መግቢያ

በኖርዌይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የቅዱስ ገብርኤል እና የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርሰቲያን በአቡነ ኤልያስ መልካም ፍቃድ እና የቡራኬ ሥርዓት በ፲፱፻፹፯ ዓ.ም. ወይንም እ.ኤ.አ. በ1995 G.C. ተመሠረተች። ቤተ ክርስቲያኒቱም ስትመሠረት በኦስሎ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ዲያቆናት ብቻ ሲኖራት አገልጋይ ካህን ግን አልነበራትም። ስለዚህም ለአገልግሎት ካህናትን ከኖርዌይ አቅራቢያ ከሚገኙ አገራት በተለይም ከስዊድን እያስመጣች በስድስት ሳምንታት አንድ ጊዜ ቅዳሴ ታስቀድስ ነበረ። ከዕለት ዕለት ግን የምእመናኑ መበራከትና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች ማለትም እንደ ቊርባን፣ ሰርግ፣ ክርስት፣ ጸሎተ ፍታትና ሌሎችም እያስፈለጉ በመምጣታቸው በምእመናኑ ትግል እና በእግዚአብሔር ፈቃድ በአቡነ ኤልያስ አማካይነት የራሷ የሆነ አንድ ቄስ ለማግኘት የቻለች ሲሆን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገች በመምጣትዋ አሁን ከአምስት የሚበልጡ ካህናትና ዲያቆናት አገልግሎት እየሰጡባት ትገኛለች። የምእመናኑም ብዛት እንዲሁ እያደገ የመጣ ሲሆን በየሳምንቱ እሑድ ከ፬፻ (400) በላይ ምእመናን ቅዳሴና የተለያዩ አገልግሎቶች ያገኙባታል።

 

መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች

ይህች ቤተ ክርስቲያን በዚህ ጭንቀት በበዛበት ምድር ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው ዕረፍት እንዲያገኙና ከካህናት የምክር አገልግሎት እንዲሰጣቸው በዕለተ ሰንበት ክፍት በመሆን አገልግሎት የምትሰጥ ቤተ ክርስቲያን ናት። ዘወትር እሑድ የቅዳሴ ሥርዓት የሚከናውን ሲሆን ወር በገባ በ፲፱ (19) የቅዱስ ገብርኤል እና በ፳፬ (24) የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ወርኃዊ በዓላትን ከ፲፯ (17:00) ሰዓት ጀምሮ በጸሎት የምትዘክር ሲሆን ታኅሣሥ እና ሐምሌ ፲፱ (19) የቅዱስ ገብርኤልን እንዲሁም ታኅሣሥ ፳፬ (24) እና ግንቦት ፲፪ (12) የአባታችን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ በዓላትን ማኅሌት በመቆምና ቅዳሴ በማድረስ እንዲሁም ንግሥ በማንገሥ የምታከብር ሲሆን፤ ዓበይት በዓላትን ደግሞ ማኅሌት በመቆምና ቅዳሴ በማድረስ አገልግሎት ትሰጣለች። ከዚህ በተጨማሪም በወርኃ ጽጌ፣ በነቢያት ጾም፣ በዓቢይ ጾም እና በፍልሰታ ጾም ወቅት የጸሎት አገልግሎት ትሰጣለች።
ከዚህ በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያናችን ሕፃናት ክርስትና ይነሣሉ፣ ሥርዓተ ተክሊል ይከናወናል እንዲሁም የፍትሐት ጸሎት ይፈጸምባታል።በቤተ ክርስቲያናችን ሕፃናት የሃይማኖት ትምህርት፣ መዝሙር፣ መጽሐፍ ቅዱስና የቋንቋ ትምህርት ይማራሉ።
ችግር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንም ምዕመናንን በማስተባበር ትረዳለች።