እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አሸጋገረን!!!
የመስከረም ወር የተባረከ የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመታት ወሮች ርእስ መሆኑን መጽሐፈ ስንክሳር ይነግረናል። በዚህ መሠረት በኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በመስከረም ወር የሆነበትን ምክንያት ሊቃውንቱ ሲያትቱ ብርሃናት ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ክዋክብት የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው፡፡ ያን ጊዜ ሌሊቱ ከቀኑ ጋር እኩል 12 ሰዓት ይሆናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ለዘመን መታወቂያው ይሆን ዘንድ ፀሐይና ጨረቃ ከዋክብትንም ፈጠረ” ይላልና /ሔኖክ. 21፥49/፡፡ በሌላ በኩልም በዘመነ ኖኅ በፍል ውኃ አጥለቅልቆ በኃጢአት ሕይወት ይኖሩ የነበሩት የኖኅ ዘመን ሰዎች ቀጥቶ ካጠፋ በኋላ ከንፍር ውኃ ምድር የተገለጠችበት ወር ነው /ኩፋሌ. 7፥1/፡፡ “በመጀመሪያው ወር ምድር ታየች የንፍር ውኃም ከምድር ደረቀ” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል መሠረት አድርገው የአቡሻኸር ሊቃውንት የዘመን መለወጫን ታሪካዊ አመጣጥ ያስቀምጣሉ፡፡ እንግዲህ መስከረም አንድ ቀን የዘመን መለወጫ፥ አሮጌውን ዘመን ጨርሰን መጪውን አዲሱን ዓመት የምንቀበልበት ቀን ናት። በልዩ ስም ቅዱስ ዮሐንስ ተብላ የተሰየመች ሲሆን ፍፁም መንፈሳዊ በሆነ ሁኔታ ትከበራለች።
ስለዚህ ይህችን ዕለት በፍጹም ንጽህና ሆነን ታላቅ በዓል አድርገን ልናከብር እንደሚገባን ያስተምራሉ፤ ይህች ዕለት ከሌሎች ዕለታት ተለይታ የተባረከች ናትና ከክፉ ሥራዎችም ሁሉ ተለይተን እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝባቸውን አዳዲስ የሆኑ በጎ ሥራዎችን ልንሠራባት ይገባል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እነሆ የቀደመው (አሮጌው) አልፎ ሁሉ በክርስቶስ ሐዲስ እንዳለ።(2ኛ ቆሮ 5፥17፤ ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም)
የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖናዊ ሥርዓት ያጠኑ ሊቃውንት ደግሞ አዲስ ዓመት መስከረም አንድ ቀን መሆኑን አስመልክተው በክታባቸው እንዳስቀመጡት በአራቱ ወንጌላውያን ዘመኑን ይከፍሉታል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን በዘመነ ዮሐንስ ተፀንሶ በዘመነ ማቴዎስ ተወልዶአል፡፡ በዘመነ ማርቆስ ተጠምቋል፡፡ በዘመነ ሉቃስ ተሰቅሎ ዓለምን ከፍዳና ከመርገም ነጻ አውጥቷል፤ እያሉ ያስረዳሉ፡፡ ከእነርሱም ማቴዎስና ዮሐንስ ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል ሲሆኑ ማርቆስና ሉቃስ ደግሞ ከሰባ ሁለቱ አርድዕት ናቸው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ አዳምን “— በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ” (ዘፍ 3፥17) እንዳለው ይህ የእግዚአብሔር ቃል ሕገ ተፈጥሮአዊ ሆኖ የሰው ልጅ ወጥቶና ወርዶ፣ አርሶና ቆፍሮ በወዙና በድካሙ እንጀራውን የሚበላ ሆኗል። በዚህም መሠረት በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል (መዝ 64፥11) እንዳለ፤ ዘር ተዘርቶ እሸት አፍርቶ ምድርም በልምላሜ ተጊጣ እንስሳትም ለምለም ሣርን ግጠው ፅሩውን ውሃ ጠጥተው ጠግበውና ወፍረው የሚታይበት ጊዜ ነው የመስከረም ወር።
ስለዚህ ይህ የዘመን መለወጫ አዲስ ተስፋ በልባችን የሚመላለስበት ጊዜ ነው። ቅድስት በሆነች በዚች ቀን የተተነበየው ትንቢት፣ የተቆጠረው ሱባኤ ተፈፀመ፣ ከዘመነ ፍዳ ወደ ዘመነ ምሕረት የምትሸጋገሩበት ጊዜ ደረሰ፤ እያለ ያወጀው የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ታሪክ ይነገራል። መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የጻድቃን የሰማዕታት በኩር፣ የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያው ሐዋርያ፣ መምህር፣ ሰማዕት፣ የብሉይ ኪዳን ነብያትም መጨረሻ ነውና፤ ነብያት ይወርዳል ይወለዳል እንዳሉ፥ እርሱ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ (ዮሐ 1፥29) ብሎ ስብከት የጀመረው እርሱ ነውና፣ ገና በማህፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስን የተቀበለና ለጌታችን የመጀመሪያውን የምስጋናና የስግደት መብዐ ያቀረበ፣ የሀዲስ ኪዳንን ብሥራት ከሰው ልጆች ሁሉ በፊት ያወቀ፣ ስለሆነ፣ የብሉይ (የአሮጌው) ዘመን ፍፃሜ ማግኝቱንና የሀዲስ ኪዳንን መምጣት የመጀመሪያ የብሥራት አዋጅ ነጋሪ በመሆኑ፤ የቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሊቃውንትና አባቶች ምሳሌና ምስጢርን በማስማማት ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከብሉይ ወደ ሀዲስ፣ ከዓመተ ኩነኔ ወደ ዓመተ ምህረት የተሸጋገርንበትን እንድናስብ ቤተክርስቲያን ይህቺን ቀን በሥሙ ሰይማ ዓመታትን ለሚያቀዳጅ እግዚአብሔር ምስጋናን ታቀርባለች። ስለዚህ የአዲስቱ ዓመት የመጅመሪያዋ አዲሲቱ ቀን ቅዱስ ዮሐንስ ትባላላች። በመሆኑም በየዓመቱ አዲስ ዓመትን ስንቀበል በተለየ ተስፋና ደስታ ነው፤ የጎመን ምንቸት ውጣ የገንፎ ምንቸት ግባ እንዲሉ።
መስከረም ሰማዩ፣ ወንዙ፣ ጅረቱ፣ የደፈረሰውና የጠቆረው ሁሉ የሚጠራበት ጊዜ በመሆኑ ቤተክርስቲያን ልጆቿ ከብልየት እንዲታደሱ፤ በመንፈስ እንዲጎለምሱ፤ ከርኩሰት፣ ከጣዖታት፣ ከቂም ከበቀል እንዲርቁ፣ እንዲጠሩና እንዲነጹ፤ በ1ኛ ጴጥ 4፥3 “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና።” እንዳለ፤ አሮጌውን በርኩሰት የተሞላውን ሕይወታችንን ከአሮጌው ዘመን ጋር አሳልፈን የምድር አበቦች እንዳበቡ በእምነትና በምግባር እንድናብብ ቤተክርስቲያን በሰፊው ታስተመረናለች። እግዚአብሔር ደግሞ ዘመኑን እኛነታችንን የምንለወጥበት፣ እንድናደርገው፣ ከራሳችንና ከእግዚአብሔር ጋር ቃል የምንገባበትና ቁርጠኛ ውሳኔ አድርገን በመንፈስ እንድንጎለምስ አዲስ ዘመንና አዲስ ዕድል ሰጥቶናል። ይህንን ዕድል ሳያገኙ ወደ አዲሱ ዘመን መሻገር ያላቻሉ ብዙዎች ናቸው። እኛ ምናልባትም “ —– በዚህች ዓመት ደግሞ ተዋት። ወደ ፊት ግን ብታፈራ ደህና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቆርጣታለህ –፡፡”(ሉቃ 13፥6-9) ተብሎልን በቅዱሳኑ ፀሎትና ምልጃ ለዘንድሮ የደረስን ሊሆን ይችላል። ስለዚህ እግዚአብሔር የኛን እጅግ የበዛ በደልና ኃጢዓት ሳይቆጥርብን ዕድሜ ለንስሃ ሰጥቶ ካሸጋገረን አዲሱ ዘመን እኛም ከአሮጌነታችን በንስሃ የምንታደስበትና ፍሬ የምናፈራበት ጊዜ መሆን አለበት።
አሮጌው ዓመት አልፎ አዲስ እየተተካ የክረምት፣ የጭቃ፣ የዝናብ፣ የብርድና የጭለማ ጊዜ አልፎ የብርሃን ጌዜ እየመጣ ሁሌም እየተደሰተን ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላ ዘመን በእድሜያችን ቁጥር ልክ ተሸጋግረናል። በጨዋታችንና በትውስታችን ያሳለፍነውን ጊዜ በዓይነ ህሊናችን እያየን አቤት ጊዜው (ዘመኑ) እንዴት ይሮጣል እንላለን። ነገር ግን ጊዜ ወይም ዘመን በትክክል ይሮጣል ወይ? ጊዜስ ምንድነው? ተፈጥሮውስ እንዴት ነው? አዎ ጊዜ ተፈጥሮው ረቂቅ የሆነ አሃዝ(ቁጥር) ነው። ስለዚህ ለጊዜ ገጽና ህላዌ ሰጥቶ የእንቅስቃሴ ባህርይ እንዳለው፣ እንደሚሮጥ አድርጎ ማሰብ ልክ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ጊዜ ተፈጥሮው ረቂቅ የሆነ አሃዝ(ቁጥር) ስለሆነ።
የሰው ሕይወት ጊዜ በተባለው አሃዝ ሲመጠን ልደት፣ ዕድገት፣ ብልየት(እርጅና) እና ሞት የተባሉ ክፍሎች ሲኖሩት እነዚህም የሕይወት አውራ ጎዳና ናቸው። ነገር ግን ዘመን ሲለዋወጥ የገዛ ባህርዩን ለቆ አይሄድም። ይህ ማላት ጊዜ ወይም ዘመን ለውጥ የሌለው ለውጥ ያካሄዳል፤ መለዋወጥ እያለ የለም።
ስለዚህ ዘመን የሚያረጅ፥ አርጅቶም የሚታደስ አይደለም። እንግዲህ በተፈጥሮው ጊዜ ዑድቱን ሳያዛንፍ አሃዝ ብቻ እይጨመረ ይኖራል። ስለዚህ ራሱን በማይለውጥ ጊዜ ውስጥ የሚለዋወጥ የሕይወት አውራ ጎዳና ያለንና ተለዋጭ በሆነ ዓለም ውስጥ ያለን እኛ ሰዎች በተለይ በክርስቲያኖች ላይ የሕይወት ለውጥ ሊታይብን ይገባል። አብዛኛዎቻችን መለወጥ በሌለው የጊዜ ዑደት ውስጥ ሆነን፤ ነገር ግን ስለ ጊዜ መለወጥ አብዝተን የምንጨነቅ፤ ስለራሳችን መለወጥ የረሳን ነን። አንዳንዶቻችንም የሰውን ሕይወት በጊዜ ውስጥ የሚለውጠው በየዘመን መለወጫው በምንገዛው አዲስ ልብስ፣ ቤት ወይም ሌላ ቁስ ወይም በምናዘጋጀው የድግስ ዓይነት ወይም በምንገዛው ጌጣ ጌጥ ወይም በሚኖረን የዚህ ዓለም ስኬት ይመስለናል። እነዚህ ሁሉ ለምድራዊ ሕይወታችን አስፈላጊ ቢሆኑም ነገር ግን እግዚአብሔር ከኛ የሚፈልገው መለወጥ ቁሳዊ ለውጥ አይደለም፤ ይልቁንም በምንገዛው አዲስ ልብና አዲስ አዕምሮ እንጂ። ይህ ደግሞ የሚሆነው ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ነው። “በትእዛዜም ይሄዱ ዘንድ ፍርዴንም ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ፥ በውስጣቸውም አዲስ መንፈስ እሰጣለሁ፥ ከሥጋቸውም ውስጥ የድንጋዩን ልብ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።”(ሕዝ 11፥19-20) እንዳለ።
አዲስ ዘመን ሲመጣ ዘመኑ ካለፈው ዘመን የተለየና እንደ ስያሜው አዲስ እንዲሆንልን ከፈለግን በሚመጣው ዘመን ውስጥ ራሳችንን አዲስ አድርገን ስንገኝ ነው። እኛ እስካልተለወጥን ድረስ ዘመኑ አሃዝ ከመጨመሩ በስተቀር ያው እንዳለፈው ሆኖ ያልፋል፥ ደግሞ ይመጣል። ይህ ማለት እኛ እስካልተለወጥን ድረስ የዘመን አዲስ የለውም ማለት ነው። ሰለ አዲስ ዘመን ስናወራ ስለራሳችን አዲስነት ልናስብ ይገባናል። ስለዚህ የአዲስ ዘመንን መመጣት ስናስብ በአትኩሮት ልናስብ የሚገባን የእኛን አዲስ ሕይወት ነው። ምክንያቱም በጊዜ ዑድት ውስጥ የሚለወጥና የሚያረጅ ሰውነት ነገር ግን የሚታደስና አዲስ መሆን የሚችል ልብ አለንና ነው። ልብ የሚታደሰው ደግሞ በንስሃ ነው። ከዘመን ወደ ሌላ ዘመን ስንሸጋገር ሸክማችን በንስሃ አቅልለን ሴኬማዊ ባህሪያችንን ቀብረን አዲስ ሕይወት ይዘን አዲሱን ዘመን ልንቀበለው ይገባል። ከአምና ዘንድሮ ለውጥ ለማምጣት ዝግጅትና ውሳኔ ሲኖረን ዘመኑ አዲስ ይሆንልናል፤ አለበለዚያ ግን ያው አሮጌ ነው።
ለመለወጥና አዲስ ለመሆን ዝግጅትና ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ራስን ለካህን ለማሳየት፥ ንስሃ ገብቶ ክቡር ሥጋውንና ቅዱስ ደሙን ለመቀበል፣ የተጣላነውን ለመታረቅ፣ ከሰውም ከእግዚአብሔርም የወሰድነውን ለመመለስ፣ የያዝነውን ቂም ለመርሳት፣ የበደልነውን ለመካስ፣ የሰውን ልጅ ሁሉ ያለ ልዩነት ለመውደድ፣ ሐሰት ላለመናገር፣ ቤተክርስቲያንን በትጋት ለማገልገልና በአጠቃላይ ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን ከሥጋ ሥራዎች ተለይተን የመንፈስ ፍሬ ይዘን ስንገኝ እኛም እንታደሳለን ዘመኑም አዲስ ሊባል ይችላል።
”የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።”(በገላ 5፥19-22)
በተለይ ከኛ ከክርስቲያኖች በተሰማራንባቸው ሥራዎች ሁሉ፤ ከሁሉ የተሻልን ዓርያነትና ምሳሌነት ያለን መሆን ይጠበቅብናል። በአጠቃላይ ንስሃ ገብተን ዘወትር በፀሎትና በፆም፣ በስግደትና በምጽዋት ተግተን አዲሱን ዓመት አካሄዳችንን ከእግዚአብሔር ጋር አድርገን በአዲስ ሕይወት እንኖር ዘንድ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። ሀገራችንን ኢትዮጵያነና ተዋሕዶ ሐይማኖታችንን እግዚአብሔር አምላካችን ይጠብቅልን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!