ምኩራብ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያና የዐብይ ጾም ሶስተኛ ሣምንት ምኩራብ በማለት ይጠራል ጌታችን አምላካችን መድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ወደ ምኩራብ የገባበትና ያስተማረበት ነው ምኩራብ ማለትም ቀጥተኛ ፍቺው ኮረብታ፣ ተራራ የሚያህል ታላቅ ሕንጻ ማለት ነው ።ከዚህም የተነሣ የአይሁድ ቤተ ጸሎት ወይም ቤተ መቅደስ ማለት ይሆናል። እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓትና ትውፊት መሠረት በዐቢይ ጾም ስምንቱ ሰንበታት ሊዘመር የተዘጋጀው የጾመ ድጓው መዝሙር ነው፡፡ በየሰንበቱ የሚነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት ፣ የሚዘመረው የዳዊት መዝሙር (ምስባክ) ከሰንበቱ ስያሜ ጋር የሚያያዙና የሚዛመዱ ናቸው፡፡
በሰንበታቱ ውስጥ የሚነበበውና የሚዘመረውም ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ያስተማራቸውን ትምህርቶችና የሠራቸውን ዋና ዋና ተዓምራትና መንክራት የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ጾሙ የጌታ ጾም ስለሆነ ሁሉም መዝሙራትና ምንባባት ከጌታ ትምህርትና ሥራ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት ሦስተኛው ሰንበት ምኩራብ ተብሎ ተሰይሟል፡፡
‹ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ›› የሚልና ይህን የመሰለ ጌታ በምኩራብ ማስተማሩን የሚያዘክር የሚቀርብበት ሳምንት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን በኢሩሳሌም የአይሁድ ቤተመቅደስ ነበራቸው፡፡ ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን በወረረ ጊዜ ግን ቤተመቅደሱን አፈረሰ ፤ ሕዝቡንም ወደ ባቢሎን አፈለሰ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አይሁድ በሚኖሩባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ለጸሎት ቤት ይሠሩ ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም እየተዘዋወረ በሚያስተምርበት ጊዜ ግን ብዙ ምኩራቦች ነበሩ፡፡ ሐዋርያት በሚያስተምሩበት ወቅት ከአንዳንድ ቦታዎች በቀር በምኩራቦች ገብተው ወንጌልን አስተምረዋል፡፡
በብሉይ ዘመን ቢያንስ አስር የጎለመሱ ወንዶች /የቤተሰብ ኃላፊዎች/ በቦታው ከተገኙ እነዚህን ምኩራቦችን ለመሥራት ይፈቀድላቸው ነበር፡፡ በምኩራብ ውስጥም የሕግ መጽሐፍትና በነቢያት የተጻፉ ጽሑፎች በብራና ጥቅልል ይገኛሉ፡፡ ምዕመኑ እንዲሰማቸው እንደ መድረክ ባለ ቦታ ላይ ካህናትና መምህራን ቆመው መጽሐፍትን ያነባሉ ቃለ እግዚአብሔርንም ያስተምሩ ነበር።
ምኩራብን የሚመሩት አለቆች ጥፋተኛ ሰው ሲገኝ በመግረፍ ወይም ከምኩራብ በማስወጣት ሊቀጡ ሥልጣን ነበራቸው፡፡ አገልጋይ ወይም የሚራዱ ወጣቶችም ልጆችን በማስተማር ጥቅሎችን በማቅረብ በተጨማሪ የአለቆችን ትዕዛዝ በመፈጸም ያገለግላሉ፡፡
በየሰንበቱ ሕዝብ ሁሉ በምኩራብ ተሰብስበው አምልኮታቸውን ይፈጸሙ ነበር፡፡ ከአምልኮታቸው ውስጥ ጸሎት፤ ከሕግና ከነቢያት ንባብ ፤ስብከትና ቡራኬ ነበር፡፡
በዚህ ምኩራብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገኝቶ ሕዝቡን አስተምሯል፡፡
‹‹ ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ምኩራብ ገባ ሊያነብም ተነሳ፡፡›› ሉቃ 4፡16
‹‹ ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በሚገባቸው ያስተምራቸው ነበር፡፡›› ማቴ 13፡52
‹‹ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኩራብ ያስተምር ጀመር›› ማር 6፡1
ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤የሰንበት ጌታዋ የምሕረት ባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም የሰንበት ጌታዋ ነው ፡፡ያባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል (እያለ የሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው) ፤ ወደ ምኩራባቸውም ገብቶ ዝም ይሉ ዘንድ ገሠፃቸው፤ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕምና፣ የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ።
ምንባባት መልዕክታት
(ቆላ. 2÷16-ፍጻ.) እንግዲህ በመብልም ቢሆን÷ በመጠጥም ቢሆን÷ በልዩ ልዩ በዓላትም ቢሆን÷ በመባቻም ቢሆን÷ በሰንበትም ቢሆን የሚነቅፋችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡ ……
(ያዕ.5÷14) ወንድሞቻችን ሆይ÷ እምነት አለኝ፤ ምግባር ግን የለኝም የሚል ሰው ቢኖር÷ ምን ይጠቅመዋል? በውኑ እምነቱ ልታድነው ትችላለችን? ከወንድሞቻችን÷ ወይም ከእኅቶቻችን÷ የታረዙ ወይም የዕለት ምግብ ያጡ ቢኖሩ÷ ከእናንተም አንዱ …….
ግብረ ሐዋርያት
(የሐዋ.10÷1-8.) በቂሳርያም ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራም የመቶ አለቃ ነበር፡፡ እርሱም ጻድቅና ከነቤተሰቡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነበር፤ ለሕዝቡም ብዙ ምጽዋት ይሰጥ ነበር፤ ዘወትርም ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር፡፡ ……..
ምስባክ
መዝ 68፡9
እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ
ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ
ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡
ትርጉም፦የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና
የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና
ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፡፡
ወንጌል
ዮሐ. 2÷12-ፍጻ. ከዚህም በኋላ እርሱና እናቱ÷ ወንድሞቹና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቅፍርናሆም ወረዱ፤ በዚያም ብዙ ያይደለ ጥቂት ቀን ተቀመጡ፡፡ ……..
ቅዳሴ: – ቅዳሴ ዘእግዚእ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር