስከ ጌታችን በቤተ ልሔም እስከተወለደበት ዘመን) የሰው ልጅ የጽድቅ ሥራው ለመንግሥተ ሰማያት የማያበቃው ነበር። ይልቁንም ነቢዩ ‘’ጽድቃችን የመርገም ጨርቅ ሆነ’’ ኢሳ 64:6 እንዳለ የአዳም ዘር በሙሉ እስከ ዕለተ ዐርብ ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ እስካዳነን ድረስ በዲያብሎስ ባርነት ሥር ነበርንና ሰሞነ ሕማማትም የዘመነ ፍዳ ምሳሌ ነው።ይህንንም ለማሰብ በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት በሰሙነ ሕማማት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፣ ስብሐተ ነግህ አይደርስም፣ ሥርዓተ ማኅሌት፣ ሥርዓተ ተክሊል፣ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይም፣ ጸሎተ አስተሰርዮም አይደረግም፣ ጥምቀተ ክርስትና አይፈጸምም፣ በመስቀል መባረክ፣ ኑዛዜ መስጠትና መቀበል፣ እግዚአብሔር ይፍታሕ ማለት አይኖርም። ከላይ የተዘረዘሩት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች አስቀድሞ በዕለተ ሆሳዕና ይከናወናሉ።በሰሞነ ሕማማት ከዚህ ዓለም በሞት የሚለይ ሰውም የፍትሐት ጸሎት አይደረግለትም። ይህ ማለት በዕለተ ሆሣዕና በአካለ ሥጋ እያለን ካህናት አባቶቻችን የፍትሐት ጸሎት ያደርጉልናል። ሰሙነ ሕማማት የተለየ ሳምንት ነውና፣ እንኳን ሥጋዊ ደስታና ሣቅ ጨዋታ መንፈሳዊ ደስታም የተከለከለ ነው፡፡በሰሙነ ሕማማት ምእመናን እርስ በርስ በመሳሳም ሰላምታ አይለዋወጡም።ይህም ይሁዳ ጌታችንን በመሳም አሳልፎ ሰጥቷልና ያንን ለማሰብ ነው።
በሰሞነ ሕማማት መጻሕፍተ ኦሪት፣ መጻሕፍተ ነቢያት፣ የዳዊት መዝሙር ይነበባል።በዚህ ልዩ በሆነ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠልስት፣ በቀትር በተሰዓትና በሠርክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርሰቲያን በመጓዝ ስለጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ምዕራፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማሙንና ሞቱን ያዘክራሉ።’’እርሱ ግን ስለመተላለፋችን ቆሰለ፣ ስለበደላችንም ደቀቀ፣ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፣ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን’’ ኢሳ.53፡4-7 ተብሎ የተነገረው ቃል ተፈጽሞ ጌታችን ለድኅነተ ዓለም ሲል በአጭር ደረት በጠባብ ደረት ተወስኖ የተቀበለው ጸዋትወ መከራ የሚዘከርበት ሳምንት ነው።ነቢያት መቼ ወደ ዚህ ዓለም መጥተህ ከዓመተ ፍዳ ታድነናለህ? ሲሉ የተማፀኑበት ጸሎት፣የጌታችንን ስለእኛ ሲል የመያዙን፣የመገረፉን እና የመሰቀሉን ነገር ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው በትንቢት መነፀር እየተመለከቱ የተጻፉ የነቢያት መጻሕፍት ይነበባሉ፣ይጸለያሉ።
ከቤተ ክርስቲያናችን ሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት ውስጥ የረቡዕ እና ዐርብ ጾም የሚጾምበት ምክንያትም
በሰሙነ–ሕማማት አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ ከዕለተ ሰኞ ጀምሮ እስከ ረቡዕ ድረስ ክፉ ምክር ሲመክሩ ቆይተው በዕለተ ረቡዕ ምክራቸውን ያፀኑበት ቀን ሲሆን በዕለተ ዐርብ ደግሞ ጌታችንን የሰቀሉበት ቀን ስለሆነ ነው። በሰሞነ ሕማማት ሳምንት በቤተ ክርስቲያን ግብረ ሕማማት የተባለ መጽሐፍ ይነበባል።ግብረ ሕማማት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለዘሩ ድኅነት የተቀበለውን መከራ የሚዘክር መጽሐፍ ነው፡፡ ግብረ ሕማማት ማለት የሕመም ፣ የመከራ ሥራ ማለት ነው፡፡ የጌታን መከራውን ሥቃዩን ሕማሙን በሠዓትና በጊዜ ከፍሎ የሚናገር ፣ እንዲሁም ምን በማን መጸለይ እንደሚገባውም በዝርዝር የሚገልጽ በመሆኑና የጌታችንን ሕማም በምናስብበት በሰሙነ ሕማማት በዋነኝነት አገልግሎት ላይ የሚውል በመሆኑ ግብረ ሕማማት ተባለ፡፡ መጽሐፉ ግብረ ሕማማት እንዲባል በውስጡ የታዘዘ መሆኑን የአማርኛው ትርጉም መቅድም ይገልጻል፡፡በግብረ ሕማማት መግቢያ ላይ ‘ሐዋርያት ለስብከት ወንጌል በሚፋጠኑበት ጊዜ፣ስለ እርሱ ስለ ጌታችን ታሪኩና ተአምራቱን ይከታተሉ ከነበሩት መካከል የተከበሩና የታወቁ ሊቃውንት በኢንፎስና በገማልያል እጅ ተፅፎ በቅድስት ሀገር በኢየሩሳሌም በክብር ቦታ ተቀምጦ የተገኘ ነው’ ይላል።
የሰሙነ ሕማማት ሥርዓቶች
የሰሙነ ሕማማት ዜማ፥ ከሰኞ እስከ ረቡዕ – ግዕዝ፣ ሐሙስ – አራራይ፣ ዓርብና ቅዳሜ – ዕዝል ነው፡፡ በእነኚኽ ዕለታት፣ ከኹሉም በፊት የሠዓቱ ተረኛ አገልጋይ ቃጭል እየመታ ሦስት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ይዞራል፡፡ የሰባት ቀን ውዳሴ ማርያም፣ አንቀጸ ብርሃን፣ መዝሙረ ዳዊት በሙሉ ይጸለያል፤ በዕለቱ ተረኛ መምህር/መሪጌታ/ የዕለቱ ድጓ ይቃኛል፡፡ ድጓው ከአራቱ ወንጌላት ምንባብ ጋራ እንዲስማማ ኾኖ ነው የሚቃኘው፡፡ ድጓውን እየተቀባበሉ እያዜሙ ይሰግዳሉ፡፡ ድጓው ሦስት ጊዜ ተመላልሶ ከተዘለቀ በኋላ፡–
ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
ዐማኑኤል አምላኪየ ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለም
ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለም፤
ኀይልየ ወጸወንየ ውእቱ እግዚእየ እስመ ኮንከኒ ረዳዕየ እብል በአኮቴት
እየተባለ፣ በቀኝ በኩል ስድስት፣ በግራ በኩል ስድስት ጊዜ እየተዜመ ይሰገዳል፡፡ በድምሩ ዐሥራ ኹለት ጊዜ ማለት ነው፡፡ በዚያው ልክ አቡነ ዘበሰማያት በዜማ /በንባብ/ ይደገማል፡፡
ከዚያ በመቀጠል፡–
ለአምላክ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
ለሥሉስ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
ለእዘዙ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
ለመንግሥቱ፣ ለሥልጣኑ፣ ለምኩናኑ፣ ለኢየሱስ፣ ለክርስቶስ፣ ለሕማሙ /በዓርብ ለመስቀሉ/ ይደሉ
እያሉ በቀኝ በግራ እየተቀባበሉ ይሰግዳሉ። በመቀጠል የነግሁ ምንባብ መነበብ ይጀምራል። በመጨረሻ ተኣምረ ማርያም እና ተኣምረ ኢየሱስ ይነበባሉ፡፡ ከዚያ ከዳዊት መዝሙር ምስባክ ተሰብኮ የሰዓቱ ወንጌል ከተነበበ በኋላ፣ ጸልዩ በእንተ ጽንዓ ዛቲ የተባለው ጸሎት በካህኑ ሲነበብ፣ ምእመናንም፣ አቤቱ ይቅር በለን፤ እያሉ በመስገድ ይጸልያሉ፡፡
ከዚያም ኹለተኛው ሥርዓተ ስግደት ይጀመራል። ዜማውን በቀኝ በግራ በመቀባበል፣ አንዱ ይመራል ሌላው ይቀበላል፡፡ እንዲኽ በማለት፡–
ኪርያላይሶን/አምስት ጊዜ/ በመሪ በኩል
ኪርያላይሶን/ሁለት ጊዜ/ ዕብኖዲ ናይን በተመሪ በኩል
ኪርያላይሶን ታኦስ ናይን
ኪርያላይሶን ማስያስ ናይን
ኪርያላይሶን ኢየሱስ ናይን
ኪርያላይሶን ክርስቶስ ናይን
ኪርያላይሶን ዐማኑኤል ናይን
ኪርያላይሶን ትስቡጣ ናይን
በዚኽ መልኩ አንድ ጊዜ ከተዘለቀ በኋላ እንደገና ይደገማል፡፡ በመጨረሻ በግራ በቀኝ በማስተዛዘል 41 ጊዜ ይደገማል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት፣ የጌታችን ኅቡእ ስሞች ናቸው፡፡ ኪርያላይሶን ማለት አቤቱ ይቅር በለን ማለት ነው፡፡ ምንባባቱ ከመለያየታቸው በቀር በኹሉም ዕለታት ሥርዓቱ ተመሳሳይ ነው፡፡
በሰሙነ ሕማማት ያለው ዐርብ፣ የስቅለት ዐርብ ይባላል፤ የአዳምን ነጻነት ለመመለስ ዕዳ በደሉን ተሸክሞ የተንገላታው የዓለሙ ኹሉ መድኃኒት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛ ኾኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ የተሰቀለበት ነው፡፡ ስቅለት፣ ከዘጠኙ የጌታችን ዐበይት በዓላት አንዱ ሲኾን፣ የጌታን የመከራውንና የሕማሙን ነገር የምናስታውስበት በመኾኑ የሚከበረውም በስግደት፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በንባብና በትምህርት ነው፤ ስግደቱም ከሰሞኑ ኹሉ የበለጠ ነው፡፡
በመኾኑም በስቅለት ዓርብ፣ መሪው ዕዝል ይመራል፤ ሕዝቡ ይከተላል፤ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ፡፡ በየመሀሉ፥ “ወጸቢሖ ተማከሩ ሊቃነ ካህናት = ሲነጋም ሊቃነ ካህናት ተማከሩ” የሚለው ዜማ፣ በመሪ በተመሪ በሕዝብ ተሰጥዎ ይከናወናል። ምንባቡም ስግደቱም ድጓውም እንዳለፈው ይቀጥላል፡፡ ይህም ቀኑን በሙሉ ሲከናወን ውሎ በአሥራ አንድ ሠዓት፣ ካህናት በዐራት ማዕዝን ቆመው እግዚኦታ ያደርሳሉ፡፡ ዕለቱን የሚመለከቱ መዝሙራት ተመርጠው ይነበባሉ፡፡ ንሴብሖ እየተባለ ቤተ መቅደሱን በመዞር በከበሮ በጸናጽል በሕማሙ ያዳነን እግዚአብሔር ይመሰገናል፡፡ ዑደት የሚደረገው ሥነ ስቅለቱን በመያዝ ነው፡፡
ምእመናንም፣ በሰሙነ ሕማማት የሠሩትን ኃጢአት እየተናዘዙ በካህናት አባቶች ንስሐ ይቀበላሉ፤ ካህናቱም በወይራ ቅጠል ትከሻቸውን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጣቤ ማለት ቸብ ቸብ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ይኸውም፣ በአንድ በኩል የክርስቶስ ግርፋት ተሳታፊዎች መኾናቸውን ለመግለጥ ሲኾን፣ በሌላ በኩል የተግሣጽ ምሳሌ ነው፡፡ ወይራ ጽኑዕ ነው፤ የተቀበልከው መከራም ጽኑዕ ነው፤ እኛም ይህን መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን፤ ለማለት ነው፡፡
ጥብጣብ የሚደረግለት ሰው፣ በሕማማቱ ወቅት የፈጸመው በደል ወይም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር፣ አቅሙ ተመዝኖ የስግደቱ ቁጥር ከፍ እንዲል ይደረጋል፤ በታዘዘውም መሠረት ይፈጽማል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዕለተ ስቅለት ሲሰግድ፣ ሲጸልይ፣ ሲያነብ ከዋለ በኋላ፣ በካህኑ ኑዛዜ ወደየቤቱ ይሰናበታል፡፡ መስቀል መሳለም የለም፤ የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል፣ ጌታ በደሙ ቀድሶ፣ የምሕረት ምልክት፣ የሕይወት ዓርማ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ አድርጎ የሰጠበትን የትንሣኤውን ብርሃን እስክናይ ድረስ፡፡
ከዓርብ ስግደት መልስ፣ እስከ እሑድ /የትንሣኤው ሌሊት/ ድረስ ኹለት ቀን የሚያከፍሉ ምእመናን፣ ምንም ሳይቀምሱ ያድራሉ፡፡ ይህም አክፍሎት ይባላል፡፡ የማያከፍሉ ግን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው ይሰነብታሉ። ብዙ ጊዜ የሚቀመሰውም፣ ከጸሎተ ሐሙስ የተረፈውን ጉልባንና ዳቦ ነው፡፡
ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና በጸሎተ ሐሙስ የሚበላ ንፍሮ ነው። እስራኤላውያን፣ ከግብጽ ተሰደው በሚወጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር፣ አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ኹኔታ ያመለክታል፡፡ ይህን መሠረት አድርጎ የሚዘጋጀው ጉልባን እንዲኹም ቂጣ፣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ውኃ የሚያስጠማ በመኾኑ የጌታን መጠማት ያስታውሳል፡፡
ቅዳሜ ጠዋት፣ ምእመናኑና ካህናቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፤ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸም፣ “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሀደ = በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ፤ ትንሣኤውን ገለጸ፤ የምሥራች” እየተባለ እየተዘመረ ቄጤማው ቤተ መቅደሱን ዞሮ በካህኑ ተባርኮ ለምእመናን ይታደላል፤ ምእመናኑም እየሠነጠቁ በራሳቸው ያስሩታል፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ላልመጡትም፣ ካህናቱ ልብሰ ተክህኖአቸውን በመልበስ፣ መስቀልና ቃጭል ይዘው በየሰበካቸው፣ ቄጤማውን የምሥራች እያሉ ያድላሉ፤ ምእመናንም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ቄጤማው በራስ ላይ መታሰሩ፥ አይሁድ በጌታችን ጭንቅላት ላይ የእሾህ አክሊል ያሰሩበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡ ጥንተ አመጣጡና ምስጢሩ ግን፣ ከአባታችን ኖኅ ታሪክ ጋራ የተያያዘ ነው፡፡ ምድር በጥፋት ውኃ በጠፋችበት ወቅት፣ የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሠረችው ቄጤማ ባፏ ይዛለት በመግባት ነው፡፡ ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች፦ የኃጢአት ውኃ ጠፋ፤ ኃጢአት – ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ፤ በክርስቶስ ሞት ነጻነት ተሰበከ፤ ታወጀ በማለት፣ አዳምና ልጆቹ፥ ከለምለሚቱ ሥፍራ ከተድላ ገነት መግባታቸውን ለመግለጽ፥ ምእመናን ቄጤማ ይዘው፣ ቄጤማ አስረው ይታያሉ፤ ትንሣኤውንም ለሚናፍቁ ትልቅ ብሥራት ነው፡፡
የሰሙነ ሕማማት ቅዳሜ፣ “ሰንበት ዓባይ” ትባላለች፤ ጌታችን፣ የሦስት ዓመት ከሦስት ወር የማዳን ሥራውን በመስቀል ላይ ፈጽሞ በከርሠ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት ናት፡፡ ኹለተኛም፣ ይህች ዕለት ሥዑር ቅዳሜ፤ የተሻረች ቀዳሚት ሰንበት ትባላለች፡፡ ሥዑር መባሏ በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም ነው፤ “ቅዳሜ ሹር” እንዲሉ፤ አንድም፣ በዚኹ ቀን በሚባለው ዕዝል ውስጥ፥ ስኢሮ ሞተ፤ ሞትን ሽሮ ተነሣ፤ ይላል፤ ሞትም የተባለው ዲያብሎስ ያመጣው ሞተ ነፍስ ነውና፣ የተሻረ የተባለው ዲያብሎስ ነው፡፡
በአዳም ከሲኦል መውጣትና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መነሣት፣ ቤተ ክርስቲያን የምታሰማን የምሥራች ከደስታ ኹሉ የበለጠ ነው። ምንም እንኳን፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው እሑድ በመንፈቀ ሌሊት ቢኾንም፣ አዳም ከሲኦል ወጥቶ ወደ ገነት መግባቱ የታወቀው፤ የክርስቶስ ትንሣኤው የተመረመረው በቀዳም ስዑር ስለኾነ፣ የትንሣኤው ብሥራት በአፈ ካህናት ለሕዝበ ክርስቲያን ይነገርበታል፡፡ የኀዘኑ ዜማዋና የኀዘኑ ልብሷ ተለውጦ፣ የጸናጽል የከበሮ ድምፅ ታሰማለች፡፡
ቅዳሜ ምሽት፣ የአብያተ ክርስቲያናቱ ቅጽርና ዙሪያው ነጫጭ በለበሱ ምእመናን መልቶ ሲታይ ያስደንቃል፡፡ የአብያተ ክርስቲያናቱ ደወሎች ሲደወሉ፣ መዘምራኑ የማሕሌቱን፣ ቀሳውስቱ የሰዓታቱን ሥርዓት ማከናወን ይጀምራሉ፡፡ ማሕሌቱ ተቁሞ ቆይቶ በምልጣኑ ሠዓት ዲያቆኑ ከዳዊት መዝሙር፣ ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃሕ እምነዋም… ብሎ በሰበከ ጊዜ፣ የሕዝቡ ደስታ በጣም የበዛ ይኾናል፤ በውስጥም በውጭም ያለው ሕዝብ በእልልታና በጭብጨባ ተቀባብሎ ያደምቀዋል፡፡
ከዚኽ በኋላ፣ የትንሣኤውን ነገር የሚያነሣው ወንጌል ተነቦ፣ መሪው መስቀሉን ከዲያቆኑ ተቀብሎ፦ ዮም ፍሥሓ ኮነ በሰንበተ ክርስቲያን እስመ ተነሥአ ክርስቶስ እሙታን = ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶአልና ዛሬ በክርስቲያን ሰንበት በዚኽች በእሑድ ፍሥሓ ኾነ፤ ደስታ ተደረገ፤ ብሎ መርቶ መዘምራኑ ይህንኑ ተቀባብለው ይዘሙታል፤ ያሸበሽቡታል፡፡
ከዚኽ በኋላ፣ ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ = ትንሣኤህን ለምናምን ኹሉ ብርሃንህን ላክልን፤ የሚለውን እስመ ለዓለም የተባለውን ቀለም አለዝበው በወረቡት ጊዜ፣ ለተሰበሰበው ሕዝበ ክርስቲያን፣ ከሰም የተሠራ የጧፍ መብራት ይታደልና ዑደቱ ሊደረግ ይጀምራል፤ ከጧፉ ውጋጋን የተነሣም ምሽቱ ሰዓተ መዓልት ኾኖ ይገኛል፡፡ ይህን ተከትሎም፣ ሦስት ጊዜ ከተደወለ በኋላ ቅዳሴ ለመግባት ሲዘጋጁ ይታያል፤ መንፈቀ ሌሊት ሲኾን ቅዳሴ መቀደስ ይጀመራል፤ ድርገትም በወረዱ ጊዜ በጣም ብዙ ሰው ሥጋወደሙን ለመቀበል ተዘጋጅቶ ይቀርባል፡፡ከቅዳሴም በኋላ፣ ኹሉም ወደየቤቱ ተመልሶ በትንሣኤው በዓል ከየቤተሰቡ ጋራ ደስ ብሎት የሚገባውን ያደርሳል፡፡ በበነጋውም በየቤተ ዘመዱ እየሔደ፣ እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታልህ፤ እንኳን አብሮ ፈታልን፤ እየተባባለ ይጠያየቃል፤ እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታልን፤ ማለት፣ ሁለት ወር ሁዳዴ ሲጾም ሰንብቶ በጌታ ትንሣኤ ምክንያት ጾሙ ስለቀረለት ነው፡፡በተጨማሪም፣ የአክፋይ ወይም ገብረ ሰላመ እየተባለ፣ ምእመናን፣ ከማዕዶት እስከ ዳግም ትንሣኤ ያሉትን ዕለታት ተከፋፍለው ለሰበካቸው ካህናት፥ ጠላ በመንቀል፣ እንጀራ በአገልግል በመውሰድ ያበላሉ፤ በየቤታቸውም እየጠሩ ይጋብዛሉ፤ እንዲኹም ዘመድ ዘመዱንም ሲጠይቅ ይሰነብታል። ይህም፣ ጌታችን ከተነሣ በኋላ እስኪያርግ ድረስ፣ ለደቀ መዛሙርቱ ሦስት ቀን ግብር አግብቶ መግቧቸው ነበርና ያንን ያሳስባል፡፡
ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን አሜን
+++++++++++++////////////++++++++++/////////////+++++++++++/////////+++++++++++++++