የሰንበት ትምህርት ቤት

እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ በአርያውና በአምሳሉ ከፈጠረ በኋላ ሰው ከፈጣሪው ጋር በጥብቅ እንዲናገናኝ ልዩ ልዩ የአገልግሎት መንገዶችን አዘጋጀ። እያንዳንዱ በተሰጠው መክሊት ያተርፍና በጸጋው ያገለግል ዘንድ በመጀመርያ ዕድሜው በፈቀደለት ሁሉ መማርና ማገልገል ይኖርበታል። እግዚአብሔር አምላክ መመለክ በአለበት አግባብ ለማምለክ እምነት ያስፈልጋል፤ ከእምነት እንዳንወጣ ደግሞ ስለምናምነው ነገር በቂ ዕውቀት ሊኖረን ይገባል፤ እምነትን፣ ተስፋና ፍቅርን ሰንቆ እስከመጨረሻ ድረስ ለመጽናት መንፈሳዊ ዕውቀት መሠረታዊ ነው።

“ህዝቤ ዕውቀት በማጣት ጠፍቷል” (ሆሴ 4፥6) የተባለው በእኛ ላይ እንዳይፈጸም ዕድሜያችን በሚፈቅድልን ሁሉ ሃይማኖታዊ ዕውቀትን እንድንማር ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳን ጸሎት በእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ ሰንበት ት/ቤትን አቋቋመች። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ልጆቿ ጽድቅን ይማሩ ዘንድ በሰንበት ት/ቤት አሰባስባ ቃለ እግዚአብሔርን አውቀው፣ ባሕርየ እግዚአብሔርን ተረድተው እንዲያመልኩ፣ ሕጉን ጠብቀው፣ በሃይማኖት፣ በምግባርና በትሩፋት ፀንተው አምላካቸውን መስለው እንዲኖሩ የእርሱ የሆነችውን መንግስተ እግዚአብሔርን እንዲወርሱ በብሉይ ከአምላኳ የተቀበለችውን ሕግጋተ እግዚአብሔርን አስተምራ በሐዲስ ኪዳንም በ40 እና በ80 ቀን እያጠመቀች ለምዕመናን እንደ እድሜያቸው እና እንደ አዕምዕሮ ብስለታቸው ቃለ እግዚአብሔርን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል ታስተላልፋለች። በስብከት፣ በዝማሬ፣ በቅዳሴ፣ በስዓታት፣ በማሕሌት የቅኔውን ምሥጢር በትርጓሜ እያስተማረች ምዕመናንን በእምነት አንፃ ለመንግስተ ሰማያት እያዘጋጀች ዛሬ ላይ ደርሳለች።

ከስሙ እንደምንረዳው ሰንበት ትምህርት ቤት ማለት የጾታ ልዩነት ሳይደረግ የቤተ ክርስቲያን ተተኪ ትውልድ ወይም መንፈሳዊ ወጣቶች በዕለተ ሰንበት፣ በዓበይት በዓላትና አመቺ በሆነ ጊዜ ሁሉ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እየተገኙ የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ቅኖና፣ሥርዓትና ትውፊት የሚማሩበት እና በእምነት፣በምግባርና በሃይማኖት ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን የሚያጠነክሩበት ትምህርት ቤት ነው:: መንፈሳዊ ወጣቶች የሚባሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓትና ትውፊት በዕድሜ ክልላቸው የሚማሩ የቤተ ክርስቲያን አባላት ናቸው (ቃለ ዓዋዲ ፲፱፻፺፩)።

በመጽሐፍ ቅዱስ ሰንበት ት/ቤት ተብሎ የተፃፈ ቀጥተኛ የሆነ ስም ባይገኝም ዛሬ ላይ በሰንበት ት/ቤት የሚተገበረው መንፈሳዊ አገልግሎት ማለትም ልጆችን በቤተ እግዚአብሔር ማስተማር በብሉይ ኪዳን ዘመንም ይፈጸም እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል። የሰንበት ት/ቤት ፅንሰ ሀሳብም ከዚያ የመነጨ ነው። “እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ እነርሱንም ለምልክት በእጃችሁ ላይ እሠሯቸው በዐይኖቻችሁም መካከል እንደ ክታብ ይሁን ልጆቻችሁንም አስተምሯቸው በቤትህም ስትቀመጥ በመንገድም ስትሄድ ስትተኛም ስትነሣም አጫውቱአቸው” (ዘዳ 11÷18-21 )በማለት እስራኤላውያን ልጆቻቸውን ሕግጋተ እግዚአብሔር እንዲያስተምሯቸው ታዘዋል፡፡ እነርሱም ይህን አምላካዊ ቃል ተግባራዊ ለማድረግ ልጆቻቸውን ወደ ቤተ እግዚአብሔር እየላኩ እና በቤታቸው ውስጥም ተግተው ያስተምሩ ነበር።

በሐዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌ ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው ቁም ነገሮች መካከል ሕፃናት ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጡ ዘንድ ነበር። ልበ ንጹሐንን በሕጻናት መስሎ ያስተማረበት አንቀጽም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጽፎ ይገኛል። ይህም በዘመናችን ላለችው ቤተ ክርስቲያን የሕፃናት፣ የወጣቶች እና የጎልማሶች ማስተማሪያ ለሆነችው ሰንበት ትምህርት ቤት መነሻ የሆነ እና መሠረቱም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን ያረጋግጥልናል (ማቴ 18፥3፣ 21፥16፣ ማር 9፥37)፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤት አመሠራረት በኢትዮጵያ ስንመለከት ዘመናዊ ትምህርት ቤት እየተስፋፋ ሲመጣ ወጣቱ ትውልድ ከአምልኮተ እግዚአብሔር እንዳይለይ፤ በተለይ ለዘመናዊ ትምህርት አስተማሪነት በመጡ እራሳቸውን ”ኢየሱሳውያን” ብለው በሚጠሩ የውጭ መምህራን ከመጡበት ዓለማዊ ትምህርት ባሻገር የኑፋቄ ትምህርት ማሰራጨታቸው፣ በተቃራኒው ደግሞ ወደ አብነት ትምህርት ቤት የሚሄደው ወጣት ቁጥር በመቀነሱ ምክንያት በ20ኛው ክፍለ ዘመን ወጣቱን ለመያዝ መንፈሳዊ መርሐ ግብሮችና የማኅበራት እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ። እነዚህ የተጀመሩ መርሐ ግብሮችና ማኅበራት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮዎቿ ሳይበረዙ ለትውልድ እንዲተላለፉ በተለይ በሕጻናት እና በወጣቶች ላይ ትኩረት ሰጥው እንዲሠሩ ትልቁን ድርሻ ወስደዋል።

በዚህም መሠረት ሰንበት ትምህርት ቤት በማቋቋም ትውልድን በኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖት የማነጽ፣ ዶግማን፣ ቀኖናን እና ትውፊትን ማስተማር ተጀመረ። በ1960 ዓ.ም ይህን የሰንበት ትምህርት ቤቶች እንቅስቃሴ ለማስተባበር እና ለማጠናከር ይቻል ዘንድ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በስብከተ ወንጌልና ማስታወቂያ መምሪያ ሥር ማእከላዊ ጽ/ቤት በዋናነት ተቋቁሞ ስያሜውም የሰንበት ት/ቤት መምህራን ጽሕፈት ቤት ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ይህ አካሄድ እያደገ ሲመጣ በ1965 ዓ.ም ራሱን ችሎ ወደ ወጣቶች ጉዳይ መምሪያነት እንዲያድግ ተደርጓል፡፡ ዛሬ ላይ የሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ መምርያ የሚል ሰንበት ትምህርት ቤቶችን የሚያደራጅና የሚመራ በተቋም ደረጃ ትልቅ መምርያ ተቋቁሞ አገልግሎቱን እየፈጸመ ይገኛል።

የሰንበት ት/ቤት ጥቅሙና አስፈላጊነቱ የጎላ መሆኑ በተግባር በመረጋገጡ በ1970 ዓ.ም “ሰንበት ት/ቤት” በሚል ስያሜ ሕጋዊ ሆኖ እንዲቀጥል እና በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሰንበት ት/ቤቶች እንዲቋቋሙ የተቋቋሙትም እንዲጠናከሩ ተሻሽሎ በወጣው ቃለ ዓዋዲ እንዲጸድቅ ተደርጓል፡፡ የሰ/ት/ቤት አገልግሎትን የበለጠ ለማጠናከር ሰንበት ት/ቤቶች የሚመሩበትን መተዳደሪያ ደንብ አጽድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ያደረገ ሲሆን አሁን አስካለንበት ዘመን ድረስ ሰንበት ት/ቤቶች ይህን መመሪያ ከዋናው ቃለ ዐዋዲ ጋር በማስተባበር እየተመሩበትና ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡

ይህን ወጣቱን ትውልድ በዘመናዊነት ተፅዕኖ ውስጥ ወድቆ ከመንፈሳዊ ሕይወት እንዳይወጣ ልዩ ክትትል በማድረጉ ረገድ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን እኅት አብያተ ክርስቲያናትም ሰንበት ትምህርት ቤትን አቋቁመው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ብዙ ዓመታትን አስቆጥረዋል። በተለይ ግብፅና ሕንድ በተደራጀ መልኩ እየሠሩበት ይገኛሉ።

የሰንበት ትምህርት ቤት የተቋቋመበት ዋና ዓላማ

የሰንበት ትምህርት ቤት ዓላማ፦

  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዶግማ፣ ቅኖና፣ እምነትና ሥርዓት ተጠብቆ ሳይበረዝ ሳይከለስ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ
  • ማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታይ የሆነ ምእመን የሃይማኖቱን ሥርዓት በውል እንዲያውቅና እንዲረዳ ማድረግ
  • ወጣቶች የቤተ ክርስቲያንን ሕግና ሥርዓት ተምረው ለሀገርና ለወገን ጠቃሚ፣ መልካምና በሥነ ምግባር የታነፁ ዜጎች እንዲሆኑ ማድረግ
  • በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ (መክ. ፲፪፡፩) የሚለውን የአምላክ ተእዛዝ ወጣቶች እንዲፈጽሙ ማስቻል
እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትን አበይት ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ ጠንካራ ሰንበት ትምህርት ቤት ያስፈልጋል። ወጣቶችን በሰንበት ትምህርት ቤት ለማሳደግ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት በእጅጉ አስፈላጊ ነው። አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጴጥሮስ ከሰጠው መመርያና ትዕዛዝ መካከል ሕፃናትንና ወጣቶችን በሃይማኖት እያስተማረ ለመንግስተ ሰማያት ማብቃት እንደነበር ቅዱስ ዮሐንስ በመጽሐፍ ቅዱስ ጽፎልናል (ዮሐ 21፥15)። የአምላካችንን ትዕዛዝም ትውልድ ሁሉ ይፈጽመው ዘንድ ሕፃናትን እና ወጣቶችን አስተባብሮ ማስተማር የሚችል ሰንበት ትምህርት ቤት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም።
 
ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቱን ትውልድ በአምልኮተ እግዚአብሔርን አፅንቶ በሃይማኖትና በምግባር ከማኖርም ባሻገር ለቤተ ክርስቲያን ቀናኢ የሆኑ አገልጋዮችን አፍርቷል፤ በማፍራት ላይም ይገኛል። ሰንበት ትምህርት ቤት በዕለተ ሰንበትና አበይት በዓላት ወቅት ያሬዳዊ መዝሙራትን ከማቅረብም በላይ ዲያቆናትን፣ ቀሳውስትን፣ ቆሞሳትን፣ ጳጳሳትን፣ መምህራነ ወንጌልን፣ ሰባኪያንን እና በልዩ ልዩ አገልግሎት ላይ የሚፋጠኑ ዘመኑን የዋጁ አገልጋዮችን ለቤተ ክርስቲያናችን አበርክቷል። ይህ አገልግሎት እንዳይቋረጥና ቤተ ክርስቲያን ለትውልድ ሁሉ ከነሙሉ ክብሯ ትተላለፍ ዘንድ በያለንበት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሰንበት ትምህርት ቤትን ማጠናከር የዘወትር ተግባር ሊሆን ይገባል። በተለይ በዚህ በውጭው ዓለም ልጆቻችንን የምዕራቡ ባህልና እምነትየለሽ ዘመናዊነት እንዳያጠቃቸው በሰንበት ትምህርት ቤት አስመዝግበን ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ እንዲያውቋት ማድረግና በሃይማኖትና በምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ ማስቻል የወላጅ ሃይማኖታዊ ግዴታ መሆን አለበት። ምክንያቱም ልጆቻችን ኦርቶዶክሳዊት እምነትን፣ ዶግማን፣ ሥርዓት እና ትውፊትን በሰንበት ት/ቤት ካልተማሩ ሃይማኖታችንን ጠብቀውና አስጠብቀው ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ አይቻላቸውም፡፡
 
በአጠቃላይ ሰንበት ትምህርት ቤት ትውልድን ለመቅረጽ የሚሰጠው ጠቀሜታ ታላቅ ስለሆነ ወጣቶችና ሕፃናት በሰንበት ትምህርት ቤት የሚሰጠውን መደበኛ ትምህርት መከታተል እንዲችሉ ማድረግና በማነኛውም ጊዜና ቦታ አርያና ምሳሌ ሁነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት አፅንተው ይይዙ ዘንድ ከሁልጊዜውም በተለየ መልኩ የሁላችንም ድጋፍ እንደሚያስፈልግ መረዳትና በመተግበርም እግዚአብሔር አምላክ የሰጠንን ሃይማኖታዊ ተልእኮ መፈጸም ይጠበቅብናል።