ሆሣዕና በአርያም

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩት የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዓበይት በዓላት መካከል በዓብይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት ላይ የሚገኝው ሆሣዕና ሲሆን ትርጓሜውም መድኅኒት ማለት ሲሆን ይህንኑ በማስመልከት ቅድስት ቤተ-ክርስቲያን በደመቀ መልኩ ታከብራዋለች ይህውም ጌታችን አምላካችን መድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ከፊት የቀደሙት ከዋላ የሚከተሉት ህዝብ በተለይ አዕሩግ ሕፃናት ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው ሆሣዕና በአርያም በማለት ጌታችን እያመሰገኑ መቀበላቸው የሚታወስበት ታላቅ በዓል ነው። ማቴወስ ወንጌል 21 ፥ 1)።

 

በነብየ እግዚአብሔር ዘካርያስ አስቀድሞ በትንቢት አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ ፣አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ ፥እልል በይ ፣እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ፣ትሑትም ሆኖ በአህያ በአህያይቱም ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በማለት አስቀድሞ በትንቢት ተናግሯል፣ ጌታ ከደብረ ዘይት ወደ ኢየሩሳሌም በቀረበ ጌዜ ደቀ መዛሙርቱን ልኮ ከፊት ካለችው መንደር ገብታችሁ አህያይቱ የአህያይቱ ግልገል ውርንጫይቱ ታገኝላችሁ ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሏቸው ወድያውም ይሰጧችኋል ፣ ደቀ መዛሙርቱ ከመንደር ገብተው አህያይቱን ከውርንጫይቱ ጋር አቀረቡለት ፣ የሰላም ከተማ ተብላ የተሰየመች እየሩሳሌም በውስጧ ያሉት ሁሉ ሽማግሎች ፣ሴቶች፣ የሚጠቡ ሕጻናት ሁሉ በአንድነት ሆነው *ነብየ እግዚአብሔ ቅዱስ ዳዊት እንደተናገረው(በመዝሙር 117:26 በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው )እያሉ በታላቅ ዝማሬ አመሰገኑት ።

ኢየሩሳሌም ከተማ በገባ ግዜ ከተማዋ እጅግ ተጨነቀች አይሁድ፣ የካህናት አለቆች ከህዝቡም መካከል ይህ ማነው የሚለው የማጉረምረም ድምጽ ይሰማ ጀመር፣ ምስጋና የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ ጌታችን አምላካችን በእግዚአብሔር ስም የመጣ እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ አይሁድን እጅግ አወካቸው ፣ በአርያም በሠራዊተ መላእክት የሚመሰገነውን በባርያው መልክ በትሕትና የተገለጸውን የእርሱ መመስገን የአይሁድን ቁጣ አነደደው ፣ ህዝቡንም ዝም ለማሰኝት አይሁድ ደከሙ ነገር ግን በነብየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በትንቢቱ መዝ 8፥2 “ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ ተብሎ እንደተነገረ ለራሱ ምስጋናን አዘጋጀ ።

ኢየሩሳሌም የዘንባባና የወይራ ዝንጣፊዋን ይዛ ምንጣፉን ዘርግታ ወደእርሷ የገባውን የሰላም አምላክ የሰላም ንጉሥ እየተቀበለች ግን አላወቀችውም እርሱ ስለእኛ እራሱን ቤዛ አድርጎ ሊሰጠን የዋህ ትሁት ሆኖ ወደእነርሱ እየመጣ የገዛ ወገኖቹ አላወቁትም ትንቢተ ኢሳይያስ 1 ; 3። ሰማይ ስሚ ምድርም አድምጪ በሬም የገዚውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ እስራኤል ግን አላወቀም እንደተባለ ጌታ በተወለደ ግዜ ትንቢቱን ምሳሌውን የሚያውቁ ባላወቁ ባልተቀበሉት በዚያ በብርድ ወራት እመቤታችን የምታለብሰው ልብስ አጥታ በተቸገረች ግዜ ሙቀታቸውን የገበሩለት እረኞቻቸውን ተከትለው የመጡ ከብቶች ላሞችና አህዮች ናቸው ። ወአስተማወቅዎ እስትንፋሰ አድግ ወላህም እንዲል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ። በኢየሩሳሌም በእናቶቻቸው ጀርባ ላይ የነበሩት አዕሩግ ሕፃናት ጌታቸውን አውቀው ምስጋናቸውን አቀረቡለት።

ጌታችን አምላከችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ወደዚህ ዓለም ሲመጣ በዋሻ በጎልና በሆሣዕና ያሳየው ትሕትና እጅግ የሚደንቅ ነው ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ የጌታችን በአህያ ጀርባ ላይ በትሕትና መቀመጡን ምስጢር እንዲህ ይግልጸዋል ፣ ፍቅር ከዘባነ ኪሩብ አውርዶ በአህያ ዠርባ ላይ እንድትቀመጥ አስገደደ፡፡ ብዙ ዓይንና ብዙ ገጽ ካላቸው ከሠራዊተ መላክእት ይልቅ በዲዳዋ አህያ ትመሰገን ዘንድ ወደደክ፡፡ በሰማይ ሠራዊት ሠረገላ ተቀምጠህ ክብርህን ማሳየት አልወደድክም፤ በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጠኅ ወደሰማይ ሠራዊት መኼድን መረጥክ እንጂ፡፡ በአርያም እሳታውያን የሚኾኑ ኪሩቤል ያመሰግኑኻል፤ በምድርም ሕፃናት ይዘምሩልኻል ፡፡ በአርያም ብርሃናውያን መላእክት በብርሃን ክንፋቸው መንገድኽን ያነጥፉልኻል፤ በምድርም ደቀ መዛሙርት ልብሳቸውን አንጥፈው መንገድኽን አስተካከሉ ፡፡ ወዮ! አርያማዊ ሲኾን ምንም ሳይንቀን ይጐበኘን ዘንድ ከአባቱ መጣ ፡፡ እርሱም በገዛ ፈቃዱ ሰው እስከ መኾን ደርሶ መጣ ፡፡ በአህያ ላይ ተጭኖም ይጐበኘን ዘንድ መጣ ፡፡ ነቢዩ ዘካርያስ የመንፈስ ቅዱስን እንዚራ ይዞ በደስታ ትንቢትን ለመናገር ይቻኰላል ፡፡ እየደረደረም የጽዮንን ልጅ ይጠራታል፡፡ በማለት አስተምሯል::

ጌታችን ይህንን ፍቅሩንና ትሕትናውን እያሳየ ወደ ቤተመቅደስ ሲገባ ግን የቤተ መቅደሱን መቆሽሽ ተመለከተ ቤተ-መቅደሱ የንግድ ቦታ ሆኖ ሲሽቀጥበት፣ ሲለወጥበት ተመለከተ ስለ ቤተ መቅደሱ ቅንዓት ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት በማለት የንግድ ገበታቸውን ገለበጠ የተገመደ ጅራፍ በላያቸው አሳረፈ ፣ ነገር ግን እርሱ በጸጋ አድሮባቸው እንዲከብሩ ወደ እነርሱ ቀረበ የሰውነታቸው ቤተ መቅደስ እጅግ ቆሽሾ ምኩራብ ቤተ መቅደሳቸው ረክሶ መስዋዕታቸው ሸቶ ከእግዚአብሔር ፀጋ ርቀው ታዩ፣ ከውሳጣዊ ሰውነታቸው ከበደል የራቀ መልካም መዐዛ ንጹሕ ልቦና ፈለገባቸው ኑ ወደእኔ ቅረቡ ከሸክማችሁ አሳርፈችኋለሁ እያለ ወደ ሁላቸው በፍቅር መጣ የወደዱ ተከተሉት አሳረፋቸው አሁንም ለሚሹት እርሱ ቅርብ ነው ። እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ ማንም ድምጼን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደእርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል ።ዮሐ ፡ራእይ 3፡20።

ታዲያ እኛ ይህን ዓቢይ በዓል የምናከብረው እንዴት ነው? በነቢያቱ ከላይ እንደተገለጠው በወንጌላቱም አንደተፈጸመው እርሱ ወደ እኛ የሚመጣበት ጊዜ መቼ ነው? ሲመጣስ ምን እናድርግ? የእግዚአብሔርን መምጫ ጊዜ ማሰብና መዘጋጀት ያለብን እንዴት ነው? ምክንያቱም በዓሉን ማክበር የሚጠቅመን እኛኑ ነው፣ ይህን በዓል ስናከብር ሰላምንና ፍቅርን የእርሱን የክብር አመጣጥ እያሰብን ሊሆን ይገባል ለጌታ የማያስፈልግ ፍጥረት የለም ይልቁንም የክብር ዘውድ አድርጎ በመልኩ የፈጠረው ሰው ያስፈልገዋል።ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ የተፈጠረ ማንም የለም። እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ዓላማና ዕቅድ የተፈጠርን እንደመሆናችን መጠን እግዚአብሔር የሚከብርበትን ሥራ ልንሠራ ይገባል። አህያ በሰው ሰውኛ ስትታይ የንቀትና የውርደት ሊመስል ይችላል።

የአህያ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ስንመለከት ግን በዓለም በሥጋዊ ገንዘብ መንፈሳዊ ዓይኑ ታውሮ እግዚአብሔር ያልረገማቸውን እስራኤላውያንን ሊራገም ሲሄድ እስራኤላውያንን እንዳይራገም ለመንገር ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከው መልአክ በሚሄድበት መንገድ ላይ ቆሞ ሳለ ከበለዓም ይልቅ ያየችው የበለዓም አህያ ነበረች፣ ኦሪት ዘኁልቅ 22፡23 በሆሣዕና ዕለት ከሌሎች እንሰሳት ይልቅ ጌታን በክብር የተሽከመች አህያ ናት ። አህያ ከዛ በፊት ለእኛ እህል ተሸክማ ስትሄድ ሒጂ ተብላ ትደበደብ ነበር ነገር ግን የሆሣዕና ዕለት እንኳን በዱላ ልትደበደብ ቀርቶ ሰዎች በእርሷ ላይ ለተቀመጠው ጌታ ሲሉ ልብሳቸውን ሁሉ እያነጠፉላት በምንጣፍ ላይ ተራምዳለች።

ስለዚህ ክርስቶስ በአህያይቱ ላይ እንዲቀመጥባት ልብስ እንደጎዘጎዙላት ሁሉ እኛም ጌታ በፀጋውና በረድኤቱ እንዲያድርብን ልባችንን ከኃጥያትና ከተንኮል አንጽተን ፍቅርንና ትሕትናን ልንጐዘጉዝ ይገባል። ጌታ በእኛ ላይ በፀጋው ሲያድር በእርሱና በቅዱሳኑ ዘንድ ያለን ክብርና ፀጋ ታላቅ ነው ። በነገር ሁሉ መከናወን ይሆንልናል። ክርስቶስን በመሽከሟ የአህያይቱ ታሪክ እንደተወለጠ በክርስቶስ ማደሪያነታችን ያለፈው ታሪካችን ይለወጣል ። ለዚህም የሰውነታችንን ቤተ መቅደስ በንስሐ በማንጻትና በመቀደስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን በመቀበል የእርሱ ማደሪያ ለመሆን መፋጠን ይኖርብናል ። እንግዲህ በዕለተ ሆሣዕና ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ህዝቡ ሁሉ በደስታ በዝማሬ እንደተቀበሉት እኛም ሐሤት አድርገን ሆሣዕና እምርት እንተ አቡነ ዳዊት በማለት እናመሰግናዋለን።


ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር

አንዳርጋቸው ስዮም
2010ዓ፡ም