የ 2016 የልደት መልእክት (አባ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

የልደት ቃለ በረከት እና ምዕዳን

የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን የክርስቶስ አደራዎቻችን የሆናችሁ የተወደዳችሁና በደመ ክርስቶስ የከበራችሁ ኦርቶዶክሳውያን ሁላችሁ እንኳን ለጌታችን እና ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት አደረሳችሁ። አባቶቻችን ሊቃውንት በየጊዜው ከታነገሩትና ከቅዱሳት መጻሕፈት በማሰባሰብ ተዘጋጅቶ ከዚህ በታች የቀረበላችሁ የበዓሉ መልእክትና ቃለ ምዕዳን መንፈሳዊ ጥቅምን የሚሰጣችሁ እንዲሆን ከመልእክቱ ጋር መንፈስ ቅዱስ ይምጣላችሁ።

መግቢያ

በኢትዮጵያ የልደተ ክርስቶስ በዓል የአከባበሩ ሥነ ሥርዓት የሚከተለውን ይመስላል፤ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ሲሆን የጌታንን መወለድ የምሥራች የሚያበሥሩ የአብያተ ክርስቲያናቱ ደወሎች በያሉበት ድምፃቸውን ካሰሙ በኋላ ካህናቱም ሕዝቡም ወደ ቤተ ክርስቲያን ይገሰግሣሉ። ከዚያም በኋላ ካህናቱ ማኅሌት ቁመው ክርስቶስ ተወለደ በምድርም ሰላም ሆነ እያሉ ሲዘምሩ ወንዶቹም ሴቶቹም ተባብረው ሲያመሰግኑ ይቆዩና ቅዳሴ አስቀድሰው ልክ ከሌሊቱ ፱ ሰዓት ሲሆን ከዚህ ላደረሳቸው አምላክ ምስጋና እያቀረቡ ወደቤታቸው ይሄዳሉ።

አንዳንድ በስም ክርስቲያን ሆኖ የሚኖረው ግዴለሽ ደግሞ በሌላ ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሳይደርስ፣ ከምእመናንም ጋር ተባብሮ በጸሎትም ሆነ በቅዱስ ቍርባን ተካፋይ ሳይሆን ይከርምና ማኅበራዊ ኑሮ ስለሚያስገድደው በዓመት አንድ ቀን በዓሉን ለማክበር ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣል። መንፈሳዊ ደስታን ያስገኝልኛል በማለት ሳይሆን በዚህ ቀን ምርጥ ምግብና ዝና ያለው መጠጥ ስለሚቀርብበት የስጦታም ልውውጥ ስላለ ለሥጋዊ ደስታው ሲል በክርስቲያን ስም የሚጠራው ሁሉ ያከብረዋል። ይህ ዓይነቱ አከባበርም አሳዛኝ ከመሆኑም በላይ ለኑሮው መሻሻልን ለሕይወቱ ደስታን ሊፈጥርለት አይችልም። እንዲህ ያለው አድራጐት ራስን በራስ ማታለል በመሆኑ የበዓሉ መንፈስ ወደ አክባሪው ልብ ገብቶ የሚያርፍበት ሥፍራ የለውም፤ እንዲያውም በተዘዋዋሪ መንገድ ጸጸት እየሆነ የሕሊና ወቀሳ ያሳድርበታል።

በዓለ ልደትን ታኅሣሥ ፳፰ ቀን የማክበር ታሪክ

ከሮም ነገሥታት አብዛኛዎቹ ራሳቸውን በታሪክ የሚያሳውቁበት አንዳንድ ምክንያት ይፈጥሩ ነበር። ከነዚህም ውስጥ ሕርቃል ከዓቢይ ጾም የመጀመሪያውን ሱባዔ እንደ ዓወጀ ዮስጣትያኖስ የሚባለውም የሮም ንጉሥ ለምሥራቅና ለምዕራብ ኤጲስ ቆጶላት ሁሉ የልደትን በዓል ካኑን በሚባለው ወር በ14 ቀን ይኸውም ታኅሣሥ 28 ቀን መሆኑ ነው እንዲከበር ጸፈላቸው። በየዓመቱ በዚህ ቀን ለማክበር የማይስማሙለት ቢሆን ሠግር በሆነ ጊዜ ማለትም ጳጉሜን ስድስት ስትሆን ለማክበር ባቀረበው ተለዋጭ ሐሳብ ከብዙ ክርክር በኋላ ተስማሙ። የተስማሙበትም ምክንያት ጌታችን በማኅፀነ ድንግል የቆየው ዘጠኝ ወር ካምስት ቀን ነውና የጳጉሜ ስድስት መሆን ዘጠኝ ወር ከስድስት ቀን እንዳያደርገው በቍጥሩ ለመጠንቀቅ በማለት ነው።

ይህንንም የሮም ንጉሥ ዮስጣትያኖስ ራሱን ዝነኛ ለማድረግ ብሎ በፈጠራ እንዲከበር ያደረገውን በዓል የኢትዮጵያ ሊቃውንት የጸጋና የቅብዓት የተዋሕዶ ሃይማኖት መለያ ምልክት አድርገውት ኑረዋል። በዚህም የተነሣ እገሌ በዘመነ ዮሐንስ ታኅሣሥ 28ን ይጾማልና ጸጋ ወይም ትብዓት ነው በማለት ሲነቅፉት የቅብዓት ወገኖች (የጸጋ እምነት እንኳ በዘመናችን ጠፍቶልናል) ደግሞ ተዋሕዶዎችን በገሐድ ይበላሉ እያሉ ሲያሽሟጥጧቸው ይገኛሉ።

በየዐራት ዓመቱ በ28 በዓለ ልደትን ለማክበር ምክንያቱ አጥጋቢ አይመስልም። እንደ እውነቱ ከሆነ የልደት በዓል ብቻ የሚዘዋወርበት ግዝረቱ ጥምቀቱ ቦታውን የማይለቅበት ምን በቂ ማስረጃ አለው? ይኸ ሁናቴ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የማይደገፍ ለመነታረኪያ የእኛ አባቶች ብቻ የፈጠሩት መስሎ ስለሚታይ በየዓመቱ ልደት በ29 ቀን ብቻ የሚከበር ቢሆን መልካም ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ቢያስብበት።

ጾመ ገሐድ

ገሐድ ማለት በዚህ በተነሣንበት ዐውድ በዓርብና በረቡዕ ፋንታ፤ ወይም ምትክ የሚጾም ጾም ማለት ነው። አባቶቻችን ሐዋርያት የልደትና የጥምቀት በዓላት ዓርብና ረቡዕ ቀን በዋሉ ጊዜ እንደ ትንሣኤ ወይም ፋሲካ በመንፈቀ ሌሊት እንዲገደፍ እንጂ እንደ ሌላው ጊዜ እንዳይጾም ሥርዓት ሠርተዋል። እንዲህ ማድረጋቸው ሁለቱም በዓላት በጣም የተከበሩና የገነኑ በመሆናቸው ነው። የሁለቱን በዓል ታልቅነት አባቶች በምሳሌ ሲያስረዱ «ሰሞን ሠርቶ ለሰንበት፤ ዓመት ለፍቶ ለልደት» ይላሉ። ስለ ጥምቀትም «ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ» በማለት ይናገራሉ። እነዚህ በዓላት በእንዲህ ያለ ሁኔታ የሚከበሩ ገናናዎች ስለሆኑ እንዳይጾሙ በመደረጉ የቀደሙ የቤተ ክርስቲያን መምህራን በዓላችን መንፈሳዊ ሥራ የተለየው እንደ አይሁድ በዓላት ለዚህ ዓለም ተድላ ደስታ ለመብልና ለመጠጥ ብቻ የተዘጋጀ እንዳይሆን መንፈሳዊነትን የተላበሰ እንዲሆን ከልደትና ከጥምቀት አስቀድሞ ያሉት ዕለታት እንዲጾሙ አዘዙ። ስለዚህ እነዚህን ሁለት የጽድቅ ምግባራት ጾምን እና ከጾም በኋላ በዓል ማክበርን ሠሩልን። ነገር ግን ይህ በዓል እሑድ እና ሰኞ የዋለ እንደሆነ ሰንበታትን መጾም ስለማይገባ ሰኞ ቢውል እሑድን እሑድ ቢውል ቅዳሜን የውሎ ጾሙ ቀርቶ በሁዳዴ ወይም በዐብይ ጾም የሚበላውን ጥሉል ያልሆነውን ምግብ መመገብ ብቻ ይበቃል ብላ ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ሠርታዋለች። ይህ ጾምም ሲጾም ሕዝባዊ ቢሆን እስከ 9 ሰዓት፤ በልደትና በጥምቀት ቀን ሥጋ ወደሙን ለመቀበል የሚያስቡ ምእመናንና ቀድሰው የሚያቆርቡ ካህናት ቀን ውሏቸውን ከመጾማቸውም በላይ እስከ መንፈቀ ሌሊት በጾም ቆይተው ሥጋውንና ደሙን ማቀበልና መቀበል አለባቸው።

በዓለ ጌና/ገና

ገና ማለት ከፅርዕ ቋንቋ የተወረሰ ሲሆን የቃሉ ትርጉም ልደት ማለት ነው። እግዚአብሔር ለዓለም በሰጠው ተስፋ መሠረት የክርስቶስ መወለድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ፤ ይህም ዓለም የክርስቶስን የልደቱን በዓል ለማክበርና የደስታው ተካፋይ ለመሆን ተዘጋጅቶ የቀኑን መድረስ በታላቅ ናፍቆት ረዘም ላለ ጊዜ ሲጠባበቅ ቆየ። ጊዜውም ሲደርስ በአውግስጦስ ቄሣር ዘመነ መንግሥት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም የሰጠውን ቃል ኪዳን ለመፈጸም በቤተ ልሔም ከድንግል ማርያም ተወለደ። ጨለማና አሮጌ የነበረውም ዓለም አዲስ ዓለም ሆነ። በዚህም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ለአዲስ ዘመንና ለሥልጣኔ በር ታላቅ መክፈቻ ቁልፍ ሆኖ ተገኘ።

ስለዚህ የክርስቶስ ልደት ራሱ አንድ ታላቅ ስጦታ ስለሆነ ቃል ሥጋን ለብሶ በዚህ ዓለም ሲሠራና ሲያስተምር በቆየበት ጊዜ ለእያንዳንዳችን የምንጠቀምበትን ምሳሌና ትምህርት ስለሰጠን ለሕይወታችን ዓይነተኛ መምሪያ ሆነልን ።

የጌታችንና የመደኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን የማይመረመር ይልቁንም ምን ይረቅ ምን ይመጥቅ ተብሎ የሚደነቅ ታላቅ ምሥጢር ነው። መላው የሰው ዘር ከድቀተ አዳም ጀምሮ አምስት ሺህ ከአምስት መቶ ዘመን ሙሉ ከኀጢአት አዘቅት ወድቆ፣ የእርግማንና የሞት ፍርድ ቅጣቱን ተሸክሞ፤ በእግረ ሰይጣን እየተረገጠ የቁም ሙት ሆኖ ሲኖር ቃላት ሊገልጡት ከማይችሉት ኀዘን፣ ሥቃይና ተስፋ መቁረጥ ያድነው ዘንድ ስለወደደ እግዚአብሔር ቃል ሰው ሆኖ ሥጋን ለብሶ በተገለጠ ጊዜ የመላው የሰው ዘር የመከራ አዋጅ ተሻረ።

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን የእግዚአብሔር መለኮታዊ ፍቅሩ፤ ጸጋውና ይቅርታው ተገልጿል። ከፈጣሪው ቅጽረ ረድኤት ውጭ ሆኖ የነበረውም አዳም ወደ ጥንት ቦታው፣ ማዕረጉ፣ ክብሩና ሞገሱ ተመልሷል። ከፈጣሪው ጋር እንዲሁም ከራሱና ከአካባቢው ጋር ተጣልቶ ይኖር የነበረው አዳም ከሁሉም ጋር ታርቋል። ይህም ዕርቅ ምን ማለት እንደሆነ ለመግለጽ ያህል ኦሪት ዘፍጥረት 323 ላይ እንደተገለጸው አዳም የፈጣሪውን መንግሥት ለመገልበጥ ባደረገው አመፅና መቀናቀን ሞት ተፈርዶበት ከገነት ሲወጣ ዱሮ በትእዛዙ ይተዳደሩ የነበሩት ሲልካቸው ወዴት ሲጠራቸው አቤት ይሉት የነበሩ አራዊት አፋቸውን ከፍተው ሊወጡት ጥፍራቸውን አዘርዝረው ሊቧጥጡት ቀረቡ፤ እንዲሁ አልበህ ወተታችንን ጠጣ አርደህ ሥጋችንን ብላን እስከማለት ይወዱት የነበሩ እንስሳት ሁሉ ቀንዳቸውን አሹለው ሊወጉት ተነሡ። ይህም አዳም ባደረገው የተጣላው ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ ሳይሆን ከአካባቢውም ጋር እንደ ነበር ያስተምረናል።

ልደተ ክርስቶስ በጠቅላላው ነገደ አዳምን በሙሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ አውጥቶ ከአካባቢውና ከመላው ሥነ ፍጥረት ጋር ከነበረው ቂም፣ በቀልና ጠላትነት አስታርቆ የራሱንም የኅሊና ጦርነት ድል እንዲነሣ አድርጎ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን አብቅቶታል። በርሱም የሚገኘው ጸጋና ክብር የማይደርቅና የማያቋርጥ ሁል ጊዜም የመለኮትን በተዋሕዶ መገለጥ በሚያምኑት ኅሊና ውስጥ ሁሉ የሚፈስ የምሕረት፣ የሰላምና የይቅርታ አዕይንተ ተከዚ ነው።

በዚህ ዕለት እስኪ ዓይነ ሕሊናችን ወደ ቤተ ልሔም አንሥተን እንመልከት፤ እነሆ! ሰማይና ምድር የማይወስኑትና ሊሸከሙት የማይችሉት መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጭር ቁመትና በጠባብ ደረት ተወስኖ በልማደ ሰብእ በጨርቅ ተጠቅልሎ በአንዲት በረት ተኝቶ እናያለን! አህዮች፣ ላሞችና በጎች በአስተብርኮ በትንፋሻቸው ኃይል ብርዱን ሲከላከሉለት ይታያሉ። መላእክት በሰማያት እንሆ ከዛሬ ጀምሮ በምድርና በሰማይ መካከል ማለት በሰማይ በሚኖሩ በሠራዊተ መላእክትና በምድር ባሉት በደቂቀ አዳም መካከል የነበረው ቂምና በቀል ተሠርዞ ፍጹም ዕርቅ ሆነ፤ የሰላም ሰንደቅ ዓላማም ተተከለ እያሉ እረኞችን ሲያበሥሩ ይሰማሉ። በቤተ ልሔም አካባቢ ባሉ ጫካዎች የሚገኙ እንስሳትም ዛሬ የዓለም መድኀኒት ተወለደ እያሉ በዝማሬና በእልልታ ሲዘሉና ሲደሰቱ ይታያሉ።

እስኪ ደግሞ በእግረ ሕሊና ወደ ገሊላው ገዥ ወደ ሔሮድስ ቤት እናምራ ሁለት ዓመት የፈጀውን ጉዞአቸውን ፈጽመው ከሔሮድስ ቤተ መንግሥት የደረሱት ሰብአ ሰገል ዜናውን ሲያበሥሩት የተሰማው ድንጋጤ ይታየናል። ዓይኑ ደፍርሶ ግንባሩ ተቋጥሮ ከንፈሩ እየተንቀጠቀጠና ጥርሶቹ እየተፋጩ ከዙፋኑ ላይ ቁጭ ብድግ እያለ ከመማክርቱ ጋር በሕፃኑ ላይ ያደረገውን ምክረ ሰይጣንና የወሰነውን ዲያብሎሳዊ ውሳኔ በመንፈስ እናነባለን። ከሁለት ዓመትም በታች የሆኑ ሕፃናት በሙሉ እንዲሰበሰቡ አዋጅ ሲያስነግር ነጋሪት ሲመታና ጥሩንባው ሲነፋ በጀሮአችን ውስጥ ይደውላል፤ ለሕፃናቱም መታረጃ የተሳሉት ሰይፎች ከአፎቶቻቸው ተመዝዘው እንመለከታለን። ከፍ ብሎ እንደተረዳነው በቤተ ልሔም የተወለደውን ሕፃን ሁለት ዓይነት ወገኖች ይፈልጉታል፤ አንደኛው ወገን ሊሰግድለት፣ ሊያመልከውና የእጅ መንሻም ሊሰጠው ሲሆን ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ሊገድለው ሰይፍ የሚስል ነው።

ዛሬም ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን በስሙ የታነጸችውንና የቆመችውን የርሱን መንግሥት በመስበክና በማስተማር ላይ የምትገኘውን ቤተ ክርስቲያን ሁለት ዓይነት ሰዎች በጥብቅ የሚፈልጓት መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ከነርሱም አንደኛው ክፍል እንድትጠፋ የሚጥረው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እንድትስፋፋና ከውስጥና ከውጭ የገጥሟትን የመንፈስ፣ የሥርዓት፣ የአክራሪና ልቅ ዓለማውያን፣ የሐሰት ተራክያን ጦርነቶች ድል ነሥታ እንድትኖር የሚጥሩ በሐሳብም ሆነ በሥራ ከርሷ ጋር የተሰለፉት ናቸው፤ ነገር ግን ሊያጠፋት የሚጥሩ ሁሉ በከንቱ ይደክማሉ እንጂ ቤተ ክርስቲያን አትጠፋም። ቤተ ክርስቲያን ትልቅ እብነ አድማስ ናት፤ የወደቀባት ይሰበራል የወደቀችበትንም ታደቀዋለች ትፈጭዋለች።

ማጠቃለያ

አሁን ባለንበት ዘመን የክርስቶስ ልደት አከባበር ከመንፈሳዊ ሥርዓት ፈቀቅ እያለ ይታያል፤ የልደት ሌሊት የቅዳሴ፣ የማሕሌት፣ የመዝሙርና የጸሎት ሌሊት መሆኑ ቀርቶ የስፔይኖች የልደት አከባበር ተኮርጆ የዳንስ፣ የጭፈራና የስካር ምሽት እየሆነ ነው። መንፈሳዊ በዓልነቱ እንዲህ ጥቂት በጥቂት እየተሸረሸረ መሄድ የለበትም።

የጌታችንና የመደኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት በዘመነ ዮሐንስ ታኅሣሥ 28 ቀን ማክበር እንዴት ተጀመረ፤ ስለ ጾመ ገሐድ ቀኖና እና ስለ ጌና ወይም ገና ቃል ትርጉም፤ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥና በሕዝቡም ዘንድ ያለውን መንፈሳዊና ሥጋው አከባበር የዳሰስንበት፣ በልደቱ ቀን በቤተ ልሔም የተደረጉትን እና የታዩትን ክሥተቶች እንድናስብበት፤ እንዲሁም የበዓሉን ቃለ በረከትና ምዕዳን ለማስተላለፍ የተዘጋጀው ጦማር በዚሁ ይደመደማል።

ከሰባት መቶ ዓመት በፊት በነብይ «ሕፃን ተወልዶልናል፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል» (ኢሳ 96) እንደተባለው ኃያል አምላክ መደኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ከአቅሟ በላይ ለሆኑባት ኃይል፣ ክፉ ለሚመክሩባት ድንቅ መካሪ፣ ሰላሟን ለሚያውኩ የሰላሟ አለቃ ይሁንላት። ከእመቤታችን ከቅድስት ወንጽሕት ድንግል ማርያም መወለዱን ለምናምን ውሉደ ጥምቀት ለሆን ኦርቶዶክሳውያንም የዘላለም አባት ይሁነን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

አባ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ

ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 /ም።