የበዓለ ልደት መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በዓለ ልደት መልእክት

የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?

ወተወሊዶ እግዜእ ኢየሱስ በቤተ ልሔም ዘይሁዳ በመዋዕለ ሔሮድስ ንጉሥ። ናሁ መጽኡ መሰግላን እምብሔረ ጽባሕ ወበጽሑ ውስተ ኢየሩሳሌም። እንዘ ይብሉ አይቴ ሀሎ ዘተወል ደንጉሠ አይሁድ እስመ ርኢነ ኮከበ ዚአሁ በምሥራቅ ወመጻእነ ከመ ንስግድ ሎቱ ትርጉም፦ ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል፦ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። (ማቴ. 21፤ ሉቃ. 21̵ 7 ፤ ዘኁ. 2415̵ 17)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩት ዐበይት በዓላት ዋናው የልደት በዓል ነው። የልደት በዓል ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ትሕትና ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ የማይታየው የታየበት ሥውሩና ኃያሉ እሳተ መለኮት አምላክ በሰው መጠን ለሰው ድኅነት የተወልደበት፣ ተስፋ አበው፣ ትንቢተ ነቢያትና ምሳሌ መጻሕፍት የተፈጸመበት እና እውን የሆነበት ታላቅና የበዓላት በኩር በዓል ነው።

በአፍ መነገሩ፣ በልብ መታሰቡ፣ ምስጋናውም ሁሉ ከፍ ከፍ ይበልና ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕለቱን ተፀንሶ ዕለቱን ተወልዶ ማድግና የወደደውን ሁሉ ማድረግ ሲቻለው ፍጹም አምላክ ብቻ ያይደለ ፍጹም ሰውም በመሆኑ ዘመን የማይቆጠርለት እርሱ ከብቻዋ ከሐጢአት በቀር በሰው ሥርዓትና ጠባይዕ በመገለጡ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው ? እንዲሁም የእናቱ ፈጣሪ ሲሆን ሕፃኑን ከእናቱ ጋር በጨርቅ ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኙታላችሁ እየተባለ ተነገረለት።

ሰብአ ሰገል ወደ ኢየሩሳሌብ እንደደረሱ የተወልደው አምላክ ወደየት ነው ቢሉ አምላክን ማንችሎ ይወልደዋል አምላክ ያስገኛል ከባሕርዩ ይህን ዓለም አስገኝቷል እንጂ እሩሱን ማን ይወልደውል እንዳይባሉ፤ ሕፃን ቢሉ በኢየሩሳሌም ሀገር ሰንቱ ሞቶ ስንቱ ተወልዶ ያድራልና እናውቅላቸዋለን እንዳይባሉ ግሩም የሆነ ጥያቄ ጠየቁ። ዛሬ በዓለም በቀን 385000 ፣ በዓመት 140 000 000 ሕፃናት ይህን ዓለም ይቀላቀላሉ ወይም ይወለዳሉ። ከዚህ በመነሣት በ2056 የዓለም ህዝብ 10 ቢሊየን ይሞላል እየተባለ ነው። ከዚህ ውስጥ የዛሬ 2013 ዓመት ቅደመ ዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው አምላክ መድኀኒትነት ያለው ንጉሥ ሁኖ ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት በድንግልና የተወለደባት እስራኤል ድርሻዋ ሰፊ ነው። የሚወልዱ ሴቶችን በማበረታታትና በመሽለም በርካታ ሕፃናት እንዲወለዱላት አጥብቃ ትሠራለች፣ ስለዚህ የተወለደ ሕፃን እያሉ ቢመጡ ኖሩ ስንቱ ሞቶ ስንቱ ተወልዶ ይውላል ያድራል ምን አይነት ጥያቄ ነው እንዳይባሉ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው እያሉ መጥተው የመጡበትን አሳክተው ተመልሰዋል።

ከእነዚህም የጥበብ ሰዎች ወይም ከሰብአ ሰገል መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ንጉሥ ለመሆኑ ዓለም እየተቀበለው ያለ እውነት ነው። ይደንቃል! እንዲህ ያለው በረከት ኢትዮጵያን አምልጧት አያውቅም። ንግሥተ አዜብ ወይም ንግሥት ማክዳ የሰሎሞንን ጥበብ ለመረዳት ወደ ኢየሩሳሌም ሂዳ ከንጉሥ ሰሎሞን ይልቅ የጥበብ ባለቤት የሆነውን የሰሎሞንን ፈጣሪ አድንቃና አመስግና ሰግዳ አምልካ እንደተመለሰች ሁሉ በሥጋ የዳዊት ልጅ ሁለተኛው ስሎሞን ሕፃን ነጉሥ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ደግሞ ከፊተኛው ሰሎሞን ይልቃልና ልጆቿ የሆኑ ነገሥታት ፍለጋዋን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው አምላክ ከሰው የሚጠብቀውን ቁም ነገር ፈጸሙ። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በብሥራት ቀን ለሕፃኑ እናት ለድንግሊቱ ንግሥት ለቅድስት ደንግል ማርያም «እግዚአብሔር አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋልለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም» እንዳላት ሁሉ በአባቱ በዳዊት ከተማ በቤተ ልሔም ሲወለድ የኢትዮጵያ ነግሥታት ሂደው ሰገዱ ወርቅ፣ ዕጣን እና ከርቤ እጅ መንሻ አቀረቡ።

የዛሬዎቹም የኢትዮጵያ መሪዎች ይህንን የቀድሞ መሪዎች መንገድ በመከተል ለተመሪዎች የበረከት ምንጭ የበጎ አብነት ሊሆኑ ይገባል። ለእግዚአብሔር መንበረከክ ለእግዚአብሔር መገዛት የሀገር ሰላም ነው፤ ለሀገር ልማት ነው፣ ከርሱ የተገኘውን ሥልጣን ገንዘብ ማድረጊያ መንገዱም ይሄው ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ( ሮሜ . 13 1) ይላልና የዛሬዎቹ ባለሥልጣናትም ከበታቻቸው ያለው ሕዝብ እንዲመራላቸው እንዲታዘዛቸው እንዲያከብራቸው ላሠለጠናቸው የባሕርይ ንጉሥ መገዛት ይገባቸዋል። ሹመቱን ሥልጣኑን በራሳቸው ብልጣ ብልጥነት፣ ኃይልና ጉልበት ያገኙት እየመሰላቸው ዓለምን የሁከት፣ የበሺታ፣ የጦርነት፣ የአንበጣ፣ የስደት፣ በዓጠቃላይ ገሐነም እያደረጓት ስለሆነ ማስተዋል ይገባቸዋል። የተወለደ ንጉሥ የሰላም አለቃ ነውና ቢቀርቡት ከሰላሙ ያሳድርባቸዋል።

ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት የተሳላሚ ጉዞ መሪ ቃሉ የተወለደው የይሁድ ንጉሥ ቢሆንም ንጉሡ የተገኘ ከእነሱ ስለሆነ የሚደሰቱና የሚኮሩበት መስሏቸው አይሁድን እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እንጂ የዓለም ንጉሥ መሆኑ ተስቷቸው አይደለም። የዓለም ንጉሥነቱንና የእግዚአብሔር ልጅነቱን ባለትንቢቱ መሢሕ መሆኑን ተረድተው ካለሆነ ለአይሁድ ንጉሥ በፈቃዳቸው ባሪያ ሊሆኑ እንዴት ይሄዳሉ? ሳይማርካቸው ሳያስፈራራቸው ያንን ለማድረግም ላልደረሰ የዳዊት የሰሎሞን ዓይነት አምላክነት የሌለው ሕፃን ንጉሥ ሊሰግዱ ሂዱ ማለት አይቻልም። የሁሉ ንጉሥ፣ መሆኑን በሚገባ አውቀዋል።

ሰብ አሰገል የጥበብ ሰዎች የሚባሉት ነገሥታት በኮከብ ተመራምረውና በኮከብ ተመርተው ኢየሩሳሌም መግባታቸው ብቻ ሳይሆን የተወልደው ሕፃን ወይም የተወለደው አምላክ ወዴት ነው? ቢሉ የማያስኬድ መሆኑን ማስተዋላቸው የጠለቁ የጥበብ ሰዎች መሆነቸውን ያጠይቃል።

የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ተብሎ በሰብአ ሰገል የተጠራው ሕፃን ለሰው ልጅ በሙሉ የሚበቃ በረከትን እና ሰላምን፣ ደኅነትን፣ ጸጋንና እውነትን ተመልቶ ከማይታየው ዓለም ወደሚታየው ዓለም የመጣ የዓለም መሪ ንጉሥ መሆኑን ለመረዳት ቀጥሎ ያሉትን ማስረጃዎች እንመልከት።

ወርኢኩ በራእየ ሌሊት፤ ወናሁ መጽአ ዓቢይ በደመና ሰማይ ከመ ወልደ እጓለ እመሕያው፤ ወበጽሐ ኀበ ብሉየ መዋዕል፤ ወተውኅበ ሎቱ ምኩናን ወክብር ወመንግሥት፤ ወኩሎሙ አሕዛብ፣ ወነገድ ወበሐውርት ተቀዩ ሎቱ፤ ወምኩናኑሂ ምኩናን ዘዓለም ዘኢየሐልቅ፤ ወመንግሥቱሂ ዘኢይማስን ትርጉም፦ በቀን ሳይሆን በሌሊት ራእይን አየሁ። ዓቢይ ጌታ ወለደ እጓለ እመሕያው እንደመሆኑ በምልዐተ ክብር በስፍሐተ ክብር በሥጋ ማርያም መጣ። አብ የሚገዛውን ይገዛል፣ አብ የሚፈርደውን ይፈርዳል፣ አንድም ወልደ እጓለ እመሕያው እርሱ በምጽአት በክበበ ትስብእት ይመጣል በመለኮቱ የሚፈርደውን በሰውነቱ ይፈርዳል፤ አንድም ደመናውን እየተረገጠ ይመጣል። የደብረ ታቦርን የዕርገትን የዮርዳኖስን ያጠይቃል፤ በነዚዚያ +የታየውን ደመና የተባለ የባሕርይ ክብሩን ያመለክታል። መመለክ ሊሰገድለት የሚገባው ነው። አገዛዝ፣ ክብርና መንግሥት ተሰጠው። መንደር መንድረው ሀገር አቅንተው የሚኑሩ ነገደ አህዛብ፣ ነገደ እሥራኤል፣ ነገደ ሴም፣ ነገደ ካምና ነገደ ያፌት ሁሉ ተገዙሉት ወይም ይገዙለታል። አገዛዙ ለዘላለም የማይፈጸም ነው። መንግሥቱም የማያልፍ ነው። (ዳን. 713)

ሰብአ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው ቢሉም ቤተ ልሔምንና አካባቢዋን እንኳ ደስ ያለሽ ሠራዊተ መላእክት ዘመሩብሽ ሰማያዊ ንጉሥ ተገኝብሽ አምላክ ያለወንድ ዘር በግብረ መንፈስ ቅዱስ በተአምር ከድንግል ተወለደብሽ ሰማይን መስለሽ ተገኝሽ ክብሩ ደስታው ለአዳም ዘር በመላው ቢሆንም ይህ ሁሉ ምሥጢር በመንደራችሁ በከተማችሁ የተፈጽመላችሁ ከእኛ ላቅ ያለ ደስታ ይገባችኋል ለማለት ያህል ነው እንጂ፣ የተወልደ ንጉሡማ ለግዛቱ ስፋት ወሰን የሌለው፣ እንደሰውነቱ መናገሻው ኢየሩሳሌም፣ ዙፋኑ የአባቱ የዳዊት ዙፋን፣ እንደ አምላክነቱ በወደደው መጠን ለወዳጆቹ የሚገለጥበት ቅዱሳንመላእክት በፊቱ እየሰገዱ ምስጋና የሚያቀርቡበት፤ የሞቱ ሰዎች ነፍሳቸው ሰግዳ ፍርድ የምትቀበልበት ሰባተኛው ሰማይ ጽርሐ አርያም ጣራ የሆነለት በሰድስተኛው ስማይ ጀርባ በሰማይ ውዱድ በመንበረ መንግሥት ላይ የተዘረጋው ነው (ኢሳ.61።ሕዝ. 122–27። ራዕ.42)። ሠራዊቱ ሠራዊተ መላእክት ነቢያት ሐዋርያት ምእመናን፣ አገዛዙ ወይም አመራሩ ሰይፍና ጦር የሌለበት በዘንግ፣ ሰላሙ የተትረፈረፈ፣ ብልጽግናውንና ልማቱን በተመለከተ ማርና ቅቤ እንደውሃ የሚፈሰበት፣ ርሀብና ጥም የሌለበት መሆኑ ቀደም ብሎ በነቢያት ተነገሯል። በኋላም የማዳን ሥራውን በይፋ ሲጀምር በራሱ ተገልጧል፣ በሐዋርያቱም በዓለም ተሰብኳል። እንዲህ ተብሎ።

ሕፃን ተወልደ ለነ ወልድ ተውህበ ለነ፤ ወቅድመት ኮነ ዲበ መትከፍቱ ወይሰመይ ስሙ ዓቢየ ምክር፣ አበ ዓለም፣ መልአከ ሰላም። እስመ አነ አመጽእ ሰላመ፤ ወሕይወት ዚአሁ፤ ወዕብይ ቅድሜሁ ወአልቦ ማሕለቅት ለሰላሙ። ዲበ መንበረ ዳዊት አቡሁ ትጸንእ መንግሥቱ። ወይትዌከፍ በጽድቅ ወበርትዕ እምይእዜ ወእስከ ለዓለም። ቅንዓተ እግዚአብሔር ይገብር ከመዝ ትርጉም፦ ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም። የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል። (ኢሳ. 96)

የተወለደው ንጉሥ የሰላም አለቃ ነው። የሰላም አለቃ ማለት ምን ማለት ነው? ሰላም የባሕርይ ገንዘቡ የሆነች ከማንም የማይፈልጋት ከእርሱ የምትመነጭና ለሚፍልጓት ሰዎች ሁሉ የሚሰጣት ማለ ነው። የሰላም አለቃ የሆነውን ጌታ ከመከተልና እርሱን ከማምለክ የራቀች አለቅነቱን ያልተቀበለች፣ ግዛቱ ዘላለማዊ መሆኑን የዘላለም ንጉሥነቱን አላውቅም እንቢ ያለችው ይህች የኛ ዓለም የሰላም ሚንስትር መሥሪያ ቤት ብታቋቁም፣ የሰላም ሺልማት ብታዘጋጅም ሰለሰላም አብዝታ ብትጮህም የሰላሙን ምንጭ ስላደረቀችው ሰላምን ከማይገኝበት ቦታ ስለምትፈልግ አልተሳካላትም። አሁን የዐመፅ ዋጋዋን እያገኘች የክህደት ፍሬዋን እየለቀመች ትታያለች ። የዘላለም መድኀኒት ተወልዶላት 2013 ዓመት ሁኖታል። እርሷ ግን በጸና ታማ ትገኛለች፤ የዘላለም አባት ከተገለጠላት እና በደሙ እንደገና ከወለዳት 2013 ዓመት ሁኖታል እርሷ ግን እጓለ ማውታ ሁና ትገናለች፣ የሰማይ መንግሥቱን በምድር ላይ እንድታሰፋፋ ውክልና ተሰጥቷት ነበር እርሷ ግን ወካይ የለኝም እንዳሻየ እሆናለሁ አለች፣ ቅባት አልባ አመዳምና ደረቅ ሥርዓቶችን ዲሞክራሲ፣ ሪፕብሊክ ምናምን እያለች ወዝ አልባ ሁና በድርቀት ትሠቃያለች።

ሕፃኑ መደኀኒት ነው፣ አባት ነው፣ መካር ነው፣ ኃይልና ብርታት ነው፣ አምላክ ነው፣ ነጉሥ ነው፣የሰው ብርሃን ነው፣የሰው ሕይወት ነው፣መልካም እረኛ ነው፣ ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ ነው። የተወለደው ለእኛ ነው። ተሰጥቶናል ተወልዶልናል የሚለው የቅዱሳን ነቢያት አነጋገር የሚያስረዳን ለእኛ እንጂ ለራሱ ወይም ለመላእክት እንዳልተወልደ ነው። እግዚአብሔር የሰጠን ሰላም ልጁ ነው። እርሱን ቀዳሜ ጸጋ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለው ቅዱስ ባስልዮስ የሰጦታ ሁሉ መጀመሪያና መጫረሻ ወድ ስጦታ ክቡር ስጦታ ታላቅ ስጡታ ብሎ ከመቀበል ውጭ ሌላ ሰላም ከሌላ ሥፍራ አናገኝም። ከድንግሊቱ የተወለደልንን ሕፃን በመካከላችን በማሳደግ ፋንታ ከመካከላችን እንዲጠፋ ካደርግነው ተጫማሪ ችግር የሚፈጥር እንጂ ከችግር የሚያወጣ በቁዔት ያለው ልጅ ከኛ ውስጥ አናገኝም።

ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ወትስምዮ ስሞ አማኑኤል፤ መዐረ ወቅብዐ ብዑል። እስመ ዘእንበለ ያእምር ሕፃን ሠናየ ወእኩየ የኀርያ ለሠናትይ። ወትተርፍ ምድር እንተ ትፈርኅ እምቅደመ ገጾሙ ለክልኤቱ ነገሥት ትርጉም፦ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። ክፉን ለመጥላት መልካሙንም ለመምረጥ ሲያውቅ ቅቤና ማር ይበላል። ሕፃኑ ክፉን ለመጥላት መልካሙን ለመምረጥ ሳያውቅ የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት አገር ባድማ ትሆናለች። (ኢሳ.714)።የሕፃኑ የንግሥና ዘመ በማር በቅቤና ለሰው ልጆች ጣቃሚ በሆኑ አልሚ በረከቶች የተመላ ነው። ክፉ አድራጊዎችን በሚቀጣ ሰላማውያንን በሚጠብቅ አለቅነት፣ አድልዎና ግፍ በሌለብት ንጉሥነት፣ በአባትነት ርኅራኄ በሚንከባከብ ፍቅር፣ በዕረፍትና ልማት የተመላ ዘመን ነው። የሰማይ መንግሥት ቅጥያ የማይታየው የእግዛብሔር ሰማያዊ ግዛት ነጽብራቅ የሆነችን ሰላማዊትና የአንድነት መንግሥት ይዞ ከሚታየው ወደ እውነተኛውና ሥውሩ መንፈሳዊና ዘላለማዊ መንግሥት የሚያሻግር፣ ወደዘላለም ሕይወት የሚመራ መልካም አመራር ይዞ የመጣ መሪ ነው። ነቢያት ይህን ዘመን በመናፈቅ ትንቢት ተናግረዋል። ሐዋርያት በዚህ ዘመን በመፈጠራቸው በሐሤት ተመልተው ይህንን ንጉሥ በፍጹም ልባቸው በፍጹም ሀሳባቸውና ኃይላቸው አገልግለውታል፣ ተገዝተውለታል። እንደ ንጉሥ ዳዊት ኃያላን እንደ ኢያቡስቴ፣ አዲኖን እና ኤልያና ደማቸውን እስከማፍሰስ ተከትለውታል። የመንግሥቱን ሕግ ወንጌልን በብዙ መካራ ውስጥ እየተመላለሱ ሰብከውለታል።

የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በጠቅላላው ስለ ተወለደው ሕፃን ንጉሥነትና የመንግሥቱ ሁኔታ የሚናገር ነው። በኃጢአት፣ በተላላፊ ወረርሺኝና በልዩ ልዩ የተለመዱ ቋሚ በሺታዎች የተያዘው ዓለም እንግዲህ ፍውስንና ድኅንነትን የሚፈልግ ከሆነ አይፍራ ደስ ይበለው ፤ መልአኩ እንዲህ የሚል የምሥራች ይዞለት መጥቷል። እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። መሪዎች የተፈበረከውን ለአንዱ ሲውጡት ሌላውን የሚያሳምመውን እና ያለተረጋገጠውን ክትባት ትተው የተወለደውን በዳዊት ከተማ የተገኘውን ለሁሉ በሺታ አስተማማኝ የሆነውን መድኀኒት በመከተብ አርአያ ቢሆኑ የሚያስተዳድሩት ሀገር ይለማል፣ የሚመሩት ሕዝብ ይባረካል።

የተወለደው አሁን ወደሰማይ ዐርጎ በአባቱ ዕሪና ያለው ንጉሥ፣ በተዋሕዶ የከበረው የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን በዓል በምታክብሩና በምትወዱት ኦርቶዶክሳውያን ላይ ሁሉ የልደቱ ብርሃን ይላክላችሁ።

የተወለደ ንጉሥ በእኛ ላይ በእኛም ውስጥ ይንገሥ፣ ከድንቅነቱ፣ ከምክሩ፣ ከአለቅነቱ፣ ከኃይሉ፣ ከሰላሙ ከመድኀኒትነቱ በእረኞች ላይ ከበራው የልደቱ ብርሃን ያሳትፈን። የዘለዓለም አባት ይሁነን አሜን።

አባ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ።

2013 /