ጌታችን ከተጠመቀ በኋላ የአይሁድ ፋሲካ ለሦስት ጊዜ ተከብሯል፡፡ የመጀመሪያው ፋሲካ ጌታችን ቤተ መቅደሱን ያጸዳበትና በቤተ መቅደስ ሲሸጡ ሲለውጡ የነበሩትን ያስወጣበት ሲሆን በመጨረሻው ፋሲካም ሰሞን እንዲሁ ለሁለተኛ ጊዜ ቤተ መቅደሱን አንጽቶ ከፋሲካው ማግስት ተሰቅሏል፡፡ በሁለቱ ፋሲካዎች መካከል በነበረው ፋሲካ ደግሞ ጌታችን ወደ ቤተ ሳይዳ መጣ፡፡
ቤተ ሳይዳ የመጠመቂያው ስፍራ ስም ሲሆን ከአጠገቡ ደግሞ በጎች በር ነበር፡፡ (የበጎች በር በአሁኑ ሰዓት የቅዱስ እስጢፋኖስ (ሊወግሩት ያወጡበት) በር እና የአንበሳ በር ተብሎም ይጠራል) እንደሚታወቀው ዘመነ ኦሪት በግ መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርብበት ነበር፡፡ ስለዚህ በዚያ በር መሥዋዕት ሆነው የሚቀርቡ በጎች የሚገቡበት ነበር፡፡ በጎቹ ነውር እንደሌለባቸው ማለትም ቀንዳቸው እንዳልከረረ ፣ ጥፍራቸው እንዳልዘረዘረ፣ ጠጉራቸው እንዳላረረ እያገላበጡ የሚጠኑበት ፣ የአንድ ዓመት ተባዕት/ወንድ/ መሆናቸው የሚታይበት ሥፍራ ነው፡፡ ይህን መስፈርት አሟልተው ያለፉ በጎች ለመሥዋዕትነት ሲቀርቡ ለዚህ ብቁ ያልሆኑትን ግን ለይተው ፣ በአለንጋ እየገረፉ ያስወጡአቸዋል፡፡
በቤተ ሳይዳ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያዪቱ ወርዶ ውኃውን አንዳንድ ጊዜ ያናውጥ ነበር፡፡ ይህ መልአክ ‹በሰው ቁስል ላይ የተሾመ ፣ በበሽታም ላይ ሁሉ የተሾመ› የስሙም ትርጓሜ ‹እግዚአብሔር ፈዋሽ ነው› ማለት የሆነ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነበር፡፡መልአኩ ውኆችን ለመቀደስ ፣ ጸሎትን ከሰው ወደ ፈጣሪ ለማድረስ ወደ ውኃው ይወርድ ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ ውኃ በራሱ ማዳን ባይቻለውም ቅዱሳን መላእክት የነኩት እንደሆነ በረከትና ፈውስ እንደሚሠጥ የሚያስረዳን ነው፡፡ ውኃው ከተነዋወጠ በኋላ ግን መዳን የሚቻለው መጀመሪያ መግባት ሲቻል ነበር፡፡ በዚህ የጠበል ሥፍራ በነበሩ አምስት መመላለሻዎች ‹በሽተኞች ፣ አንካሶች ፣ ዕውሮችና እግራቸው የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር፡፡በተለይ ደግሞ አንካሶች ፣ ዕውሮችና እግራቸው የሰለለ ሰዎች በቁጥር የሚበዙት ከሌላው በሽተኛ በተለየ እነሱ የውኃውን መንቀሳቀስ አይተው ለመግባት እንዳይችሉ ወይ ዓይናቸው ማየት አይችልም ፤ ያም ባይሆን መንቀሳቀስ ያቅታቸዋል፡፡ ገብተውም እንኳን ቢሆን ድንገትከእነሱ ቀድሞ የገባ ሰው ካለ እነሱ ስለማይፈወሱ ከውኃው መልሶ የሚያወጣቸውም ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡ አለዚያ ገብተውም አውጪ አጥተው ሊቸገሩ ይችላሉ፡፡ ምናልባትም በእንዲህ ዓይነት ችግር ለባሰ ነገር የተዳረገም ሊኖር ይችላል፡፡
ከእነሱ ቀድሞ የሚድነው እንግዲህ ሁለት ዓይነት ሰው ነው፡፡ አንደኛው በሽታው ለመንቀሳቀስ የማያግደው ሆኖ እያለ የእነሱ ይብሳል ብሎ ሳያዝን የሚገባ ነው፡፡ መቼም ሰው እንኳን ቀድሞ የገባ ሰው ብቻ በሚድንበት ሥፍራ ቀርቶ ፤ በማንኛውም ሰዓት ቢገባ በሚዳንበት የጠበል ሥፍራ ‹ከእኔ በሽታ የእገሌ ይብሳል ፤ እስቲ ቅድሚያ ልስጠው› ሲል ብዙ ጊዜ አይታይም፡፡ ስለዚህ እነዚህን ደካሞች ቀድሞ የሚገባ በሽተኛ ብዙ ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ወደ መጠመቂያው ሊወረውሩት የሚጠባበቁ ዘመዶች ያሉት ፣ አለዚያም ዘመድ የሚያፈራበት ገንዘብ ያለው በሽተኛ ደግሞ ሌላው ቀድሞ ወደ መጠመቂያው የሚገባ ነው፡፡
በዚህ ሥፍራ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል የተኛ በሽተኛ (በግእዙ መጻጉዕ) ነበር፡፡ ግሪካውያን የዚህን ሰው ስም ኢያኢሮስ ይሉታል። እንግዲህ ሠላሳ ስምንት ዓመት ማለት የጉልምስና ዕድሜ ነው፡፡መጻጉዕ የመጣው በዐሥር ዓመቱ ነው እንኳን ብንል አሁን አርባ ስምንት ዓመቱ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጌታችን በኋላ ‹የሚብስ እንዳይደርስብህ ደግመህ ኃጢአትን አትሥራ › ብሎ ስለተናገረ ከመታመሙ በፊት ለዚህ ጽኑ ደዌ የሚዳርግ ኃጢአት ለመሥራት የሚችልበት ዕድሜ ላይ ደርሶአልማለት ነው፡፡ መቼም ክፉ ደግ በማያውቅበት ሕጻንነቱ በድሎ ‹‹የልጅነቱ መተላለፍ ታስቦበት›› ታመመ ብሎ መናገር ይከብዳል፡፡ ብቻ ይህ ሰው የአንድ ጎልማሳ ዕድሜ ያህል በአልጋ ላይ ሆኖ በቤተ ሳይዳ ተኝቶአል፡፡ ጠበል ሊጠመቅ ሲጠባበቅ በጸጉሩ ሽበት ፣ በግንባሩ ምልክት አውጥቶአል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ግርግም ውስጥ ሲወለድም ይህ በሽተኛ በዚሁ መጠመቂያ ስፍራ ነበረ:: ድንግል ማርያም የወለደችውን ሕጻን በበረት ውስጥ ስታስተኛው ይህ በሽተኛ አልጋው ላይ ከተኛ ስድስት ዓመት ደፍኖ ነበር::
ከሁሉ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ሰው አልጋው ላይ ሆኖ እጅግ ብዙ ሰዎች ሲፈወሱ መመልከቱ ነው፡፡ ከእሱ በኋላ መጥተው ከእሱ በፊት ድነው የሚሔዱ ሰዎችን ማየት እንዴት ይከብደው ይሆን? እንደሱ ብዙ ዘመን የቆዩት ሲድኑ ሲያይ ተስፋው ሊለመልም ይችላል፡፡ በመጡ በአጭር ጊዜ ዘመደ ብዙ በመሆናቸው ብቻ የሚድኑ ሰዎችን ሲያይ ግን ልቡ በኀዘን ይሰበራል፡፡ ዓመቱ በረዘመ ቁጥር ተስፋ ቆርጦ ቤተ ሳይዳን ቤቴ ብሎ ከመኖር በስተቀር ምንም የሚታየው ነገር አይኖርም፡፡ እግዚአብሔርን በመከራው ውስጥ ተስፋ እያደረገ ይጽናናል አንዳንል ደግሞ እንደ ጻድቁ ኢዮብ ወይም እንደ በሽተኛው አልዓዛር ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት የነበረው ቢሆን ኖሮ መቼ ለዚህ በሽታ የሚዳርገው ኃጢአት ይሠራ ነበር? ስለዚህ በቃለ እግዚአብሔር ይጽናናል ማለትም ያስቸግራል፡፡ያም ሆነ ይህ ይህ ሰው እጅግ ተሰቃይቶ ነበር፡፡
ጌታችን የዚህን ሰው ችግር ብቻ ሳይሆን ብዙ ዘመን እንደዚህ እንደነበረ ያወቀው ማንም ሳይነግረው ነበር፡፡ በሽታውን ከነመንሥኤው አስቀድሞ ያውቃልና ወደዚህ የብዙ ዓመታት በሽተኛ መጣና ‹ልትድን ትወዳለህን?› አለው፡፡ ጌታችን የሚፈልገው ይህንን ሰው መፈወስ እንጂ የራሱን ማንነት ማሳየት ስላልነበረ ‹ላድንህ ትወዳለህን?› አላለውም፡፡ በዚያ ላይ ይህ ሰው የጌታን ማንነት አያውቅም፡፡ ጌታችን ‹ስታምኑብኝ ብቻ ነው የምፈውሳችሁ›የሚል አምላክ አይደለም ፣ ለሁሉ ፀሐይን የሚያወጣ ፣ ለሁሉ ዝናምን የሚያዘንም አምላክ ይህንን ሰውም ለመፈወስ እስኪያምነውም አልጠበቀም፡፡
ይህ በሽተኛ‹ልትድን ትወዳለህን?› ሲባል የሠጠው መልስ እጅግ የሚያስገርም ነው፡፡ እንደሚታወቀው በሽታ አመል ያጠፋል፡፡ በሽታው በቆየ ቁጥር ደግሞ መራር ያደርጋል፡፡ ሰዎች በበሽታ ሲፈተኑ በሰው በፈጣሪም ላይ ብዙ የምሬት ንግግር ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ ጌታችን ‹ልትድን ትወዳለህን?›ብሎ ሲጠይቀው ‹ታዲያ መዳን ባልፈልግ ጠበል ቦታ ምን አስቀመጠኝ? እያየኸኝ አይደል… › ወዘተ ብሎ ብዙ ያለፈ ንግግር ሊናገር ይችል ነበር፡፡ ይህ ሰው ግን ምንም የምሬት እና የቁጣ ቃል አልተናገረም፡፡ ጌታችንም ሲያናግረው በጨዋ ሰው ደንብ ‹ጌታ ሆይ..›ብሎ ነው የመለሰለት፡፡ በዚህ ሁኔታው ትሑት ሊባል ይችላል፡፡
ነገር ግን የመለሰው የተጠየቀውን አይደለም፡፡ ጥያቄው ‹ልትድን ትወዳለህን?› የሚል ከሆነ መልሱ ‹አዎ መዳን እወዳለሁ› አለዚያም ‹አይ አልፈልግም› ብቻ መሆን ነበረበት፡፡ እሱ ግን ‹ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት።› እንግዲህ የጌታችንን ማንነት ባይረዳውም ጌታችን በወቅቱ የሠላሳ ሁለት ዓመቱ ነበርና ‹ምናልባት ወደ መጠመቂያው ሊጨምረኝ አስቦ ይሆናል ያም ባይሆን ግን ከተከተሉት ሰዎች አንዱን አደራ ሊልልኝ ይሆናል› ብሎ አስቦ ነበር፡፡ ‹ሰው የለኝም› ብሎ የሠላሳ ስምንት ዓመታት ብሶቱን ተናገረ፡፡ ‹ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል› ብሎ እያየ የቀደሙትን ሰዎች አስታወሰ፡፡
ጌታችን ‹ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ› አለው፡፡ ባላሰበው ባልጠበቀው መንገድ ፈወሰው፡፡ ይህ ሰው ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ ሲጠባበቃት የነበረችውን የቤተ ሳይዳ ጠበል ሳያገኝ ፣ በመልአኩ መውረድ ሳይሆን በመላእክት ፈጣሪ ቃል ተፈወሰ፡፡ ገባሬ መላእክት ክርስቶስ ራሱ መጥቶ አዳነው፡፡ ይህ ሰው እግዚአብሔር በዚህች ጠበል ካልሆነ በቀር በሌላ በምንም መንገድ ያድናል ብሎ አስቦም አልሞም አያውቅም ነበር፡፡ ለመዳን የሚያስፈልገው ምንድን ነው ተብሎ ቢጠየቅ የሚመልሰው ‹ወደ ውኃው የሚጨምር ሰው እና የቤተ ሳይዳ ውኃ› ብሎ ነበር፡፡ ጌታችን መጻጉዕ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ተስፋ ያደረጋትን ጠበል ወይም ደግሞ ወደ ጠበሉ የሚጨምሩትን ሰዎች ሳይጠቀም ፈወሰው፡፡ እግዚአብሔር ያለ ጠበልም እንደሚያድን ማመን ካልቻልን እምነታችን ሙሉ አይደለም፡፡ ይህ ሰው ወደ ውኃው ገብቶ ቢድን ኖሮ‹ጌታዬ አዳነኝ› ከማለት ይልቅ ‹‹መዳን ይነሰኝ? ሠላሳ ስምንት ዓመት እኮ ነው የጠበቅኩት…›› እያለ ልፋቱን ያወራርድ ነበር እንጂ ፈጣሪውን አያመሰግንም ነበር፡፡
ጌታችን ጠበል ቦታ ያገኘውን ያለ ጠበል ፈወሰው ሲባል መቼም ጠበል መጠመቅ የማይወዱ ወይም በጠበል የማያምኑ ሰዎች ደስ ሊላቸው ይችላል፡፡‹‹እኛስ ምን አልን ጌታ እኮ ይህን በሽተኛ ጠበል ቦታ አግኝቶ እንኳን የፈወሰው ያለ ጠበል ነው›› ብለው ባቀበልናቸው በትር ሊመቱን ይፈልጉ ይሆናል፡፡ ሆኖም እዚሁ ዮሐንስ ወንጌል በዘጠነኛው ምዕራፍ ላይ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ጠበል በሌለበት ሥፍራ አግኝቶት እኛ እመት (እምነት) የምንለውን አፈር በምራቁ ለውሶ ከቀባው በኋላ ‹ሒድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ› ብሎ ልኮታል፡፡ ጠበል ምንም የማያስፈልግ ቢሆን ኖሮ ዓይነ ስውሩን ሰው ወደ ወንዝ ወርደህ ተጠመቅ ብሎ አይልከውም ነበር፡፡ ዛሬ ለታመሙ ሰዎች ጠበል ሒዱ ብለን ስንመክር ክርስትና ያልገባን ፣ ክርስቶስን የማናውቅ የሚመስለው ይኖራል፡፡ አሁን ባየነው ታሪክ ውስጥ ግን ለበሽተኛው ‹ጠበል ሔደህ ተጠመቅ› ብሎ የመከረው ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ መፈወስ የሚቻለው ክርስቶስ ጠበል ተጠመቅ ብሎ ከተናገረ ፤ የታመመን መፈወስ የማንችለው እኛ ኃጢአተኞቹ ከንፈር ከመምጠጥ ይልቅ ሔደህ ተጠመቅ ብንል ምን አጥፍተናል? ጌታችን ሲያደርግ ያየነውን ነው፡፡እኔን ምሰሉ ብሎ የለ እንዴ? (ዮሐ. 9፡7)
በእነዚህ ሁለት ታሪኮች ግን ጌታችን ሲፈልግ በጠበል ሲፈልግ ያለ ጠበል ፤ ሲሻው በምክንያት ሲሻው ያለ ምክንያት፡፡ ሲፈልግ በጠበል ሲፈልግ በህክምና ፤ ሲፈልግ በቃሉ ሲፈልግ በዝምታ ፣ ሲፈልግ በቅዱሳን መላእክቱ ሲፈልግ ያለ ቅዱሳን መላእክቱ ማዳን እንደሚቻለው እንረዳለን፡፡
ጌታችን ለመጻጉዕ ‹ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ› ብሎ ሲነግረው ወዲያውኑ ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሔደ፡፡ እዚህ ላይ አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳደረገው የበሽተኛውን እምነት እናደንቃለን፡፡ ራሱን መሸከም የማይችለው ይህ በሽተኛ ተነሣና አልጋህን ተሸከም ሲባል አልሳቀም፡፡ ‹እንዴት አድርጌ ነው ደግሞ አልጋ የምሸከመው› ብሎ አልጠየቀም፡፡ በፍጹም እምነት ተነሣና ተሸክሞ ሔደ፡፡ የሠላሳ ስምንት ዓመት ጓደኛውን ፣ ሰው ሳይኖረው አብራው ኖረችውን ፣ የተሸከመችውን ባለ ውለታው የሆነችዋን አልጋ ተሸክማት አለው – ተሸክሞ ሔደ፡፡
አንድ ሰው እንኳን ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ይቅርና ለሠላሳ ስምንት ቀናት እንኳን ቢታመም እንደተሻለው ተነሥቶ አልጋ አይሸከምም፡፡ እስከሚያገግም ድረስ በደንብ መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ራሱን ያዞረዋል ፣ ይደክመዋል፡፡ የቀረ ሕመም አያጣውም፡፡ መጻጉዕ ግን የተፈወሰው ያለ ቀሪ በሽታ (ያለ ተረፈ ደዌ) ነበር፡፡ ስለዚህ ወዲያው ተነሥቶ አልጋውን እንዲሸከም ነገረው፡፡ መምህር ኤስድሮስ እንዳሉት ያንን የብረት አልጋ ተሸክሞ እየሔደ የጌታን ጽንዐ ተአምራት አሳየ፡፡ ጌታችንም ከዛ በሽታ ያዳነው በነጻ መሆኑን በሚያሳይ ሁኔታ ያችን አንዲት ንብረቱንም ተሸክመህ ሒድ አለው፡፡
መጻጉዕ የተሸከመችህን አልጋ ተሸከም ተባለ፡፡ አግዚአብሔር የተሸከሙንን እንድንሸከም የሚፈልግ አምላክ ነው፡፡ ውለታ ሳንረሳ የተሸከሙንን ወላጆቻችንን የተሸከመችንን ቤተ ክርስቲያንን ፣ የተሸከመችንን ሀገራችንን እንድንሸከም ይፈልጋል፡፡ በአንዱ ሊቅ ደግሞ ‹ዓለም እንደዚህ ናት ፤ እናት ዓለም አልጋ መጻጉዕን እንደተሸከምኩህ ተሸከመኝ አለችው› ብለው ተቀኝተዋል፡፡ ( ዝክረ ሊቃውንት 2 )
እዚህ ላይ ጌታችን ቤተ ሳይዳ ከመጣ አይቀር ሁሉንም በሽተኛ መፈወስ ሲችል ለምን አንዱን ብቻ ፈውሶ ሔደ? ብለን ማሰባችን አይቀርም፡፡ የበለጠ የሚያሳዝነው ደግሞ ሊቃውንቱ እንደጻፉት የቤተ ሳይዳው መጠመቂያ ፈውስ ከዚያ በኋላ ብዙም አልቆየም፡፡ የመልአኩም መውረድ ቆሞአል፡፡ ከዚያ በኋላ በሰባ ዓመተ ምሕረትም ኢየሩሳሌም መቅደስዋ ፈርሶአል ተመሰቃቅላለች፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስም የዮሐንስ ወንጌልን ሲጽፍ ‹‹ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት።… ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር።… ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆንነበር።›› ብሎ በኃላፊ ኃላፊ ግሥ /past perfect tense/ ነበር፡፡
ታዲያ ጌታችን እንዲህ መሆኑን እያወቀ ምነው መጻጉዕን ብቻ ፈውሶት ሔደ? ቢባል የፈወሰው እሱን ብቻ አይደለም፡፡እሱን በሥጋ ቢፈውሰውም ተአምራቱን አይተው በማመናቸው በነፍሳቸው የተፈወሱ ይበዛሉ፡፡ ‹ሕሙማነ ሥጋን በተአምራት ሕሙማነ ነፍስን በትምህርት እየፈወሰ› እንዲሉ አበው በዚያ ሥፍራ በሥጋ ታመው በነፍሳቸው አምነው የዳኑ ብዙዎች ናቸው፡፡ የጌታችንና የእርሱ አካል የሆነች የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ሥራዋ ነፍስን መፈወስ እንጂ ሥጋዊ በሽታን መፈወስ ብቻ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው እንጂ ጌታችን ሰው ሆኖ ይህችን ምድር በእግሩ ሲረግጥ በሽታ እንዳይኖር ያደርግ ነበር፡፡ ቅዱስ ባስልዮስ ‹በመስቀል ላይ በቆሰልኸው ቁስል ከኃጢአቴ ቁስል አድነኝ› ብሎ እንደጸለየ እኛም የዘወትር ልመናችን ለሚከፋው ለነፍሳችን በሽታ ነው፡፡
የጌታችን መምጣት ዋነኛ ዓላማ ለነፍስ ድኅነት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ለሥጋ አልመጣም ማለት አይደለም፡፡ ጌታችን ‹‹ኃጢአተኞችን ለንስሐ ልጠራ መጣሁ እንጂ ጻድቃን ልጠራ አልመጣሁም›› ‹‹ከእስራኤል ቤት በቀር ለአሕዛብ አልተላክሁም›› ሲል ለጻድቃን አይገደኝም ፣ ለአሕዛብ አላስብም ማለቱ እንዳልነበር ሁሉ ለነፍስ ድኅነት ቅድሚያ ሠጥቶአል ማለት ለሥጋ አይገደውም ማለት አይደለም፡፡
በመጻጉዕ ታሪክ ውስጥ ብዙ ቀሪ ነጥቦች ቢኖሩም ሁለት ነገሮችን ብቻ እናንሣና ይህችን አጭር ጽሑፍ እንግታ፡፡ ይህ ሰው ተፈውሶ አልጋውን ተሸክሞ ሲሔድ ሰንበት ለሰው ድኅነት እንደተፈጠረች ያልተረዱ አይሁድ በቁጣ ነደዱ፡፡ ‹‹ሰንበት ነው አልጋህን ልትሸከም አልተፈቀደልህም›› አሉት፡፡ ልብ አድርጉ ይህ ሰው በቤተ ሳይዳ ሠላሳ ስምንት ዓመታት ሙሉ ሲማቅቅ እንደኖረ የሰውን ገመና አዋቂ ነን ባዮቹ አይሁድ ይቅሩና ቤተ ሳይዳን የረገጠ ሰው ሁሉ ያውቃል፡፡ ላለፉት ሠላሳ ስምንት ዓመታት ወደዚያች የመጠመቂያ ስፍራ ሲሔዱ ያም ባይሆን በጎች ታጥበው ተመርጠው ወደሚገቡበት ወደ በጎች በር ሲያልፉ ይህን በሽተኛ በአልጋው ተጣብቆ ሳዩት አይቀሩም፡፡ አሁን ግን ከአልጋው ተነሥቶ የተሸከመችውን አልጋ ተሸክሞ በአደባባይ ሲያዩት የጠየቁትን ጥያቄ ተመልከቱ፡፡ ‹‹እንኳን ለዚህ አበቃህ ፤ ዛሬ መልአክ ወረደ ማለት ነው?›› ‹‹እሰይ ልፋትህን ቆጠረልህ!›› ያለው የለም፡፡ የተናገሩት አንድ ዐረፍተ ነገር ነው፡፡ ‹‹ሰንበት ነው አልጋ ህን ልትሸከም አልተፈቀደልህም›› የሚልብቻ!! በአይሁድ ዓይን ድኖ ሠላሳ ስምንት ዓመት የተኛበትን አልጋ ከመሸከሙይልቅ ሰንበት ማፍረሱ የሚያስደንቅ ትልቅ ዜና ነው፡፡
መጻጉዕ ‹ያዳነኝ ያ ሰው አልጋህን ተሸከም አለኝ› አላቸው፡፡ እስቲ በደንብ አስተውሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ይህን በሽተኛ ፈጽሞ አያውቁትም ነበር እንበል፡፡ እንደዛ ከሆነ ‹ያዳነኝ ሰው› ሲላቸው ‹ከምንድን ነው የምትድነው? ምን ሆነህ ነበር? ከየት ነው የመጣኸው?› ይሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ መዳኑን ማየት አልፈለጉም እንጂ ማን እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ከዚያም ‹‹ያዳነኝ ያ ሰው አልጋህን ተሸከም አለኝ›› ሲላቸው ‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሒድ ያለህ ሰው ማን ነው?››ብለው ጠየቁት፡፡ እስቲ ጥያቄና መልሱ ውስጥ ያለውን ሽሽት እንመልከት፡፡ ‹‹ያዳነኝ ሰው አልጋህን ተሸከም አለኝ›› ለሚለው መልስ ተከታዩ ጥያቄ ‹ማን ነው ያዳነህ?› የሚል ነበር፡፡ እነሱ ግን የጌታን የማዳን ሥራ ላለመስማት ጆሮአቸውን ደፍነው ስለነበር ‹አልጋህን ተሸከም ያለህ ማን ነው?› አሉ፡፡ የማዳኑን ሥራ እያዩ ከማመን ይልቅ መከራከር ፣ ከማድነቅ ይልቅ የትችት ሰበብ መፈለግ እንግዲህ ጌታን የሰቀሉ የአይሁድ ጠባይ ነው፡፡
የመጨረሻው ነገር መጻጉዕ ከዚህ በኋላወደ አይሁድ ሄዶ ጌታን መክሰሱና ለጌታ ሞት የመማከራቸው ምክንያት መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሰው ‹የሚብስ እንዳይገጥምህ ደግመህ ኃጢአትን አትሥራ› ብሎ ጌታ ቢያሳስበውም አልሰማም፡፡ ጌታ በተያዘበት በምሴተ ሐሙስ ለሊቀ ካህናቱ አግዞ ጌታችንን በጥፊ መታው፡፡ ጌታችንም‹‹ክፉ ተናግሬ እንደሆነ ስለ ክፉ መስክር መልካም ተናግሬ ከሆነ ግን ስለምን ትመታኛለህ?›› አለው፡፡ (ዮሐ.18፡23) ‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሒድ ከማለት በቀር ክፉቃል ተናግሬህ ከሆነ መስክርብኝ ፤ የተናገርኩህ መልካም ሆኖ ሳለ ስለምን ትመታኛለህ›› ማለቱ ነበር፡፡ ጌታችን በማግሥቱ ያ ሁሉጅራፍና ግርፋት ሲደርስበት አንድም ጊዜ ‹‹ለምን ትመታኛለህ›› ብሎ አልተናገረም፡፡ የመጻጉዕ ጥፊ ይህን ያህል ዘልቆ የተሰማውለምንድር ነው?
የመጀመሪያው ምክንያት ከቤተ ሳይዳ ከበጎች በር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ጌታችን የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ነው፡፡ በበጎች በር አልፎ የመጣው ንጹሐ ባሕርይ እንደሆነ ለማስረዳት ነበር፡፡ ለዚህም ንጽሕናው ዋነኛው ምስክር ፈውስን የሠጠው ይህ በሽተኛ ነበር፡፡ እሱ ግን መታው፡፡‹‹በቤተ ሳይዳ ክፉ ቃል ተናግሬህ ከነበር መስክርብኝ› ማለቱ ‹ነውር የሌለብኝ ፣ ለመሥዋዕት የተዘጋጀሁ በግ ነኝ ለምን ትመታኛለህ?› ማለቱ ነበር፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከሮማውያን ግርፋት በላይ ለጌታ ዘልቆ የሚሰማው ባዳነው ሰው መመታቱ ስለሆነ ነው፡፡ ውድ አንባቢያን መጻጉዕ ከሠላሳ ስምንት ዓመት በሽታ ብቻ ዳነ ፣ እኛግን የዳንነው ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በሽታ ነበር፡፡ ጌታችን እኛን ያስነሣን ከሲኦል አልጋ ነው፡፡ ከሌላው ሰው ይል ቅእግዚአብሔር የእኛ ዱላ ይሰማዋል፡፡ ይህም ዱላ ኃጢአታችን ነው፡፡ እግዚአብሔር ዛሬም ድረስ ለእያንዳንዳችን ይጠይቃል፡፡ ‹‹ለምን ትመታኛለህ?››
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ከ “የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክ ሰንበት ት/ቤት/St. George Church Sunday School” ገጽ ላይ የተወሰደ።