በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ጾመ ነነዌ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአጽዋማት ቀኖና መሠረት ሰባት አጽዋማት አሉ። ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ በዕለታት ተወሳክና በዓመቱ መጥቅዕ ድምር ውጤት ወይም በመባጃ ሐመር የምትውልበት ወይም የምትጾምበት ቀን የሚታወቀው ጾመ ነነዌ ናት።

ነነዌ ማን ናት?

ስለ ነነዌ ትንሽ ማወቅ አስፈላጊ ነው። ነነዌ በጤግሮስ ወንዝ ዳር በኃያሉ በናምሩድ ተመሠረተች፤ ዘፍ. 10፥11፣12። ነነዌ ሰፊና ያማረ መነገሻ ከተማ ነበረች። የከተማው ቅጥር ረዝመት 12 ኪ.ሜ. ነበረ። አሦር የሚባል ጥንታዊ ሀገር ዋና ከተማ ነበረች። እንደ ኦስሎ፤ እንደ አዲስ አበባ እንደ ስቶክሆልም። ጥንተ ታሪኩ ባጭሩ አሦር የተባለው የሴም 2ኛ ልጅ፤ (ዘፍ.10፥22) ነው። አሦር አሦራውያን ለተባሉት ሕዝቦች የመጀመሪያ አባት ሆነ፣ ሀገራቸው በላይኛው መስጴጦምያ ነው። ነነዌም ዋና ከተማቸው ነበረች፣ መንግሥቷ ጠንካራ በነበረችበትና በተስፋፋችበት ጊዜ በሰሎሞን ልጅ በሮበዓም ዘመን ሰሜን (እስራኤል) እና ደቡብ (ይሁዳ) ተብላ ከሁለት በመከፈሏ ብርታት ያጣችውን የእስራኤልን መንግሥት ስትፈታተን እና ስትወጋ ትኖር ነበር።

ነነዌ ዋና ከተማዋ የሆነች አሦር በዚህ ድርጊቷ በ720 ቅድመ ል/ ክ የአሥሩን ነገድ መናገሻ ሰማርያን ተቆጣጠረች። ህዝቡን አፈለሰች ወይም ማርካ ወስዳ በማያውቀው አምስት ሀገር በትነችው፣ ሳይመለስ ጠፍቶ ቀረ። በሰማርያ ደግሞ የሌላ አካባቢ ሕዝብ አምጥታ አሠፈረችበት።

ነነዌ ማእከሏ የሆነው የአሦር መንግሥት የይሁዳን ማለትም የደቡቡን መንግሥትም በዝብዛለች። በአንድ ወቅት እንዲያውም ንጉሡን ምናሴን ወደባቢሎን ወስዳው ነበር። ነገር ግን የይሁዳ መንግሥት መናገሻ ወይም ዋና ከተማ የነበረችውን ኢየሩሳሌንና ህዝቧን አላጠፋችም።

በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት አሦራውያን እግዚአብሔርን እጅግ አድርገው ተፈታትነውት ስለነበረ የእግዚአብሔር መልአክ ሠራዊታቸውን አጠፋ «በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ፥ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ። የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነሥቶ ሄደ፥ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ» (2ኛ ነገ. 19፥10፥35) ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጻፈ። ነነዌ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ612 በባቢሎን መንግሥት እክትያዝና እስክትፈርስ ደረስ «ታላቂቱ ከተማ» እየተባለች ትታወቅ ነበር። የአሦር ዋና ከተዋ የሆነችው በ700 ዓመት ቅ.ል.ክ. በሰናክሬም ዘመነ መንግሥት ነው።

ጾመ ነነዌ ወይም የነነዌ ጾም ለምን ተባለ?

ጾመ ነነዌ ማለት የነነዌ ከተማ ሰዎች የጾሙት የንስሐ ጾም ማለት ነው። የነነዌ ኃጢአት ዐመፅ እና በደል በነቢዩ በዮናስ ዘመን ሰማይ ነክቶ ነበር። የነነዌ ሰዎች ንሥሐ እንዲገቡ እና ሊመጣ ካለው ቁጣ ይደኑ ዘንድ እንዲያስጠነቅቅ እግዚአብሔር ነቢዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ላከው። ነነዌ ነቢዩ ዮናስ ከተወለደበትና ካደገበት ከጋት ሔፌር 800 ኪ.ሜ. ያህል ትርቅ ነበር። መጀመሪያ ከተል እኮው ቢያፈገፍግም «ዮናስም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሊገባ ጀመረ፤ ጮኾም፦ በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች አለ» (ዮናስ 33፥4) እንደተባለው ነቢዩ ዮናስ የኋላኋላ ወደ ነነዌ ሂዶ የእግዚአብሔርን መልእክት አውጇል። በዚያን ጊዜ የነበሩት ሰዎችም «የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ» (ቁጥ.5) እንዲል መጽሐፉ በንስሐ በጾምና እራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀው ከጥፋትና መዓት ድነዋልና ጾመ ነነዌ ተባለ።

የነነዌ ሰዎች ኃጢአት ምንደን ነው?

የነነዌ ከተማ ኃጢአት በትንቢተ ዮናስ ውስጥ አንድ ሁለት ተብሎ አልተገለጸም፤ በጥቅሉ «ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ» (ዮናስ 1፥2) ተብሎ በእግዚአብሔር ከመገለጹ በቀር አልተዘረዘረም። ይሁንና ከዚህ ጥቅስ ክፉታቸው ወደ ፊቴ ወጥቶአልና የሚለው የልዑል አምላክ ቃል የኃጢአታቸውን ታላቅነት ያመለክታል።

ኃጢአታቸው በዮናስ መጽሐፍ ውስጥ አልተዘረዘረም አልን እንጅ በሌሎቹ መጻሐፍት ውስጥ ግን ተዘርዝሯል። ለምሳሌ ነቢዩ ናሆም የነነዌ ኃጢአት ምን ምን እንደነበረ ገልጿል። የተወሰኑትን ቀጥለን እንመልከትና እኛም ራሳችንን መርምረን በዚች ሱባዔ እንጠቀምባት።

/ በእግዚአብሔር ላይ ክፋትን ማሤር።

ይህንን ለማርጋገጥ «ስለ ነነዌ የተነገረ ሸክም፤ የኤልቆሻዊው የናሆም የራእዩ መጽሐፍ ይህ ነው» ብሎ የሚጀምረው የኒቢዩ ናሆም የትንቢት መጽሐፍ «በእግዚአብሔር ላይ በክፉ የሚያስብ፥ ክፋትን የሚመክር፥ ከአንተ ዘንድ ወጥቶአል» (ናሆም 1፥11) በማለት አንደኛው ኃጢአተ ነነዌ በእግዚአብሔር ላይ ክፋትን ማሤር እንደነበር ተገልጿል። በእግዚአብሔር ላይ ማሤር ውድቀትን ማፋጠንና አወዳደቅን ማክፋት ነው። በዮናስ ዘመን የነበሩት የነነዌ ነገሥታት በንስሐ ሀገራቸውን በጾምና በጸሎት ከጥፋት ያዳኑ ሲሆኑ ከዚያ በፊትና በኋላ የነበሩት ግን ለጭካኔያቸው መግለጫ ቋንቋ አልነበረውም። እንዲያውም ይባስ ብለው እግዚአብሔር የሚባለውን የእስራኤል አምላክ አጥፍተን ጣዖታችንን እናስመልካለን በኢየሩሳሌም ለእርሱ የሚሠዋና ስሙን የሚጠራ እንዳይኖር እናደርጋለን እያሉ በልዑል እግዚአብሔር ላይ ማሤር ጀመሩ።

በዘመናችን ፊደል ባስቆጠረቻቸው፣ ግብረ ግብነት ባስተማረቻቸው፣ ሀገር ጠብቃ፣ ነጻነታቸውን አስከብራ፣ባቆየችና አሁንም የሚገባትን ሁሉ እያደረገች በምትገኝ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናቸው ላይ እንደሚከተለው ሲያሤሩ እንደቆዩት ማለት ነው።

የሃይማኖት እምነት ለአብዮቱ ጠንቅ ነው። የቀደመው የፊውዳል ሥርዓትም ለሺህ ዘመናት የደነደነ ድሩን የገመደው በአብያተ ክርስቲያናት ስለሆነ ይሄን ድር ለመበጣጠስ የግድ ሕዝቡን በሌኒንና በሌሎችም ፍልስፍና በማጥመቅ ፀረ-አምላክ እና ፀረ-ቤተ ክርስቲያን ማድረግ ለደርግ ይዋል ይደር የሚባል ጥያቄ አይደለም። የማርክሲዝም-ሌኒኒዝም አማኞች አብዮቱ እንዲያብብ ይሄን አጣዳፊ ጉዳይ ከሶቪየት ዩኒየን ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመምከር እንዴት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ከርስቲያን መደምሰስ እንዳለባት በዝርዝር አስቀምጧል።

ታላላቅ ገዳማት የሆኑትን እንደ አክሱም፣ ደብረዳሞ፣ ላሊበላ፣ ደብረ ሊባኖስ፣ ዝቋላ እና ሌሎችም በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙትን እንዲሁም በጎጃም፣ በጎንደር፣ በወሎና በሌላም ቦታ ያሉትን የቤተ ክርስቲያን ህንጻዎች ሁሉ ለጭቁኑ ህዝብ የታሪክ መዘክር እንዲሆኑ የኪነ-ጥበባት አዳራሽ ማደርግ … ።

እንዲህ በእግዚአብሔር ዘንድ ሕዝብን ወክላ በሕዝብ ዘንድ እግዚአብሔርን ወክላ በምድር ላይ የምትገኘውን በእግዚአብሔር ቅድስት መንግሥት እየገዘገዟት በርሱም ላይ 50 ዓመታትን ሴያሤሩ ሲያፌዙ እንደቆዩት እንደ ደርግ እና ወያኔ ማለት ነው። ልዩነቱ ወያኔዎቹ የአልባያ ኮምኒስቶች ነን ማለታቸው እና ሃይማኖታችሁ ምንድነው ተብለው ሲጠየቁ የብዙዎቻችን ወላጆች ኦርቶዶክሶች ናቸው እኛ ግን የምናምነው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው እያሉ ማላገጣቸው ነው።

እንኳን በሁሉ ቦታ በመላ፣ ሁሉን አዋቂ በሆነው በእግዚአብሔር ላይ ይቅርና በቅዱሳን ላይም ማሤር የራስን ስንፍና ከማጋለጥ እና አወዳደቅን የከፋ ከማድረግ እንዲሁም ሀገርን ለሁለንተናዊ ውድቀት ከመዳረግ ውጭ ከጥቅም ወገን አንድም ይህንን ይጠቅማል አይባልም።

ባለፈው ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በእግዚአብሔር ላይ ስታሤሩ የነበራችሁ እድሜ አግኝታችሁ በሕይዎት ያላችሁ በመንግሥትነትም ሆነ በተቃዋሚነት የኖራችሁ ያላችሁ አስተውሉ። በነነዌ ከተማ ባለ ሥልጣናት ምሳሌ ሆነው ንስሐውንና ሱባዔውን በመጀመርና በመምራት ሕዝባቸውንና ከተማቸውን ከእግዚአብሔር ቁጣ ባዳኑባት ሱባዔ ንስሐ ግቡባት፤ ዕድል አያምልጣችሁ በእግዚአብሔር ስም ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ እግዚአብሔር እንለምናችኋለን።

ምንም ያህል በደል ብትፈጽሙ ወደእግዚአብሔር ለመመለስ አይክበዳችሁ፣ የምንበድለው አባታችን እግዚአብሔር ክፋታችንን እንጅ እኛን አይጠላም «ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች። እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እንቢ ብትሉ ግን ብታምፁም፥ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና» (ኢሳ. 1፥18-20)። ተብሎ እንደተጻፈ።

ከኮሎኔል መንገሥቱ ኃ/ማርያም ጀምሮ እስከታችኛው ከኢሐደጎቹም ከላይ እስከታች የነበራችሁ እንግዲህ እውነት ኢትዮጵያን የምትወዷት ከሆነ፣ ልማቷንና ሁለንተናዊ ብልጽናዋን፣ ልዕልናዋንና ክብሯን የትወዱላት ከሆነ፤ የልጆቻችሁና የልጅ ልጆቻችሁ ሀገር እንድትሆን ከፈቀዳችሁ በነጻ ርምጃ ያለፍርድ የፈሰሰው የአባቶችና እናቶች ወንድሞችና እኅቶች እንዲሁም ሕፃናት ደም እየጮኸ ሲረብሻት እንዳይኖር በዘመናችሁ ንስሐ ገብታችሁ አሳረፏት። ስለተፈጸመው ግፍ የተተበተበችበትን የዐመፅ ማሠሪያ በንስሐ ቁረጡላት፣ ፍቷት የሰው መኖሪያ ትሁን።

/ በጦርነት ጊዜ ጭከናና ዝርፊያ

የነነዌ ሰዎች በተለይ ባለሥልጣኖቹና ባለጉልበቶቹ ጫካኝ ባሕርያቸው የአራዊት ንጉሥ በሚባለው በአንበሣ ተመሰሏል «አንበሳው ለልጆቹ የሚበቃውን ነጠቀ፥ ለእንስቶቹም ሰበረላቸው ዋሻውን በንጥቂያ፥ መደቡንም በቅሚያ ሞልቶታል» ናሆም 2፥12-13) ተብሎ በምሳሌ እንደተነገረው።

መናገሻ ከተማቸው ነነዌ የሆነችው አሦራውያን እንደ እኛ ዘመን ወያኔዎች እጅግ ጨካኞች ነበሩ። ንጉሦቻቸው ሁልጊዜ በተሸነፉ ሕዝቦች ላይ በሚፈጽሙት አሠቃቂ ቅጣት ይደሰቱ ነበር። የሚፈሩትን ሕዝብ ከሀገሩ አፈናቅለው ወደሌሎች ግዛቶቻቸው በማጋዝ አርመኔያዊ ተግባር በላያቸው መፈጸም የመንገሥታቸው መመሪያ ነበር። የተሸነፉ ከተሞች መሪዎች ከመገደላቸው በፊት እንዲሠቃዩና ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ አካላቸው እንዲቆራረጥ ይደረግ ነበር።

በመሆኑም በነቢዩ ዮናስ ዘመን የነበሩት በእርሱም ስብከት አምነው እና ተፀጸተው ንስሓ ቢገቡም በንስሐ የሚገኙትን ልማትና በረከት ጤና እና ሕይወት የለመዱት ክፋታቸው ሸፍኖባቸው እንደገና ወደዚሁ ከተማዋ እንድትገለበጥ ወደሚያደርስ ክፋታቸ በመመለሳቸው ነቢዩ ናሆም ተላከባቸው። የህ የእግዚአብሔር ሰው «ለደም ከተማ ወዮላት! በሁለንተናዋ ሐሰትና ቅሚያ ሞልቶባታል፤ ንጥቂያ ከእርስዋ አያልቅም … ስብራትህ አይፈወስም፥ ቍስልህም ክፉ ነው፤ ወሬህንም የሚሰሙ ሁሉ እጃቸውን በአንተ ላይ ያጨበጭባሉ፤ ክፋትህ ሁልጊዜ ያላለፈችበት ሰው ማን ነውና?» ሲል በመጽሐፉ በምዕ 3፥1 እና ቁጥ 19 ላይ ሁለተኛው በደሏ ደም አፍሳሽነት፣ ቀማኛነትና ዘራፊነት እንደነበረ መናገር ብቻ ሳይሆን ወዮታ እንደማይለቃትና መገልበጧ እንደምይቀር ተናግሮባታል። በተቆረጠ የሰው እራስ በከተማ መግቢያ በር ላይ ፒራሚድ በመሥራታቸው የሚኩራሩ እነ ስልምናሦር ሳልሳዊ ነገሥታቶቿ የነበሩ ነነዌ በንስሐ ሕይወት ባለመጽናቷ ወደ ትፋቷ በመለሷ ቅዱሳን ነቢያት ዮናስ እና ናሆም ወዮላት ትገለበጣለች እያሉ እንደተናገሩት በ612 ዓ.ዓ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ተገልብጣለች ጠፍታልች።

/ ዝሙትና መተት ወይም ጥንቆላ

ይህንን ወደ ሌላ ሳንሔድ በዚሁ ስለ ነነዌ የተነገረ ሸክም በሚለው በነቢዩ ናሆም መጽሐፍ «ስለ ተዋበችው ጋለሞታ ግልሙትና ብዛት ይህ ሆኖአል፤ እርስዋም በመተትዋ እጅግ በለጠች፥ አሕዛብንም በግልሙትናዋ፥ ወገኖችንም በመተትዋ ሸጠች» (3፥4) ተብሎ የተነገረውን አስተውሎ ማረጋገጥ ነው። በዚህ ጥቅስ ዘማዊት በዝሙቷ የተባለችው በነነዌ ከተማ የፍቅር አምላክ እየተባለች ትመልክ የነበረችው ጣዖት እንዲሁም ከዚሁ ጋር በተያያዘ የረከሰችውን ከተማዋን በአጣቃላይ ለማለት ነው። የነነዌ ኃጢአቶች ከላይ የተዘረዘሩት ብቻ አልነበሩም፤ በንግድ አጭበርብሮ መብዝበዝና የመሳሰሉት ሁሉ እንደነበሩ በትንቢተ ናሆም ተገልጿል።

እንግዲህ ከላይ ከተጠቀሱት የነነዌ ኃጢአቶችው በዘመናችን በየቤቱ፣ በየከተማው፣ በየሀገሩ፣ በየቤተ መንግሥቱና በየጉልበታሙ የማይሠራው የትኛው ነው? ክህደቱ፣ ደም ማፍሰሱ፣ ቋንቋ አልባ ጭካኔው፣ በእግዚአብሔር ላይ ማሤሩም፣ ዝሙቱ፣ መተቱ። ጥንቆላው፣ ግፉ፣ በንግድ ማጭበርበሩ ሰማይ አልነካም ወይ? በእነዚህ ታላላቅ የነነዌ ኃጢአቶች ያልተበከለ ሀገርስ በዘመናችን ይኖር ይሆን? በየትኛው አህጉር ነው የሚገኘው? ዓለማችን አሁን እኮ ከእኛ የራቀች አይደለችም። በሀገራችን በኢትዮጵያ በኛ ዘመን የሚታየው፣ የሚሰማው፣ የሚደረገው ከኃጢአተ ነነዌ ቢከፋ እንጅ የሚሻል፤ ቢባዛ እንጂ የሚያንስ አይደለም።

ማጠቃለያ

እንዲህ ዓይነቱ ርኩሰት በንስሐ ካልተወገደና በዚህ ሁሉ ረኩሰት ፈንታ ጾና ጸሎት፣ ፍቅርና ሰላም ፍህና ርትዕ እምነትና ምግባር ካልተተካ ድህነትና ስደት፣ ጦርነትና ሑከት፤ ደም መፍሰስና መናከስ፣ በሺታና አንበጣ፣ ሥቃይ መከራ ከምድር ላይ አይርቁም። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ሞታችንና ሕይወታችን በእጃችን ሰጥቶናል ማለት ነው።

ሱባዔውን እንደ ነነዌ ሰዎች ሱባዔ የሠመረ ያድርግልን።

የምሕረትና የቅርታ አባት ልዑል እግዚአብሔር በብዙ ፈተና ውስጥ የምትገኘውን ሀገራችንን ኢትዮጵያን ዳሯን እሳት መሃሏን ገነት ያድርግልን፤ ሳትጣላቸው የሚጣሏትን ሁሉ ይያዝላት።

ኮቬድ 19 የሚባለንና ሌላውንም ሁሉ ሥፍር ቁጥር የሌለው በሺታ ከዓለም ላይ ያጥፋልን። አሜን!

አባ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ።
የካቲት 14 ቀን 2013 ዓ/ም።