የ 2018 የልደት መልእክት (አባ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ!

 

የተወደዳችሁና የተከበራችሁ ኦርቶዶክሳውያን ውሉደ ክህነት፣ምእመናንና ምእመናት እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ። የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ ሰላም፣ ምሕረትና በረከት ይብዛላችሁ። 

 

ወይቤሎሙ መልአክ ኢትፍርኁ እስመ ናሁ እዜንዎክሙ ዓቢየ ዜና ፍሥሐ ዘይከውን ለክሙ ወለኩሉ ዓለም።

እስመ ናሁ ተወልደ ለክሙ ዮም መድኅን ዘውእቱ ክርስቶስ እግዚእ ቡሩክ በሀገረ ዳዊት።

 

መልአኩም እነሆ ለእናንተና ለመላው ዓለም ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ አላቸው (ሉቃ 210 ኢሳ ፰፥፩፫። ዮሐ ፬፥፳፭)

 

ሰማያዊ መልአክ፣ የምሥራቹን ለዓለም እንዳወጀው፣ የምሥራቹን የሰሙ ኖሎት/እረኞች አይተው እንደስሙት ሆኖ በማግኘታቸው እንደተደሰቱ፣ ወንጌላዊ ሉቃስ እንደመሰከረው የጌታችን ልደት የዓለም ተድላና ደስታ ነው።  

በልደት ቀን ሰማይና ምድር ተገናኙ፤ እግዚአብሔር ቃል ከድንግል ተወልዶ ሰው ሆኖ በመካከላችን አደረ። እርሱ ቅዱስነቱን፣ ልዕልናውን፣ ጌትነቱን፣ አምላክነቱንና ንጉሥነቱን በሚገልጽ በታላቅ ክብር ሳይሆን በትሕትና፣ በግርግም ተወለደ። በዚህም ልደት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን የማይመዘን ፍቅር ገለጠ፤ ለደካሞች ተስፋ፣ በጨለማ ውስጥ ለነበሩና ላሉ ታላቅ ብርሃን ወጣ፤ ለዓለም መዳን ሆነ፤ የምሥራቹን ታላቅ ያደረገውም ይህ ነው።

ከቅድስት ድንግል ማርያም በቤተልሔም የተወለደው ሕፃን የሰላም ንጉሥ ነው። በጦርነት፣ በሰላም እጦትና በፍርኀት በተጨነቀ ዓለም ውስጥ፣ ክርስቶስ ልቡናችንን ለመመለስ፣ ቁስላችንን ለመፈወስ፣ እኛን ወደ ላይ ከእግዚአብሔርና ወደጎን እርስ በርሳችን ለማስታረቅ መጣ። በመምጣቱም ጨለማን የሚያሸንፍ ብርሃን እንዳለ፣ ማንኛውንም አስጨናቂ ኃይል ሁሉ የሚያሸንፍ ጸጋ እንዳለ አበሠረን።

ደረቅ ሐዲስ ተናጋሪ የሚባለው ነቢዩ ኢሳይያስሕፃን ተወልደ ለነ ወልድ ተውህበ ለነ = ሕፃን ተወለደልን ወንድ ልጅም ተሰጠን” (ኢሳ 96) ሲል የተናገረው ትንቢት በቤተልሔም ተፈጸመ። ቅዱሳን መላእክትስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያትብለው አመሰገኑ፤ እረኞች በእምነት ሄደው አመለኩት፤ ዓለምም የሰላም ንጉሥን ተቀበለች። ስለዚህ በዚህ ቅዱስ ዕለት የቅዱሰ ባሕርይ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደቱን  እያከበርን ልባችን በደስታና በሐሤት ይሞላ።

የአምላክ ሰው መሆን የሰውም አምላክ የመሆን ትምህርተ ተዋሕዶ ምሥጢረ ሥጋዌ ወይም የጌታችን ነገረ ልደቱ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ አይደለም። በተለያየ ኅብረ ትንቢትና ምሳሌ በብሉይ ኪዳን ቅዱሳን 5500 ዘመናት እየተነገረና እየተሰበከ  ሱባዔ እየተቆጠረለት በብሉይ ኪዳን ተስፋ ሆኖ ተነግሮ በልደተ ክርስቶስ የተፈጸመ ነው። 

ትንቢት፦ ስለመሲሑ መምጣት ያልተናገረ ነቢይ የለም። ጥቂቶቹን ብንጠቅስ ድንግል በድንግልና ፀንሳ እንደምትወልድ በድንግልና የወለደችውንም ስሙን አማኑኤል (እግዚአብሔር ከእኛ ጋር) ብላ እንደምትጠራው፤ ሕፃን ነገር ግን ኃያል አምላክ እንደሆነ፤ የሚወለድበት ሀገር ወይም ቦታ በቤተልሔም መሆኑ ሁሉ አስቀድሞ በነቢያት ተነግሯል።(ኢሳ 714 ኢሳይያስ 96፤ ሚክ 52)

ትንቢታዊ ምሳሌውም፦ የአብርሃም መሥዋዕት (ዘፍጥረት 22) እግዚአብሔር ራሱ መሥዋዕትን እንደሚያዘጋጅ፤ የያዕቆብ መሰላል (ዘፍጥረት 28) ሰማይና ምድር በክርስቶስ ልደት እንደሚገናኙ፤ የሙሴ ራእይ «እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድድ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ» (ዘጸአ 32) እንደተባለው መለኮት ቅድስት ድንግል ማርያምን ሳያቃጥልት፤ ከእርሷ የነሳውን ሥጋም በተዋሕዶ እንዳከበረው የሚሰብክ ምሳሌ ነው። ይህም ምሥጢር ወይም ልደተ አምላክ በተዋሕዶ 1500 ዓመት አስቀድሞ ለሙሴ በዚህ ምሳሌያዊ ክሥተት ተገልጿል።

ይህም ሰውን ለማዳን ካለው በጎነትና ቸርነት ፍቅርና ርኅራኄ የተነሳ ነው። «ፈቂዶ ይፈውስ ትዝምደ ሰብእ። ተገምረ በማኅፀነ ድንግል ተኃቢኦ። ለኵሉ ኃይል እለ በሰማያት ማኅደር። ወለእለ ይትቃወማ ኃይል በኢያእምሮ ሠወሮሙ። ሥጋ ለብሰ ዘይማስን ወዘኢይማስን። ለሥጋ መዋቲ ረሰዮ ዘኢይማስን = ባሕርየ ሰብእን ነገደ ሰብእን ሊያድን ወዶ በሰማያዊ ቤቱ ካሉ መላእክት ተሠውሮ በድንግል ማኅፀን ሥጋን ተዋሐደ። መፀነሱንም ደቂቀ አዳምን የማዳን ሥልጣኑንና በጎ ፈቃዱን የሚቃወሙ አጋንንት እንዳያውቁት ሠወረባቸው። ዐውቀው ቢሆን የሰውን ሁሉ ፅንስ ያውኩ ወይም ያበላሹ ነበርና። የማይሞት የማያልፍ መለኮት ምዋች ኃላፊ ሥጋን በተዋሕዶ አከበረው፤ አንድም መዋቲ የአዳም ሥጋን የማይሞት አደረገው» እንዲል መጽሐፈ ኪዳን። 

ለዚህ ልደት አንክሮ ይገባል! ነቢዩ ዳዊት «እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ» (መዝ 1271) እንዳለው ለሰው ሁሉ ያማረ ቤትንና ከተማን የሚሠራ አምላክ፣ ሰባቱን ሰማያት ከእሳት የፈጠረ እሳተ መለኮት ሰውን ለማዳን ወደዚህ ዓለም ሲመጣ በአንዲት ታናሽ ብላቴና ገሊላዊት ድንግል ማኅፀን አደረ። ሕገ ሕፃናትን ጠብቆና አክብሮ ድሆች እንኳ በማይወለዱበት በከብቶች ግርግም ተወለደ። ግሩም የሆነ፣ ለገናናነቱም አቻ የሌለው፣ ለብልፅግናው ማጣት፣ አራጣ፣ መበደርና መዋስ የሌለበት እርሱ እንደ ምስኪን እንደ ድሀ በግርግም ተወለደ፤ ጒስቍልናችንን ያርቅልን ዘንድ ስለ እኛ ጐሰቈለ፡ 

ለንጹሕ፣ ኃያልና ቅዱስ መለኮት በከብቶች በረት መወለድ የመስቀሉ መከራ መጀመሪያ ነው። በማይገባው ሥፍራ ተወለደ፤ የማይገባውን የመስቀል ሞት ሞተ። እንግዲህ ክፋታችንና አበሳችን የቱን ያህል ጒስቍልናን አምጥቶብን እንደነበረና ምን ያህል ካሳ እንደጠየቀ የሚያስረዳን ነው። ይህንንም ድህነትና መዋረድ መጠን ከሌለው ሰውን ማፍቀሩ የተነሳ ስለ እኛ በፈቃዱ ተቀበለው።

እንደ ምስኪን ከሰማያት ወርዶ እንዴት ከድሀ ቤት አደረ? እንዳለው ቅዱስ ያሬድ ዛሬም ይህን የሚይጠቅ ቢኖር አንተ ሞኝ ያንተን ድህነት ወስዶ የእርሱን ሀብት አደለህ ሲል ቅዱስ ጳውሎስ ይመልለታል። ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ዳግመኛ በጻፈላቸው መልእክቱ ለዚህ ጥያቄያቸው የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና፤ ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ። (2ቆሮ 89)ሲል መልሷል። 

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ነገረ ልደቱን በትጉሕ ልብ ተምረንና መርምረን ምሥጢሩን ተረድተን በከፍተኛ የክርስቶስ ፍቅር ተመልተን በዓለ ልደቱን እናድናከብርና እንድንዘምር ጥሪ ያቀርብልናል፣ « ይህን ድንቅ (ልደት) እዩ፡፡ ስለ ተገለጠልን ምሥጢር ምስጋና አቅርቡ፡፡ ሰው የማይሆን ሰው ሆኖዋልና፣ ቃል ሥጋን ተዋሕዷልና፡፡  ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት፤ ጥንት የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ። የማይታወቅ ተገለጠ የማይታይ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ በርግጥ ሰው ሆነ፡፡ ትላንት የነበረው ዛሬም ያለው መቼም የሚኖረው ኢየሱስ ክርስቶስ እንሰግድለትና እናመሰግነው ዘንድ አንድ ባሕርይ ነው» ቅዱስ ኤፍሬም ለዚህ ከአእምሮ በላይ ለሆነ፣ ለሰው ልጅ ወሰን ከሌለው ፍቅሩ የተነሳ ለተፈጸመ የአምላክ መወለድና ከእኛ መዛመድ ስግደት፣ ዝማሬ፣ ማሕሌት ክብርና አድናቆት እንድናቀርብ ይጋብዛል።

ዛሬ በደስታና በታላቅ መንፈሳዊ ዝግጅት የምናከብረው የልደት በዓል የመዳናችን ታላቅ ምሥጢር የተገለጠበት ቀን ነው። ይህ ቀን እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን ወደ ዓለም የመጣበት ቀን ነው።ቃል ሥጋ ሆነ በመካከላችን አደረ” (ዮሐ 114) እንዲል። ይህም ታላቅ የምሥራችና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን መሠረትና ዐምድ ነው። መለኮት ከትስብእት ጋር ተዋሐደ፣ ሰው በተዋሕዶተ ቃል አምላክ ሆነ፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ኖረ በእኛው ሥጋ ሊያድነን ከኃጢአት ብቻ በቀር እንደ እኛ ሰው ሆነ እንደማለት ያለ ታላቅ ዓለም አቀፋዊ የምሥራች፣የለም። ክርስቶስ በሥጋ መወለዱ ሰውን አክብሮታልና። 

ክርስቶስ ከኃጢአት ሊያድነን፣ ከሞት ሊያወጣን፣ ከዲያብሎስ እስራት ሊፈታን ለመዳናችን ተወለደ፤ ልደቱ መጀመሪያ ነው፤ መስቀሉና ትንሣኤው ፍጻሜ ናቸው። ስለዚህ የሚወደውን የባሕርይ ልጁን መደኀኒት አድርጎ በመላክ ፍቅሩን በሥራ ስለገለጸልን (ዮሐ 316) እኛም እንደ አቅማችን ያለንን ሁሉ በመስጠት በዓለ ልደቱን እናከብረዋልን። 

በልደቱ የነቢያት ቃል ተፈጸመሕፃን ተወልዶልናል” (ኢሳይያስ 96) እግዚአብሔር በነቢያት የተናገረውን ፈጸመ። ይህ ምን ያስተምረናል? እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ቃሉ አይለወጥም፤ ስለዚህ ልደቱ የእምነታችን መሠረት ስለሆነ እናከብረዋለን።

ብርሃን ክርስቶስ ጨለማን አበራ፤በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው” (ኢሳ 92) እንዲል። ክርስቶስ የዓለም ብርሃን ነው። ስለዚህ  ከሲኦልና ከቀቢፀ ተስፋ ጨለማ የወጣንበት ስለሆነ በዓለ ልደቱን በችጹም ኃይላችንና ልባችን እናከብረዋለን። በልደቱ እውነት ተገለጠ፤ ተስፋ ተወለደ፤ ሕይወት ተገኘ።

እንዲህ ያለ ትሕትና እንደምን ያለ ትሕትና ነው! ለዘመኑ ብልየት /ማረጀት፣ ለመንግሥቱ ኅልፈት ለግዛቱ ወሰን ወይም ቦርደር፣ ለሥልጣኑ ሽረት የሌለበት ንጉሠ ነገሥት እግዚአ አጋእዝት አምላከ አማልክት ቢሆንም በቤተ መንግሥት ሳይሆን በግርግም ተወለደ። በዚህም ትሕትና የመንግሥተ ሰማያት መንገድ መሆኑና አገልግሎት ከግል ክብር እንደሚበልጥ አስተማረን። እኛም በፍቅር፣ በትሕትና፣ በንጽሕና በኑሯችን ሁሉ ልደቱን እንመስክር።

የተወደዳችሁ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንና ምእመናት፣ ሊያድነን፣ ሊያበራልን፣ ሊቀድሰን፣ ልጆቹ ሊያደርገን እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ወደእኛ ምድር ስለመጣልን፣ በቤተልሔም ስለተወለደልን በዓለ ልደቱን በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት እናከብረዋለን። በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት በዓለ ልደትን ከማክበር አስቀድሞ በጾምና በጸሎት እንቆያለን፤ ምክንያቱም በበዓሉ የሚፈጸመው ሥርዓተ አምልኮ፣ ምስጋናው፣ መሥዋዕቱ የሚወደው እንዲሆንና  የክርስቶስን ልደት በንጹሕ ልብ ለማክበር በንስሐ ለመዘጋጀት ነው። 

በመሆኑም የሰላማችን፣ የክብራችን፣ የመድኃኒታችንን፣ የዘላለም አባታችንን የብርሃናችንን ጠላቶቹ ስንሆን ያለልክ የሚወደንን የጌታችንን የአምላካችንን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ልደት ለማክበር እስከምን ተዘጋጅተናል? መላእክት ምስጋናን፣ ኖሎት አድናቆትን፣ እንስሳት የስትንፋሳቸውን ሙቀት፣ ሰብአ ሰገል ወርቅ ዕጣንና ከርቤን ይዘው ቀርበዋል። እኛስ ምስጋናውን፣ መሥዋዕቱን በአጠቃላይ አምልኮቱን ይዘን ወደፊቱ ለመቅረብ ምን ያህል ተዘጋጅተናል? በምን አይነት ሰብእና፣ በምን አንደበት፣ በምንስ አይነት ከናፍር! ለመቅረብ ተዘጋጅተን ይሆን! እንግዲህ ዘንድሮ  የምናመሰግነው በሊህ በአጥንትና በጅማት በተያያዙ ከናፍር አይደለም። ሐሰትና እውነት በማፈራረቅ በሚነገርባት በዚች ሥጋ አንደበት አይደለም። አላ በዝኩ ቃል ዘበላዕሌነ መንፈስ። ጌታችን በሰው ፋንታ ተገብቶና አብነት ሆኖ አብን በአመሰገነበት፣ በአብና በወልድ ህልው የሆነ መንፈስ ቅዱስ በገለጸው በዚያ ቃል ነው፤ መንፈስ ቅዱስ ባደሰው ቃል ነው፤ የማመስገን ፈቃዱ ከትጋት ጋር ካለን ከዚህ ሸንጋይና አታላይ የነጹ አያሌ ቃላት አሉልን እነሱን እንፈልግ። እንግዲህ ከዚህ ከለመድነው ቃል የተለየ ሌላ ከወዴት የተገኘ ቃል ነው? የሚል ቢኖር ሕፃናት በማኅፀን ሁነው የሚያመሰግኑበት ቃል ነው፤ ጻድቃን ከበቁ በኋላ የሚያመሰግኑበት ቃል ነው፤ ነፍሳት በገነት ሁነው የሚያመሰግኑበት ቃል ነው፤ አዳም ሰባት ዓመት ሙሉ በገነት ሳለ ያመሰግንበት የነበረ ቃል ነው፤ ብዙ የብዙ ብዙ የሚሆኑ ትጉኃን ሠራዊተ መላእክት በቤተልሔም ተገኝተው በዓለ ልድቱን ሲያከብሩ ያመሰገኑበት ዘወትርም የሚያመሰግኑበት ቃል ነው። እንደዚህ ከፍ ባለ መንፈሳዊ  ሥርዓት እንደናክብረው የልደቱ ባለቤት ይርዳን። 

እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ሲፀነስና ሲወለድ፤ ሰው መሆኑ የአምላክነቱን ክብር አልቀነሰውም። በበረት እስከ መወለድ፣ እስከ መስቀልና መቃብር ድረስ የተዋረደውም ከመለኮቱ ጋር በተዋሐደ ሰውነቱ ነው። እኛን ለማዳን ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ በእንስሳት መካከል በግርግም ተወልዶ ትሕትናን አስተማረን፤ በድኾች መካከል ተገኝቶ ፍቅርንና ርኅራኄን ገለጠ። ልደተ ክርስቶስ፦ የእግዚአብሔርን ፍቅር ገለጠ፣ ብርሃንን አበራ፣ ሰላምን አመጣ፣ መዳንን ሰጠ። ስለዚህ ልደት የፍቅር፣ የብርሃን፣ የሰላም እና የመዳን ቀን ነው።

ዛሬም ክርስቶስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይኖራል፤ በቅዱስ ቃሉ፣ በቅዱስ ቁርባን ከእኛ ጋር ይተባበራል፤ እኛን ይዋሐዳል። ስለዚህ በንስሐ እንቅረብ፣ በጸሎት እንጽና፣ በፍቅርና በትሕትና እንመላለስ። ቤቶቻችን ታናናሽ ቤተ ክርስቲያንኖች ይሁኑ፤ ልጆቻችን በእምነት ይደጉ፤ ድሆችንና ችግረኞችን በርኅራኄ እንርዳ። እንዲሁም የቅድስት ድንግልን ትሕትና፣ የእረኞችን ታዛዥነትን፣ የመላእክትን አመስጋኝነት/ምስጋና እንከተል፣ ወንጌሉን በተግባር እንኖር። ሕይወታችንም የክርስቶስ ፍቅር ምስክር ይሁን። ድሆችን፣ ብቸኞችን፣ በሺተኞችንና ተስፋ የሚያጡትን አንዘንጋቸው። ያገኘነውን ደስታ ከእነርሱ ጋር እንካፈል።

የልደቱ ብርሃን በእያንዳንዳችሁ ሕይወት ይብራላችሁ፤ መልአኩ በልደቱ ዕለት ለምድር ያወጀውን ሰላም በሀገራችን በኢትዮጵያ ዛሬም ደግሞ ያውጅልን። እረኞች ያገኙት መንፈሳዊ ደስታ፣ የመላኩ የምሥራች ድምፅ፣ የዓለሙ ሁሉ ደስታ መሠረት የሆነች የቅድስት ድንግል ማርያም ጸጋ በልባችሁ ይኑር። የልደቱ በረከት ዛሬ፣ ነገና ሁል ጊዜም በሁላችሁ ላይ አድሮ ይኑር።

 

ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት 

ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ!

 

ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ፳፻፲፰ ዓ/ም

አባ ሕርያቆስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኢጣሊያና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና

በኖርዌይ የኦስሎ መካነ ቅዱሳን ቅ/ገብር ኤልና አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤ/ክ የበላይ ጠባቂ።