ጾመ ፍልሰታ

ፍልሰታ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ፍልሰታ ማለት ምን ማለት ነው?

ፍልሰታ የሚለው ቃል የተገኘው ፈለሰ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን በጥሬ ትርጉሙ መለየት፣ማረግ፣ከመቃብር ከምድር ወደላይ መውጣት የሚለውን ትርጉም ይይዛል። በእዚህ መሠረትም ጾመ ፍልሰታ የእመቤታችን ድንግል ማርያምን የሥጋዋ ከመቃብር መነሣት፣ ከሞታን ተለይቶ ማረግን ያመለክታል። «እመቤቴ ማርያም ሆይ ምጡቅና ሩቅ ወደሚሆን የደስታ ቦታ ላረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል ከመሬት ወደሰማይ ላረገው ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል እመቤቴ ማርያም ሆይ በምሥራቃዊ ተክለ ገነት የብርሃን ድንኳኖች ወደተተከሉባት ላረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል» እንዳለ ደራሲ። ይህም የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት በኦርቶዶክሱ ዓለም ብቻ ሳይሆን በካቶሊኩ ዓለም የሚታወቅና የሚከበር ነው።

ጾም ማለት ምን ማለት ነው?

ጾም (ጦም) ማለት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ሁሉ ነገሮች መከልከል መወሰን ማለት ነው። ወይም ለሰውነት የሚያምረውን የሚያስጎመጀውን ነገር መተው ማለት ነው። ጾምና ሃይማኖት የማይቋረጥ ዘላቂና ቋሚ ዝምድና አላቸው። ሃይማኖት ካለ ጾም አለ ጾም ካለ ሃይማኖት አለ፤ ከሃይማኖት ጋር ያልተያያዘ ከምግብና ከሌላም የላም የጣመ አልሚ እና ሥጋዊ ደስታ ሊስጥ የሚችል ነገር ሁሉ መከልከል እና መወሰን ከጾም አይገባም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመጣ የረሀብ አድማ የሚባል አለ እሱ ሊሆን ወይም ጥቅም የሌለው ሌላ ምክኒያት ሊኖረው ይችላል እንጂ ከጾም አይቆጠርም።

ጾም በብሉይ ኪዳንም ከእግዚአብሔር ሕዝብ ከእስራኤልና ከአገልጋዮች ካህናት ወነቢያት ጋር በሰፊው ተግባር ላይ ውሎ ይገኛል። በሐዲስ ኪዳንም ክብርና ምስጋና ይግባውና በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የቆሮንቶስ 40 መዓልትና 40 ሌሊት ጾም (ማቴ. 4) ተጀምሮ ከሐዋርያት፣ ከሰብአ አርድእትና ሌሎችም ቅዱሳንና ጠቅላላው ክርስቲያኖች ጋር አብሮ ያለ ነው።

የብሉይ ኪዳን ነቢያት እነ ሙሴ እንደ ዳንኤል እነ ኤልያስ ወዘተ በጾም ሃይማኖታቸውን ገልጸዋል።

1/ ሙሴ ጽላን ለመቀበል ወደ እግዚአብሔር ሲቀርብ እንደጾመ «ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ ወደ ተራራውም ወጣ፤ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀን አርባ ሌሊትም ቆየ። በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ እንጀራም አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። በጽላቶቹም አሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ» (ዘጸ. 2418 3428)። ተብሎ ተጽፏል።

2/ ዳንኤል የእስራኤል መከራ እንዲያልቅ ለመለመን ወደ እግዚአብሔር በጾም እንደቀረበ «በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ። ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፥ ሥጋ ጠጅም በአፌ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም። (ዳን. 102) ተብሎ ተጽፏል።

3/ ኤልያስ የእግዚአብሔርን ካህናት እና እንደሱ ያሉ ነቢያትን ታርድና ታሳረድ ከነበረችው ኤልዛቤል ከተባለችው ሰወበላ ንግሥት በሸሸ ጊዜ እንደጾመ አንድ ጊዜ በተመገበው ምግብ በርትቶ 40 መዓልትና ሌሊት በጾም እንደቆየ «ተነሥቶም በላ ጠጣም፤ በዚያም ምግብ ኃይል እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ» (ነገ/ቀዳ. 198) ሲል ይገኛል። እነ ዕዝራን እነ ነሕምያን እነ ዳዊትን ሌሎችንም ነቢያት ሁሉ እንዳልዘረዝር ጊዜ ያጥርብኛል፤ ለሚሰማም ለአሁኑ ይህ በቂ ማስረጃ ነው። እነዚህ ሁሉ እንግዲህ ከእግዚአብሔር ጋር በሚገናኙበት ወቅት እህል ውሃ ባፋቸው አልገባም ነበር።

በኃጢአት ብዛት ምክንያት የታዘዘው የእግዚአብሔር መዓት የሚመለሰው ቁጣው የሚበርደው በጾም ሲማልዱት ነበር። «በአምላካችን ፊት ራሳችንን እናዋርድ ዘንድ፥ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛና ለልጆቻችን ለንብረታችንም ሁሉ እንለምን ዘንድ በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም አወጅሁ ስለዚህም ነገር ጾምን፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመንን፤ እርሱም ተለመነን» (ዕዝ. 821-23) እንዲል።

በሐዲስ ኪዳንም ከፍ ብሎ እንደተገለጸው ጾም ሰው ሰራሽ ሕግ ሳይሆን ጀማሪው ባለቤቱ ራሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በዚሁ መሠረት በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከተወሰኑት ሰባቱ አጸዋማት ውስጥ አንዱ ትንሽ ትልቁ በታላቅ መንፈሳዊ ስሜትና ትጋት በየዓመቱ የሚሳተፍበት በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እና ቃል ኪዳን ወደ ፈጣሪው የሚቀርብበት የሚማፀንበት ይህ የፍልሰታ ለማርያም ጾም ነው።

ፍልሰታ ጾም ለምን እንጾማለን?

በቤተ ክርስቲያናችን በእመቤታችን ዜና እረፍት እንድሚተረከው የፍልሰታ ጾም ከነሐሴ 1 እስከ 15 የሚጾም ሲሆን ምክንያቱና መነሻ መሠረቱ እንደሚከተለው ነው። እመቤታችን ያረፈችው በጥር 21 ቀን ነው። ሐዋርያትም አስከሬኗን ሊቀብሩ ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሲሔዱ አይሁድ በምቀኝነት ልጇ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል። አሁንም እርሷ ገቢረ ተአምር ልታደርግ አይደል? ብለው አስከሬኗን ተሸክመው የሚሔዱትን ሐዋርያትን በታተኗቸው። በዚህን ጊዜ መላእክት የእመቤታችንን አስከሬን ከአይሁድ ነጥቀው በገነት አኖሩት። በስምንተኛው ወር በነሐሴ ሐዋርያት ከነሐሴ 1 እስከ 14 ሁለት ሱባዔ ገብተው ለምነው ከጌታችን አስከሬኗን ስጥቷቸው በጸሎትና በምህላ ቀበሯት። በዚህ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ቶማስ የተባለው ለሐዋርያዊ አገልግሎት ወጥቶ ነበር እና መገኘት አልቻለም ነበር።

እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን ከላይ እንደተጠቀሰው በነቢያት ትንቢት እንደተነገረላት እንደ ልጇ ተነሥታ ስታርግ ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ በሕዋው ላይ አገኛት። በዚህን ጊዜ ትንሣኤዋን ሌሎች ሐዋርያት አይተው ለእርሱ የቀረበት መስሎት በረከት ቀረብኝ ሲል ተበሳጨ። ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ አሁን ደግሞ ያንችን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ እራሱን ከደመና ላይ ሊወረውር ቃጣው። በዚህን ጊዜ እመቤታችን ቶማስን አፅናናችው ከእርሱ በቀር ትንሣኤዋን ያየ አለመኖሩን ነገረችው።ለምስክርነት እንዲሆንም በቀብሯ ጊዜ የነበረውን ሰበኗን ሰጥታው አረገች።

ቶማስም ሰበኗን ደብቆ ይዞ ሐዋርያት ካሉበት ደረሰ። ሐዋርያትንም የእመቤታችን ነገር እንዴት ሆነ? አላቸው። ሐዋርያትም እመቤታችን ሱባዔ ገብተን ጌታችን አስከሬኗን ከዕፀ ሕይወት ሥር ከገነት አምጥቶ ሰጥቶን በክብር ቀበርናት አሉት። ቶማስም መልሶ ሞት በጥር፣ በነሐሴ መቃብር? እኔ አላምንም እንዲህ ያለውን ነገር አላቸው።ሐዋርያትም ቶማስ አትጠራጠር ቀድሞ ጌታችን በተገለጠ ጊዜ ትንሣኤውን ጣቶቼን በተቸነከሩ እጆችህ ካላስገባሁ ብለህ የደረሰብህን ታውቃለህ አሁንም የእመቤታችንን መቀበር አላመንክምን? አሉት። ቶማስ ግን ሐዋርያትን ይዞ ወደ መቃብሯ ሔደ። መቃብሯን ከፍተው ሲመለከቱ ሐዋርያት ደነገጡ። በዚህን ጊዜ ቶማስ አታምኑኝም ብየ ነው እንጂ እመቤታችን አርጋለች። ስታርግም በደመና ከሀገረ ስብከቴ ስመጣ ተገናኘን ለምልክቱም ይኸው የቀበራችሁበት ሰበን አላቸው። ሐዋርያትም ለበረከት ሰበኗን ተከፋፍለው ወደየሀገረ ስብከታቸው ሔዱ።

በዓመቱ ግን ሐዋርያት ተሰበሰቡ እና ቶማስ ያየው የትንሣኤሽና የዕርገትሽ ወይም የፍልሰትሽ በረከት አይቅርብን ብለው ከነሐሴ አንድ ጀምረው ሱባዔ ገቡ። ነሐሴ 16 ቀን ጌታችን ከመላእክት እና ቅዱሳን ጋር ሆኖ ሐዋርያትን ወርዶ በመካከላቸው ተገኝቶ አቁርቧቸው የእመቤታችንን ትንሣኤዋንና ባለንጀራቸው ቶማስ ያየውን እርገቷን አሳይቷቸዋል። (ውዳሴ ማርያም ትርጉም)

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮ እና ሐዋርያት መሠረት ላይ የታነፀችው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያትን ግብር ምሳሌ በማድረግ ልክ እንደ ሐዋርያት ለሐዋርያት የተገለጠ በረከት እና የእመቤታችን ረድኤት እንዲያድርብን እንጾመዋለን። በቤተ ክርስቲያናችን ሰባ የአዋጅ አጽዋማት መካከል በመሆኑም ሁሉም ምእመናን እንዲጾም ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች። ነቢዩ ዳንኤል በትንቢተ ዳንኤል ምዕ 1021 ላይ እንደተጠቀሰው በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ።ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፥ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም።እንዳለ ጾሙን ከፅሉላት ምግቦች ከሥጋ እና ወተት ውጤቶች በመጾም እና ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሔድ፣ በስግደት፣ በምፅዋት እና ሎት ይጾማል

የእግዚአብሔር ምህረት ቸርነት የእመቤታችን ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን!

አባ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ