የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት ምኩራብ በመባል ይጠራል ይህም ስያሜ የተሰጠው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለቱ ከሠራው ሥራ አንጻር ነው፡፡ ለዛሬው ለትምህርታችን መነሻ የምናደርገው የቤትህ ቅናት በላኝ በሚል ይሆናል፡፡
‹‹ቅንዓተ ቤትከ በልዓኒ›› የቤትህ ቅናት በላኝ፡፡ መዝ. 68(69) ፤10
ቤት ሲባል ማደሪያ ወይንም ቤት ለእኛ ሁለንተናችን ነው ማለት ይቻላል:: ሰው ከድካም የሚያርፍበት በአጠቃላይ ቤት ብዙ ነገር የያዘ ለሰው ልጅ ከመሠረታዊ ፍላጎቶቹ መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ወደ መኩራብ በመሄድ በኃጢአት የተበላሸውን ቤት ያስተካከለበት ቀን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የእግዚአብሔር ቤት ማን ወይም ምንድን ነው የሚለውን ነገር የምንማርበት ነው፡፡
ቤቱ ማን ነው
መመስገኛው፡ ይህን ስንል የሰው ልጅ በዚህ ምድራዊ ሕይወቱ እያለ ከፈጣሪው ጋር በጸሎት፤ በእንባ የሚገኛኝበት ቤት ነው ይህም ቤተ መቅደስ ወይንም በዛሬው አጠራር ቤተ ክርስቲያን ወይንም የክርስቲያን ቤት ክርስቲያኖች በአንድነት እግዚአብሔርን ለማመስገን የሚሰበሰቡበት ቤት ማለት ነው፡፡ እንግዲህ በዛሬው ዕለት በብሉይ ኪዳን የነበሩ ሰዎች መቅደሱን መመስገኛ መሆኑን ዘንግተው መለወጫ፤ መሻሻጫ አድርገውት ስላገኘ ቤቴ የፀሎት ቤት ነው እንጅ የወንበዴ ዋሻ አይደለም በማለት ሥራቸውን ሁሉ የነቀፈበትም ብቻ ሳይሆን ጅራፍ አንስቶም የገረፈበትም ቀን ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቤት ንጹሕ ነው በንጽሕና ሆነን ልናገለግልበትም ልንገለገልበትም ይገባል ምክንያቱም ሲያጠፉ የተገሰጹበትን ያህል በጎ ለሚሠሩ ደግም በአንጻሩ ምን ያህል ክብር እንደሚያገኙበት ግልጽ ነው፡፡ መቼም ቢሆን መጥፎ ነገር አድርጎ ከመወቀስ እንዲሁም በህሊና ከመፀፀት ይልቅ በጎ ነገር ሠርቶ በረከትንና ሰላምን ማግኘት ለሁሉም ሰው የሚበጅ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሰው ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚሄደው ሰላምን፤ በረከትን፤ ዕድሜን እንዲሁም የአገርን ሰላም ለመለመንና ለመማፀን ነው፡፡ እንዲህ ያለው ቤት በነጋዴዎች ተሞልቶ ሲመለከት ጌታችን ጅራፍ አዘጋጅቶ ሊገርፍ ጀመር፡፡ በእርግጥ ያኔ የሚታይ ወይንም ሰው በአይኑ የሚያየው ጅራፍ ነው፡፡ ሰው በጅራፍ ቢገረፍ የውጭ ቁስል ነው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቁስሉ ሊሽር ወይንም ሊድን ይችላል፡፡ ወገኖቼ ዛሬ ዛሬ ደግሞ ሰው ሁሉ በውጭ በምንሠራው በደል ውስጣችን የህሊና ቁስለኛ ሆኗል፡፡ የማይድን ቁስል ማለት ይህ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ቤት ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ እንዲህ በፍርሃተ እግዚአብሔር ሆነን ለምናደርገው ነግ ደገሞ ፀፀጽና ወቀሳ የለበትም በረከትና ሰላም እንጅ፡፡ የዕለቱ ወንጌል ዮሐ.2፤12 እንዲህ ይላል ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፥ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ። የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፥ ርግብ ሻጪዎችንም። ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም። የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ አሰቡ። የእግዚአብሔርን ቤት ያከበረ ሁሉ እርሱ ይከብራል፡፡
ቤት የተባለ ሰው ነው፡–
ሰው በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ የተፈጠረ ክቡር ፍጥረት ነው፡፡ ዘፍ.1፤26 እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። ይህ ሰው ክብር ነው፡፡ በእግዚአብሔር አርአያ መፈጠር ብቻ ሳይበቃው ሁሉን እንዲገዛ ስልጣን ተሰጠው እንጅ፡፡ ይህ ክቡር ፍጥረት ራሱን ባለመሆን ከእርሱ ተፈጥሮ ውጭ የሆኑትን በምንም ነገር የማይመስሉትን አራዊት እንስሳትን ለመምሰል ራሱን አዋረደ፤ ክብርና ጌጡ ልብስ ሆኖ እያለ ልብሱን በመራቆት እስሳትን መሰለ በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ የተፈጠረውን ማንነቱን ወይንም የእግዚአብሔርን ቤት በዝሙት አፈረሰ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡– 1ኛቆሮ. 6፤15-20 ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም። ወይስ ከጋለሞታ ጋር የሚተባበር አንድ ሥጋ እንዲሆን አታውቁምን? ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ ተብሎአልና። ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው። ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል። ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነው የእኛ ሰውነት በዝሙት፤ በኃጢአት ሲበላሽ እግዚአብሔር ለቤቱ የሚቀናው ቅናት ከባድ ነው ምክንያቱም ቤቱ የባለቤቱ የእግዚአብሔር እንጅ የእኛ አይደለምና፡፡ እኛ ሰዎች ይህን ቤት የተቀበልነው በአደራነት ነው፡፡ አደራውን የጠበቀ ዋጋው ይጠብቀዋል፡፡ በዚህ ዓለም የምንኖር ሰዎች ቤታችንን እንዴት በንጽሕና እንደምንይዘው እንዲያውም ሰው እንደምንቀጥርለት እኛው ራሳችን ምስክሮቹ ነን፡፡ ይህ ቤት የዛሬ ቤት ነው አይከተለንም ከሞት አያድነንም እስካለን ብቻ የምንኖርበት ቤት ነው፡፡ ለዚህ ቤት እንዲህ የምጨነቅለት ከሆነ ይህን ዓለም አሳልፎ በትንሳኤ ዘጉባኤ ለሚነሣው የእግዚአብሔር ቤት ለሆነው ማንነታችን ምን ልንሠራለት ይገባል ብለን እራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል፡፡ ቤቱ ሲፈርስ የማያድሰው ማነው? እንዲያውም ከቻለም አዲስ ቤት የተሸለ ቤት ሊሠራ ይችላል እንደ ሀብቱ መጠን፡፡ እግዚአብሔር የእርሱ ቤት በመሆናችን ስተን ከገነት ስንወጣ ዳግመኛ ሠራን፤ ቤቱ አደረገን ይህም የሆነ እንዲሁ ሳይሆን በመጀመሪያ በዓለም ውስጥ ድንግል ማርያም እርሷ በንጽሕና የተሸለመች ሆና በመገኘቷ ከእርሷ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሳ፤ ተወለደ፤ ግብጽ ተሰደደ፤ ተጠመቀ፤ገዳም ገብቶ ጾመ፤ አስተማረ፤ቀራንዮ ላይ ተቸንክሮ በመስቀል ላይ ዋለ፤ሞተ፤ተቀበረ፤ከሙታን ተነሣ፤ በ40ኛው ቀን አረገ፤ዳግመኛም ይመጣል፡፡ ይህ ሁሉ የተደገረው የእግዚአብሔር ቤት ለተባለ ለሰው ነው፡፡ ለቤቱ እንዲህ ዋጋ ተከፈለ ያውም የሞት ዋጋ፡፡ እግዚአብሔር እኛን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ እኛን ያዳነበት ጥበቡ ይልቃል፡፡ ሲፈጥረን ከመሬት አፈርን አንስቶ ነፍስን እም ኀበ አልቦ ማለትም ለነፍስ ምክንያት ሳይኖራት አዋሕዶ ፈጠረን ሲያድነን ግን መስቀል ላይ ተችንክሮ አዳም ላጠፋበት ሕዋሳት ሳይቀር ዋጋ ከፍሎ ነው፡፡
አዳም በእጆቹ ኃጢአት ሠርቶ ነበር ኢየሱስ ክርስቶስ እጁን ተቸነከረ
በእግሮቹ ኃጢአት ሠርቶ ነበር እግሮቹን ተቸነከረ
በአፉ ዕፀ በለስን በመብላት ኃጢአት ሠርቶ ነበር እርሱ በአፉ ሆምጣጤ ተቀበለ
በጀሮው በድሏል እርሱም በጀሮው የአይሁድን ሽሙጥ ሰማ
በአጠቃላይ አዳም ለሠራባቸው ሕዋሳት በሙሉ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካሳ ከፍሏል ምክንያቱም ቤቱ የእርሱ ቤት ነውና የእኛ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ሰው በዚህች አጭርና በማትረባው ዓለም ውስጥ ጠብቅ ተብሎ የተሰጠውን የአደራ ቤት ሲዘሙትበት፤ ሲያጭበረብርበት ሲታይ ሁሌም ነዋሪ የማይሞት ዘለዓለማዊ ይመስላል፡፡ ግን ሁሉም ወደ መጣበት አፈር ይመለሳል፡፡ በመሆኑም ሰው የእግዚአብሔር ቤት የሆነውን ማንነቱን ጠብቆ ካቆየ በመጨረሻ ሰዓት ከፈጣሪው ጋር በፍቅር ይኖራል፡፡
ቸርነቱን ያብዛልን ወላዲተ አምላክ በምልጃዋ አትለየን
በመጋቤ ሐዲስ ፍቅረ ማርያም ባዘዘው የተዘጋጀ