በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
በዓለ ጥምቀት
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩት በዓላት አንዱና ዋናው የጥምቀት በዓል ነው። የጥምቀት በዓል ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ትሕትና ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ተጉዞ በአገልጋዩ በቅዱስ የሐንስ እጅ የተጠመቀበትን ዕለት የምናስብበት ከጌታችን ዓበይት በዓላት አንዱ ገናና በዓል ነው፡፡
በአፍ መነገሩ፣ በልብ መታሰቡ፣ ምስጋናውም ሁሉ ከፍ ከፍ ይበልና ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕለቱን ተፀንሶ ዕለቱን ተወልዶ ማድግና የወደደውን ሁሉ ማድረግ ሲቻለው ፍጹም አምላክ ብቻ ያይደለ ፍጹም ሰውም በመሆኑ ዘመን የማይቆጠርለት እርሱ ከብቻዋ ከሐጢአት በቀር በሰው ሥርዓትና ጠባይዕ ቀስ በቀስ በማደጉ 30 ዓመት ሲሆነው ሊጠመቅ ወደርዳኖስ ወንዝ ሔደ ትብሎ ዘመን ተነገረለት፡፡ ዮርዳኖስ እንደደረሰ ጌታችን ተለይቶ የሚታወቅበት ምልክት ሳይኖረው ቅዱስ ዮሐንስ በመገልጥ አወቀው። ይህንንም ራሱ ሲመሰክር «እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፦ መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ» (ዮሐ. ፩፥፴፫) ይላል። ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀት በውሃ ያጠምቅ እንደነበረና ልጅነት የሚገኝበት የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና ምሉዑ የድኅነት ምሥጢር የሚገኘውና የሚታወቀው ግን ከእርሱ በኋላ ከሚመጣው ከክርስቶስ የተነሣ እንደሆነ መስክሯል።
ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት በአንቀጸ–ብርሃን ድርሰቱ የአብን ነገር የነገረን ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ የውልድንም ነገር አጎልቶና አስፍቶ የነገረን አብ እንደሆነ ሲያስረዳ «ልጅህ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንተ ብቻ አባቱ እንደሆንክ እርሱም ብቻ ልጅህ እንደሆነ አስተማረን።በሰማይ እናት በምድርም አባት የለውም ብለን እናምናለን። መምጣቱን ካአባቱና ከእውነት መንፈስ ከጰራቅሊጦስ በቀር የሚያውቅ ሳይኖር ከሰማይ ወረደ ብለን እናምናለን» ሲል ተናግሯል። ይህም የጥምቀት መንሠረቱ ነው። አባቱን አብን ሕይወቱን መንፈስ ቅዱስንና እሱን ወልድን ማወቅ እና ማመን ከሌለ በውሃና በመንፈስ ቅዱስ አንዲቱን ጥምቀት መጠመቅና ልጅነትን ማገኘት አይቻልም።
ቅዱስ ዮሐንስ በመንፈስ ቅዱስ ተልኮ «እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸ ከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል» (ማቴ.፫፥፲፩)። እያለ የላቀ ጥቅም የምታሰጠው ጥምቀት ከእርሱ የትገኝ የጌታችንን መምጣት በጉጉት እየጠበቀ፣ ትንቢት እየተናገረ፣ የተጠራለትንና የተመረጠለትን ሥራውን እያከናወነ ሕዝቡን እያዘጋጀ ሳለ አስቀድሞ የተናገረለት ክርስቶስ በሥፍራው ተገኝቶ የጽድቅ ሥራውን ተመለከተከለት ወደደለት። አጥምቀኝ ብሎ ሲጠይቀው እውነተኛ ሥራውን እንደወደደለትና እንዳጸደቀለት ያጠይቃል።
ዛሬ እያንዳንዳችን ወደምንገኝምበት ዮርዳኖስ ጌታችን ቢመጣና ቢጎበኘን በቅዱስ ዮሐንስ ምትክ የተሾመለትን ሥራ፣ የተጠራለትን አገልግሎት በተሰጠው ጸጋ እያከናወነ የሚያገኘው ነቢይ፣ ሐዋርያ፣ ጳጳስ፣ ካህን፣ ዲያቆን፣ ዘማሪና ምእመን ያገኝ ይሆን? እውነቱን እንናገር ካልን እንዲያ ሲያደርግ የሚገኝ በጎ አገልጋይ በጭንቅ ካልሆነ በቀላሉ በሩቅ ካልሆነ በቅርቡ ማግኘት ከባድ ነው። አብዛኛውና ሁሉም በሚያሰኝ ደረጃ አገልጋዮች የተሰለፉበትን እና የተጥሩበትን የአገልግሎት ቦታ እግዚአብሔርን ለማክበር፣ በረከት ለማግኘት፣ ሰዎችን ለመርዳትና ለመጥቀም ወይም ለማገልገል፣ ሃይማኖትን ለመጠበቅ፣ ታሪክን ለማቆየት፣ ሀገርን ለማበጀትና ለማልማት፣ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ሰውና እግዚአብሔርን ለማገናኘትና፣ ትውልድን ለማነፅ መሆኑ ቀርቶ ለእንጀራ መብያ፣ ለሆድ መሙያ ለምድራዊ ኑሮ መኖሪያ እንደ ንግድ፣ እርሻ፣ የመሳሰለው ሁሉ አይነት ምድራዊ ሥራ ነው የሚቆጥሩት።
ጌታችን አጥምቀኝ ቢለውም ቅዱስ ዮሐንስ ከሌሎች ሰዎች መካከል ለይቶ እንዲያውቀው መንፈስ ቅዱስ በገለጠለት ጊዜ ደንግጦ እና በትሕትናውም ተደንቆ የተናገረውን ነገር «ዮሐንስ ግን፦ እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር» ሲል ወንጌላዊ ማቴዎስ ሁኔታውን ግልጾ ጽፎልናል።
በጌታችን ጥምቀት ዕለት በዮርዳ ኖስና በአካባቢው ስለተከሠተው ክሥተትም ቅዱሱ ደራሲ «ነድ ለማየ ባሕር ከበቦ፤ ማይ ኀበ የሐውር ፀበቦ» ትርጉም ውሃውን /የዮርዳኖስን ወንዝ/ እሳት ከበበው፤ ወሃውም መሄጃ ጠፋው ተጨነቀ» ሲል ይገልጸዋል። በሥጋ ድንግል ማርያም ተግልጾ ዮሐንስን አጥምቀኝ የሚለው አምላክም ፈጣሪም ነውና የዮርዳኖስ ወንዝ በጌታችን የክብሩ ብርሃን ተሞላ። የዚህ ቅዱስ ደራሲ አነጋገር በልደቱ ዕለት በእረኞች ዙሪያ ሰለ በራው ብርሃን ከተናገረው ከወንጌላዊ ሉቃስ ይገናኛል ማለትም «እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ» (ማቴ.፪፡፱) ተብሎ በወንጌላዊ ሉቃስ የተገለፀውን ይመስላል። የዮርዳኖስ ወንዝ መሔጃው ጠፋው ተጨነቀ የሚለውም ከነቢዩ ዳዊት ትንቢት ጋር የተገናኝ ነው። «ባሕር አየች ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ … አንቺ ባሕር የሸሸሽ፥ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽ፥ ምን ሆናችኋል? (መዝ.፻፲፬፥፭) ተብሎ እንደ ተጻፈው። ከፍ ሲል እንዳየነው ከልደቱ ብርሃን የተነሣ እረኞች እንደፈሩ ከጥምቀቱ ብርሃን የተነሣም ውሆች ፈርተዋል። ይህም አስቀድሞ «አቤቱ፥ ውኆች አዩህ፥ ውኆች ፈሩ፤ ጥልቆች ተነዋወጡ፥ ውኆችም ጮኹ» (መዝ. ፸፯፥፲፮) ተብሎ በትንቢት የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው።
ከላይ በጥቅሡ እንደተመለከትነው በእረኞች ዙሪያ የጌታ ክብር ያበራ መልአኩ ወደ እነሱ በቀረበ ጊዜ ነበር ። ያም የልደቱ ሠዓት ሌሊት ነበር። ጌታችን ሲጠመቅም ከሌሊቱ 10 ሠዓት ነበር፡፡ እንዲያ ከሆነ ታዲያ የመልአኩ ፈጣሪ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲቀርበው ቅዱስ ዮሐንስና የዮርዳኖስ ወንዝ እንዴት የበለጠ በብረሃን አይሞሉ!። ሌላው አስደናቂ ምሥጢር ደግሞ በዚያች ሠዓት ጌታችን ሲጠመቅ ርግብ መጥታ በራሱ ላይ አረፈች፡፡ ከዚያም ከሰማይ አንድ ድምጽ መጣ፤ ድምጹም “የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡ እርሱን ስሙት” የሚል የእግዚአብሔር አብ ድምጽ ነበር፡፡ ረግብ የተባለውም በቁሙ ርግብ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ ነበር። ርግቦች በሌሊት እንደማይበሩ የታወቀ የተረዳ ነገር ነው።
የጥምቀት በዓል አከባበር በቅድ ስት ሀገር ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ–ክርስቲያን በየዓመቱ ጥር ፲ ቀን ከዋዜማው ጀምሮ ጌታችን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ከመንፈስ ቅዱስ መወለጃችንን መጀመሪያ እርሱ አድርጎ ሊያሳየን፣ ሊመሠ ርትና ሊባርክልን መሄዱን በድርጊት እያሳይች ታከብራለች።
ጌታችን ፴ ዓመት ሲሞላው ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ እንደተጠመቀ ለማስታወስ ጥር 10 ቀን ሁሉም ታቦታት በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ውሃ ወዳለበት ሥፍራ በመሔድ በድንኳን ውስጥ ያድራሉ፡፡ ይህም ዕለት ከተራ ይባላል፡፡ ከተራ የሚለው ቃል «ከተረ» ሰበሰበ፣ከበበ፣ ያዘ፣ ገደበ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ይህ ዕለት ከተራ የተባለው በአካባቢው ያለው ውኃ እንዳይፈስ ተገድቦ ሕዝቡ እንዲጠመቅበት ስለሚዘጋጅ ነው፡፡
ይህም በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ከሆነ ነው እንጂ በውጪው ዓለም በአብዛኛ ለሕዝቡ አመች ቀን ተፍልጎ ይከበራል። አከባበሩም በአንዳንድ ቦታ ታቦታቱ ወጥተው የሚያድሩበት ቦታ ስለማይገኝ ቢገኝም የጸጥታ የወጭም ችግር ስለሚኖር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በፕላስቲክ ግንዳ በተከተረ ውሃ ሥርዓቱ ደርሱ ምእመናን የዮርዳኖስን ጸበል ተረጭተው ታስቦ ይውላል።
በአንዳንድ ቦታ ደግሞ በቅርብ ርቀት ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ፫ትም ፭ትም እየሆኑ በቀኑ አለመሆኑ ነው እንጂ ሁሉም ነገር በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ እንደሚደረገው ሆኖ ተባብረውና ተቀናጅተው ያከብራሉ።
ወደ ሀገር ቤቱና በሀገር ቤት ደረጃ ወደሚያከብሩት ስንመለስ ታቦታቱ ወደ ድንኳኑ ከገቡ በኋላ ሌሊቱን ካህናቱ ሲያመሰግኑ፣ ሲዘምሩና ሲቀድሱ እና ዕለቱን የተመለከተ ትምህርት ለሕዝቡ ሲያስተምሩ ያድራሉ፡፡ በዕለቱ ጥር ፲፩ ቀን ጠዋት ከ፲፪ ሠዓት ጀምሮ በተከተረው ውኃ ላይ ሥርዓተ ቅዳሴ ወይም የጥምቀተ ባሕሩ ጸሎት ከተደረገ እና ከተባረከ በኋላ በዓሉን ለማክበር የተሰበሰበው ሕዝብ ይረጫል፡፡ ካህናቱ ሕዝቡን ጸበል ከረጩ በኋላ ልዩ ልዩ ያሬዳዊ ሥርዓቶች ይፈጻማሉ፡፡
በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሆነ እንደሆነ ደግሞ እንዳሁኑ ህዝቡን የቀይ ጥቁር፣ የሀብታም ድሃ ሳያደርጉትና ሞራሉን ሳይሰልቡት ታቦታቱ ካደሩበት ቦታ ወደየመቅደሳቸው ለመመለስ እስኪነሡ ድረስ ወጣቱ ቀደም ብሎ ከየመንደሩ ወጥቶ ቡድን እየሠራ ሩር ወይም ጥንግ ልጊያ፣ ይገጥም ነበር፣ የኔ ፈረስ የጊዮርጊስ ያንተ የመርቆሬዎስ እተባባሉ ፈረስ ግልቢያ ውድድር ያደርጉም ነበር አስኳላ ቀመሱም ኳስ ይጫወት ነበር። አሁን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ለጥምቀት በዓል ልዩ ድምቀት የሚሰጠው ይህ ሁሉ ባህል ሆን ትብሎ ቀስ በቀስ ዳብዛው እንዲጠፋ እየተደረገ ነው። ከዚያም ታቦታቱ ከድንኳን ወጥተው ወደየመጡበት ቤተ ክርስቲያን በየአጥቢያቸው ምእመናን ሆታና እልልታ፣ የታቦት ዘፈን፣ በካህናት ያሬዳዊ ዝማሬ ታጅበ ሔዳሉ፡፡
የጥምቀት ምሳሌ በብሉይ ኪዳን
ነገረ ጥምቀት እንደ እንግዳ ድራሽ እንድ ጉርፍ ፈሳሽ አይደለም በበዙ ህብረ አምሳልና ትንቢት ተነግሯል እንጂ። በብሉይ ኪዳን ዘመን የተነገረው ትንቢትና ለአማናዊው የሐዲስ ኪዳን ጥምቀት ምሳሌ የሆንው ሁሉ ብዙ ነው። ከዚያም መካከል የሚከተሉትን ከብዙው እጅግ በጥቂቱ እናያለን ።
የያዕቆብ አብትር /በትሮች/ና የላባ በጎች፦ ከዚህኛው ቀጥለው ከታች የሚከተሉት ምሳሌዎች በብዙዎች ጸሐፍትና ሰባክያን የሚዘወተሩ ሲሆኑ ይህ ምሳሌ በማሕሌቱ በፀናፅልና በከበሮ ከሚታወስ በቀር ተተርጉሞ ሲነገር አይሰማም ይሁን እንጀ አስደናቂ ምሥጢርና የጥምቀት ምሳሌ ነው። መጀመሪያ ከቅዱስ መጽሐፍ ላይ እንደሰፈረው ጥሬ ጥቅሱን እናስቀድማለን «ያዕቆብም ልብን ለውዝ ኤርሞን ከሚባሉ እንጨቶች እርጥብ በትርን ወስዶ በበትሮቹ ውስጥ ያለው ነጭ እንዲታይ ነጭ ሽመልመሌ አድርጎ ላጣቸው። የላጣቸውንም በትሮች በጎቹ ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ በውኃ ማጠጫው ገንዳ ውስጥ በበጎቹ ፊት አኖራቸው፤ በጎቹ ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ ይጎመጁ ነበር። በጎቹም በትሮቹን አይተው ከመጎምጀታቸው የተነሣ ፀነሱ፤ በጎቹም ሽመልመሌ መሳይና ዝንጕርጕር ነቍጣም ያለበቱን ወለዱ። … እንዲህም ሆነ፤ የበረቱት በጎች በጎመጁ ጊዜ፥ በጎቹ በትሮቹን አይተው በበትሮቹ አምሳል ይፀንሱ ዘንድ ያዕቆብ በትሮቹን በውኃ ማጠጫው ገንዳ ውስጥ ከበጎቹ ፊት አደረገ» (ዘፍ. ፴፥፫፯–፵፩)
በጉቹ ከወለዱ በኋላ እነዚያን በትሮች በመጠጫው ውስጥ አያኖራቸው ነበር። ለመፅነስ በሚችሉበት ወቅት ሦስት በትሮችን ለጦ በውሃ መጠጫው ገንዳ ከውሃው ውስጥ ያጋድማቸውል በትሮቹን እያስመስሉም ይወልዱለት እና ይበዙለት ነበር። ላባ ብዙ ጊዜ ደመወዙን ለዋውጦበት ስለነበር እውነተኛ ደመወዝ ከፋይ እግዚአብሔር ይንን የጥምቀት ምሳሌ የሆነ ጥበብ ገልጾለት ከላባ ይልቅ እርሱ ባዕለ ፀጋ ሆነ።
የብሉይ ኪዳን ትርጓሜ መምህራን ይህንን ክፍል ሲተረጉሙትና ሲያብራሩት ሁለቱን ጨርሶ ልጧቸዋል አንዱን ቅጥልጣል አድርጎታል፤ ጨርሶ የተላጡት ነጫጮቹ የአብና የመንፈስ ቅዱስ አምሳል ቅጥልጣሉ የውልድ አምሳል፤ አምላክ ወሰብእ ማለትም ሰውም አምላክም ነውና። አባኅኩ ወይመ ጠቦቶች የመምህራን፣ አባግዕ ወይም በጎች የምእመናን፣ ወሃው የጥምቀት፣ አባግዕ ወይም በጎች አብትርን /በትሮቹን እያስመሰሉ መውለዳቸው ምእመናንም በጥምቀት ምክንያት ሥላሴን መስለው ይወለዳሉና ። ላባ የዲያብሎስ ያዕቆብ የጌታ ምሳሌ። ምልክት ያለው ለያዕቆብ ምልክት የሌለው ለላባ እንደሆነ ሁሉ ሀብተ ውልድና ስመ ክርስትና ያለው ለጌታ፤ ሀብተ ውልድና ስመ ክርስትና የሌለው ለዲያብሎስ ምሳሌ ብለዋል።
አባ ስብሐት ለአብ የተባለው የመልክአ ሥላሴ ደራሲ ይህንን አስመልክቶ «በአብትረ ያዕቆብ በርሃ ሥላሴክሙ ፀሐይ። ወተመሰሉ ሰብአ ዓይን አባግዐ ላባ ወማይ። ለኀበ አባግዕ ዘዮም ወጥምቀት ዓባይ። ትርጉም ስሉስ ቅዱስ ሆይ የሦስትነታችሁ ፀሐይ በያዕቆብ በትሮች ላይ አበራ፤ ስለሆነም ለአሁኑ የታላቂቱ የጥመቀት ልጆች የቀድሞ የላባ በጎችና የሚጠጡበት የወንዝ ውሃ መልካም ምሳሌ ሆነ። ሲል አጣፍጦ ገልጾታል።
ግዝረት፦ ግዝረት ለጊዜው ለእሥራኤል ዘሥጋ መለያ ሲሆን ፤ ፍጻሜው ግን ሊመጣ ላለውና ለእሥራኤል ዘነፍስ ምዕመናን መክበሪያ ለሆነው ለጥምቀት ምሳሌ ነው ።(ዘፍ .፲፯ ፥ ፲፬። ቆላ ፪፥ ፲፬) ።
የኤርትራ ባሕር (ቀይ ባሕር)፦ ሙሴ የክርስቶስ ፤ ባሕሩን የከፈለባት በትር የመስቀል ፤ ባሕረ ኤርትራ የፍርድና የሲኦል ፤ በተከፈለው ባሕር የተሻገሩት እስራኤል በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙና የጎኑ ወሃ በጥምቀት ከእግዚአብሔር ተወልደው ባሕረ ኃጢአትን የሚሻገሩ ምእመናን ምሳሌ ነው ። (ዘፀ .፲፬ ፥ ፳፩ ። ፩ኛቆሮ. ፲ ፥ ፩)።
የዮርዳኖስ ባሕር፦ ኢያሱ የክርስቶስ ፤ ዮርዳኖስ የጥምቀት ፤ ዮርዳኖስን የተሻገሩ እሥራኤል በክርስቶስ አምነው በመጠመቅ የዳኑ ምዕመናን ምሳሌ ነው ። (ኢያሱ. ፫፥፲፬ ፣ ፬ ፥ ፲፭) ።
የዮሐንስ ጥምቀት፦ ዮሐንስ ህዝቡን የንስሐ ጥምቀት እያጠመቃቸው ከቆየ በኋላ ጌታ በሚመጣበት ጊዜ ግን እነሆ የእግዚአብሔር በግ በማለት ወደ ጌታ መርቷቸዋል ስለዚህ የዮሐንስ ጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ለአማናዊው የጌታ ጥምቀት የሚያዘጋጅ ነው ። ማቴ. ፫ ፥፩ ። የሐ ሥ ፩ ፥ ፭ ።
ትንቢት
ከላይ እንደተገለጸው ስለ ጌታችን ጥምቀት በትንቢት ብዙ የተነገረ ቢኖርም ይህንን ብቻ ጠቅሠን ለማለፍ የዚህ ዝግጅት መጠን ይወስነናል እንሆ «ባሕርም አይታ ሸሸች፣ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ፣ ተራሮች እንደ ኮርማዎች ዘለሉ» (መዝ ፻፲፫ ፥ ፫)።
የልጅነት /የክርስትና/ ጥምቀት አንዲት ናት
ከወላጆቻችን በሥጋ የምንወለደው አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ ሁሉ ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር የምንወለደውም (የምንጠመቀው) አንድ ጊዜ ብቻ ነው ። በመሆኑም ጥምቀት አንዲት ናት አትደገምም ። የጥምቀት ምሳሌ የነበረው ግዝረት አንድ ጊዜ ብቻ እንደነበረ ሁሉ ጥምቀትም አንድ ጊዜ ነው ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጥምቀት አንዲት መሆኗን «አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት ፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ» (ኤፌ. ፬፥ ፬) በማለት ተናግሯል። ከጌታ ሥጋና ደም የምንሳተፍበት ምሥጢር በመሆኑ ጌታችንም የሞተውና የተነሣው አንድ ጊዜ ነውና አንድ ጊዜ ብቻ እንጠመቃለን ። (ሮሜ .፮ ፥ ፫)።
ይህ በዓል ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጸበት፣ የዓለሙ ሁሉ ቤዛ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከሠላሳ ዓመቱ በኋል ሰው የሆነበትን የማዳን ሥራ በግልጽ የጀመረበት፣ በዐመፃችን ምክንያት ያጣነውን ሰማያዊና መንፈሳዊ ሀብት ሁሉ የምናግኝባት ሥርዓተ ጥምቀት የተመሠረተችበት፣ የበረከቱ ግምጃ ቤት ለሰው ዘር ሁሉ ከላይ በሰፊው የተከፈተበት በዓል ነው።
አባቶቻችን ጠብቀው ያስረከቡንን በዓለ ጥምቀት ለማክበር የረዳን ቸርነቱና ፍቅሩ ወሰን የሌለው አምላካችን ለዑል እግዚአብሔር ክፍ ያለ ምስጋና ይድረሰው። የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱና የጥምቀቱ ብርሃን በቅዱስ ፈቃዱ በመላው ሕዝበ ክርስቲያን ላይ ይብራ አሜን።
አባ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ