በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር
መስከረም 2018 ዓም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ነጻነትና ክብር አጎናጻፊ፣ ዕውቀትና እድገት አስፋፊ፣ ሃይማኖትና ባህል፣ ታረክና ቅርስ ጠባቂ፣ ቋንቋ ፈጣሪ፣ ሕግና ደንብ አውጪ፣ መመሪያ ሰጪ ወዘተ በመሆን ባለውለታዋና መዝገብ ቤቷ ሆና ተገኝታለች። በመሆኑም ቤተ ክርስቲያናችን እንደ ሌሎቹ ያይደለ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ወረሰችው ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረውን 5500 ዘመን፥ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለውን 2018 ዘመን በማለት አጠቃላይ ዓለም ከተፈጠረ 7518 (ሰባት ሺሕ ዐምስት መቶ አስራ ስምንት) ዓመት ነው ትላለች።
በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ዘመናቱ በሕግ የተወሰኑና በሦስት የተከፈሉ ናቸው። እነርሱም፡
ሕገ ልቡና፦ ከአዳም እስከ ሙሴ፥ ከመጽሐፍ በፊት የነበረ፡ ከአበው ቃል በቃል የተወረሰ።
ሕገ ኦሪት፦ ከሙሴ ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ልደት። ከኦሪት የተቀዳ።
ሕገ ወንጌል፦ ከክርስቶስ ልደት እስከ አሁን ያለውና ወደፊትም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለመጨረሻ ጊዜ ጸንቶ የሚኖረው ዘመነ ሐዲስ፥ ከወንጌል የተማርነው ነው።
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን አብነት በማድረግ የዘመናት አከፋፈልን እንደሚከተለው ማየት ይቻላል። ዘፍ 5፥3 አዳም ሴትን ሲወልድ ዕድሜው 230 ነበር። ሴት ሄኖስን ሲወልድ ዕድሜው 205 ነበር። ሄኖስ ቃይናንን ሲወልድ ዕድሜው 190 ነበር። ቃይናን መላልኤልምን ሲወልድ ዕድሜው 170 ነበር። መላልኤልም ያሬድን ሲወልድ ዕድሜው 165 ነበር። ያሬድ ሄኖክን ሲወልድ ዕድሜው 162 ነበር። ሄኖክ ማቱሳላን ሲወልድ ዕድሜው 165 ነበር። ማቱሳላ ላሜሕምን ሲወልድ ዕድሜው 187 ነበር። ላሜሕ ኖሕን ሲወልድ ዕድሜው 182 ነበር። ኖሕ 600 ዓመት ሲሞላው ዓለም በውኃ ተጥለቀለቀች። በደምሩ ከአዳም እስከ ኖሕ 2256 ዓመት ነው።
ዘፍ 11፥10 ሴም ከጥፋት ውሃ ከሁለት ዓመት በኋላ አርፋክስድን ወለደ፣ አርፋክስድን ቃይንምን ሲወልድ ዕድሜው 135 ነበር። ቃይንምን ሳላን ሲወልድ ዕድሜው 130 ነበር። ሳላን ዔቦርን ሲወልድ ዕድሜው 130 ነበር። ዔቦር ፋሌቅን ሲወልድ ዕድሜው 134 ነበር። ፋሌቅ ራግውን ሲወልድ ዕድሜው 130 ነበር። ራግው ሴሮሕንም ሲወልድ ዕድሜው 132 ነበር። ሴሮሕን ናኮርን ሲወልድ ዕድሜው 130 ነበር። ናኮር ታራንምን ሲወልድ ዕድሜው 109 ነበር። ታራንም አብርሃምንና ናኮርን ሐራንን ሲወልድ ዕድሜው 100 ነበር። አብርሃም በ 75 ዓመቱ ከዘመዶቹ ተለየ። በድምሩ ከኖሕ እስከ አብረሃም 1207 ዓመት ይሆናል።
ከአብርሃም ስደት እስከ እስራኤላውያን ነጻነት 430 ዓመት፣ ከእስራኤላውያን ነጻነት እስከ ሳሙኤል ዘመን ድረስ 513 ዓመት፣ ከሳሙኤል(ንጉሥ ሳኦል) ዘመን እስከ ንጉሥ ሰሎሞን 120 ዓመት፣ ከንጉሥ ሰሎሞን እስከ በባቢሎን ምርኮ ድረስ 394 ዓመት፣ በምርኮ 70 ዓመት። በድምሩ ከአብርሃም እስከ እስራኤል ምርኮ ድረስ 1527 ዓመት።
ዳን 9፥24 የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ከ 62 ጊዜ ሰባት ሱባዔ (62×7)= 434 ዓመት፣ ከነጻነት በኋላ ቤተ መቅደሱ ተሰርቶ ለማለቅ 46 ዓመት (ከትንቢቱ 30 ዓመት በኋላ) ፈጅቷል። በድምሩ 434+76 = 510። በጠቅላላው ከአዳም እስከ የጌታችን መወለድ ድረስ በድምሩ 2256+1207+ 1527+510= 5500።
ከነብያቱ የትንቢትና ሱባዔ ቆጥራ እንደተገኘው የጌታችን ልደት ታኅሣሥ 29 ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን የዓመተ ምሕረትን አቆጣጠር መነሻው የምታደርገው ከጌታችን ፅንሰትና ልደት ነው። ይህ ደግሞ አስቀድሞ በዘመነ ዓመተ ዓለም በተነሱ ነብያት በሱባዔያቸው ፍጻሜ የጌታችንና መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የጽንሰቱንና የልደቱን ጊዜያት ወቅቱን ሰዓቱንና ደቂቃዉን ሳያዛንፉና ሳያሳስቱ አስቀድመው ተናገረዋል። ለምሳሌ ዳን 9፥24፣ ኢሳ 7፥10 ወዘተ። ስለዚህ የጌታ ልደት ከተወለደ በኋላ ሳይሆን ሲቆጠር ኖሮ በጊዜው ተፈጻሚ ሆኗል። እመቤታችን ጌታን ፀንሳ ሳለች ወደ ኤልሳቤጥ ቤት በሄደች ጊዜ ኤልሳቤጥን ሰላም ስትላት ኤልሳቤጥም የእመቤታችንን ድምፅ ስትሰማ ዮሐንስ በማሕፀኗ ሳለ ለጌታ ሰግዶ ነበርና ይህንኑ መሠረት አድርጋ የዓመተ ምሕረት ለውጡ ከጌታችን ልደት (ታኅሣሥ 29) ብቻ ሳይሆን ከፅንስ ጀምሮ ነው በማለት ያንኑ በማጽናት ተቀብላዋለች።
በዚህ መሠረት አባቶቻችን ፊትም ከአበው እንደ ተቀበሉ፥ ኋላም ከሕገ መጽሐፍ ደግሞ ተቀብለውታል። ይህን ከአዳም እስከ ኖኅ፥ ከኖኅ እስከ አብርሃም ቃል በቃል ሲተላለፍና ሲያከብሩት የቆዩትን የመባቻ በዓል ጌታ ለሙሴ በመጽሐፍ ሰጥቶታል (ዘሌ 23፥23-24)። ስሙም በዓለ መጥቅዕ ይባል ነበር። «በሰባተኛው ወር በወሩ በመጀመሪያው ቀን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ በዓል ይሁንላችሁ፤» ብሎ እግዚአብሔር ለሙሴ በሰጠው ትእዛዝ ጸንቶ ሲከበር ቆይቷል። ምን ማለቱ ነው? እግዚአብሔር ዓለምን ፈጥሮ፤ መላእክት ባደረው ጨለማ ተውጠው ሲጨነቁ በነበረ ጊዜ፤ «እቤ አነ እግዚአብሔር፤ ለይኩን ብርሃን፤» «እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ብርሃን ይሁን፤» ብሎ ድምፁን በማሰማት አምላክነቱን፥ ከሃሊነቱን፥ ጌትነቱን፥ ሥልጣኑን፤ በጠቅላላውም የማያልፍ፥ የማይሻር፥ የማይለወጥ መንግሥቱን ያወጀበት ቀን ስለ ሆነ ለእግዚአብሔር በመለከት ድምፅ የሚከበር በዓል ነው ይባላል።
እንግዲህ ወደ ዘመን አቆጣጠር ስንመጣ በዓለማችን በተለያዩ አገራት የተለያየ የዘመን አቆጣጠር ይገኛል። ለዚህ ልዩነት ዋና መንስኤው የሚሆነው አንድ ታላቅ ታሪካዊ ድርጊት ፈልጎ እርሱን መነሻ ማድረግ ነው በሚል ብዙዎች ይስማማሉ። በአንዳንድ አስረጅ መጽሐፍት ላይ እንደተገለጸው ሮማውያን የሮም ከተማ የተቆረቆረችበትን ጊዜ መነሻ ማድረጋቸውን/ በኋላም ታላቁ እስክንድር የነገሠበት ዘመን የዘመን ቆጠራ መነሻ ሆነው እንደነበር ይጠቅሳሉ። መሐመድና ተከታዮች ከመካ ወደ መዲና ያደረጉትን ስደት መነሻ የሚያደርገው ኢስላማዊ የዘመን አቆጣጠርም ሌላው ተጠቃሽ ነው። ሌሎቹን አቆጣጠሮች ትተን ሁለቱ የዘመን አቆጣጠሮች /የምዕራባውያኑ የጁልየስ ጎርጎርዮሳዊ አቆጣጠርና የኢትዮጵያና የግብጽ አቆጣጠር/ ብንወስድ ሁለቱም ዘመንን የሚቆጥሩት ከክርስቶስ ልደት መነሻ አድርገው ነው። ይሁን እንጂ እኛ ዛሬ 2018 ዓ/ም ነው ስንል ጎርጎሮሳውያን ደግሞ 2025 ዓ/ም ነው ይላሉ። በመካከሉ የ 7/8 ዓመታት ልዩነት አለ።
የኢትዮጵያና የአውሮፓ ዘመን አቆጣጠር ለምን ተለያዩ?
የኢትዮጵያና የአውሮፓ ዘመን አቆጣጠር ለምን ተለያዩ? ትክክለኛው የትኛው ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ሁል ጊዜ ይነሳሉ። ጉዳዩ በጣም ሰፊ ርዕስ ቢሆንም ለማሳያ ያክል የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት፤
አሁን ባለው የምዕራባውያን አቆጣጠር ሄሮድስ የሞተው አራት ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ (ቅ.ል.ክ) ነው። ነገር ግን ሄሮድስ የሞተው ጌታ ተወልዶ በስደት ሦስት ዓመት ያህል በግብጽ ከቆየ በኋላ ነው (ማቴ 2፥19)። ይህ ማለት በእነርሱ አቆጣጠር ጌታ የተወለደው በሰባት ዓመት ቅ.ል.ክ ነው ማለት ነው። እንግዲህ ጌታ በትክክል በተወለደበት በአንድ ዓ/ም እነርሱ ጌታ ሰባት ዓመት ሆኖታል ይላሉ ማለት ነው። ስለዚህ ትክክለኛውን ቁጥር ለማግኘት አሁን ካላቸው ቁጥር ላይ ሰባት ዓመት መቀነስ አለባቸው።
ፍላቪየስ ጆሴፈስ የተባለው የአይሁድን ታሪክ የጻፈው ሊቅ እንደመሰከረው ጌታ የተወለደበት ዓመት ነው ተብሎ በወንጌል ላይ የተጻፈው የቆጠራ ዓመት /ሕዝቡ ሁሉ የተቆጠረበትን ዘመን (ሉቃ 2፥1) በጎርጎሪያን ዘመን አቆጣጠር «ሰባት ዓመተ እግዚአ /A.D/ ላይ ነው።» በማለት መረጃ ትቶልናል ይህ ማለት ደግሞ ከምዕራባውያኑ ዘመን አቆጣጠር ላይ ሰባት ዓመታት የግድ መቀነስ አለበት ማለት ሲሆን፤ ይህ ደግሞ የኛን ዘመን አቆጣጠር ያመጣል።
የዘመን መለወጫ ቀን ልዩነት ሌላው ጉዳይ ደግሞ የዘመን መለወጫ ወርና ዕለት ልዩነት ነው። እኛ መስከረም 1 አዲስ ዓመት ስንጀምር እነርሱ በ January 1 / በእኛ ታህሣሥ 23/24 አዲስ ዓመት ይጀምራሉ። ይህ ከየት የመጣ ልዩነት ነው? የእኛ እና የግብጻውያን አቆጣጠር እዚህ ላይ ከአይሁድ አቆጣጠር ጋር ይስማማል። በአይሁድ አቆጣጠር የመጀመሪያው ወር ኒሳን የሚባለው /በእኛ መጋቢት/ ነው። «ይህ ወር የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ይሁናችሁ፣ በዚህም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የአንድ ዓመት ተባዕት ወስደው ይረዱ። (ዘፀ 12፥1-14) ተብሎ የተሰጣቸውን የፋሲካ በዓል የሚያከብሩት በዚህ ወር ነው። ይሁን እንጂ አዲስ የዓመት በዓል አድርገው የሚያከብሩት «የሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ዕረፍት ይሁናችሁ። በዚሁ በመለከት ድምጽ የሚከበር የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ መስዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ እንጂ የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት» (ዘሌ 13፣23-25) ተብሎ የተሰጣቸው የሮሽ ሆሻና፣/የመለከት በዓል ወይም በዓለ መጥቅዕ/ ተብሎ የሚጠራው በዓል ነው። ይህም ማለት አዲስ ዓመት የሚያከብሩት በሰባተኛው ወር በኢታኒም ወር /በእኛ መስከረም / ነው።
እንግዲህ በቤተክርስቲያናችንም ትምህርት ዓለም የተፈጠረው መጋቢት 29 ቀን ነው። መስከረም ደግሞ ከመጋቢት ጀምሮ ሲቆጠር ሰባተኛው ወር ነው። ይህም ከአይሁድ ዘመን አቆጣጠር ጋር ተመሳሳይ ነው። አይሁድስ ቢሆኑ የመጀመሪያው ወር እያለ አዲስ ዓመትን ለምን በሰባተኛው ወር ያከብራሉ ለሚለው ጥያቄ ሁለት ዓይነት ምላሾች /ምክንያቶች/ ይሰጣሉ። እንደ መጀመርያ ምክንያት የሚወሰደው፥ ኖሕ በመርከብ ውስጥ በነበረ ጊዜ እንደ ዕብራውያን አቆጣጠር ሰባተኛ በሆነው በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ መርከቢቱ አራራት ከሚባለው ተራራ ላይ ዐርፋ ምድርን ጨብጣለች። ስለዚህ «ሰባተኛው ወር ኖኅ ከመርከብ የወጣበት ወር በመሆኑ ይህ የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ተደርጎ መከበር በመጀመሩ ነው» የሚል ነው።
በዘመን መለወጫ ዕለት ልጃ ገረዶች አበባ እና ለምለም ሣር መያዛቸው ርግቢቱ ለኖኅ ካመጣችው ለምለም ወይራ /ቄጠማ/ ጋር ተያይዞ የተጀመረ መሆኑን ይናገራሉ። ሁለተኛው ደግሞ መስከረም የቀንና የዕለቱ ርዝመት እኩል የሚሆኑበት ወር በመሆኑ ነው የሚል ነው። የመስከረም 1 ቀን ስንክሳር «የተባረከ የመስከረም ወር የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመታት ወሮች ርዕስ ነው፤ የቀኑ ሰዓትም ከሌሊቱ ሰዓት የተስተካከለ ዐሥራ ሁለት ነው» ይላል።
እዚህ ላይ ማስተዋል የሚገባው ሌላው ጉዳይ በቤተክርስቲያናችን ትምህርት እመቤታችን ጌታን የጸነሰችው መጋቢት 29 ቀን ነው። ይህም ቅዱስ ጳዉሎስ ፣የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት ተወለደ» /ገላ 4፣4/ እንዳለው የ 5500 ዘመኑ ፍጻሜ /ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ/ ነው። ጽንሰትን መጋቢት 29 ካልን በኋላ ልደትን ታህሣሥ 29 ቀን እናከብራለን። ከመጋቢት 29 እስከ ታህሣሥ 29 ድረስ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ነው። /ጳጉሜን ጨምሮ/። ጳጉሜ 6 በምትሆንበት ጊዜ ደግሞ ታህሣሥ 28 ቀን ልደት ስለሚከበር አሁንም በመሐሉ ያለው ጊዜ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ይሆናል።
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በዓል መስከረም ላይ ለመከበሩ አንዱ መነሻ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ቀን ስሙ ቅዱስ ዮሐንስ ይባላል። መጥምቁ ዮሐንስ በሄሮድስ አንቲጳስ ጊዜ ከጳጉሜን 1 ቀን ጀምሮ ታስሮ ሰንብቶ በመስከረም 1 ቀን ሀሳብ ስለ ተቆረጠበትና በመስከረም 2 ቀን እንዲሞት ውሳኔ ስለ ተሰጠበት አንገቱን በሰይፍ ተቆርጦ ሰማዕትነትን ተቀብሏል። መጥምቁ ዮሐንስ ራሱ ደግሞ የኦሪት የመጨረሻ ነብይ የሐዲስ ኪዳን የመጀመርያ ሐዋርያ በመሆን ለኦሪትና ለወንጌል መገናኛ መምህር ስለ ነበረ ይህም በዓል ላለፈው ዘመን መሸኛ፥ ለሚመጣው ዘመን መቀበያ እንዲሆን ብለው ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በመስከረም ፩ ቀን እንዲከበር ስላደረጉ በሱ ስም ቅዱስ ዮሐንስ እየተባለ ይጠራል።
እንግዲህ ኢትዮጵያ ከሌላው የዓለም ሀገራት ጋር ትቆጥረው የነበረው ጥንታዊ የዕድሜ ዘመኑዋ እስከ 1582 ዓ/ም ድረስ አንድ ዓይነት ነበር። ከ 1582 ዓ/ም በኋላ ግን አዲሱን የቀን መቁጠርያ የተለያዩ ሀገራት በተለያየ ጊዜ ተቀብለውታል። ለምሳሌ ጣልያንና ሉክስንበርግ በ 1582 ዓ/ም ፣ ጀርመንና ኖርዌይ 1700 ዓ/ም ፣ ግብፅ በ 1875 ዓ/ም፣ እንግሊዝ 1752 ዓ/ም፣ እስቶንያና ላቲቪያ በ 1918፣ ግሪክ 1924 ዓ/ም ወዘተ። አዲሱ የጎርጎርያን ዘመን አቆጣጠር ከኢትዮጵያና በተለይም በቤተክርስቲያንዋ በኩል በበዓላት አከባበር ከሚመስሉዋት አገራት በቀር በሌሎቹ የዓለም ክፍሎች ዘንድ ልዩነት የመጣው ከዚህ ከ1582 ዓ/ም ጀምሮ እስከ 1924 ዓ/ም (በአጠቃላይ በሦስት ምዕተ አመታት ጊዜ ውስጥ) ነው። በተለይ በአውሮፓ የሚገኙ የምስራቅ ኦርቶዶክሳውያን ሀገሮች እስከ አሁን ድረስ ለበዓላቶቻቸው (ለምሳሌ የጌታችንን ልደትና ትንሣኤ በዓላት) ነባሩን የዘመን አቆጣጠር ከኢትዮጵያ ጋር በተመሳሳይ ሲጠቀሙት ይታያል። ነገር ግን ከ 1582 ዓ/ም በኋላ ጎርጎርዮስ የተባለ የሮማ መነኩሴ ነባሩ የዘመን አቆጣጠር ስህተት አለው በማለት በአዲስ ቀመር አዲስ የዘመን አቆጣጠር ፈልስፏል። በመሆኑም ከዚህ እንደሚከተለው ያለ ልዩነት አስከትሏል
በፀሐይ አቆጣጠር | በጨረቃ አቆጣጠር | |||||||
ቀኖች | ሰዓቶች | ደቂቃዎች | ሰከንዶች | ቀኖች | ሰዓቶች | ደቂቃዎች | ሰከንዶች | |
የዮልዮስ ቄሣር | 365 | 5 | 59 | 60 | 29 | 12 | 44 | 25 |
የጎርጎርዮስ | 365 | 5 | 48 | 46 | 29 | 12 | 44 | 3 |
ልዩነት | 0 | 0 | 11 | 14 | 0 | 0 | 0 | 22 |
ይህም በ 1582 ዓመታት ውስጥ የ 7(8) ዓመታት ልዩነት አስከትለ። ይሁን እንጂ ይህ የአውሮፓውያን ወይም የጎርጎርያን ዘመን አቆጣጠር የተሳሳተ ለመሆኑ ራሳቸው ምዕራባውያን ምሁራን እያመኑ ሲሆን በተለይ የሮማ ካቶሊክ ፓፓ የነበሩት ቤኔዲክት 16 ኛ ”የናዝሬቱ እየሱስ” በተሰኘ መፅሐፋቸው አሁን አውሮፓውያን የሚጠቀሙበት የክርስቶስ የልደት ዘመን ትክክለኛ እንዳልሆነ ሲገልጡ እንዲህ ብለዋል-“The calculation of the beginning of our calendar—based on the birth of Jesus—was made by Dionysius Exiguus, who made a mistake in his calculations by several years,” ”ከጅምሩ የቀን አቆጣጠራችን ክርስቶስን ተወለደ ያለበት ዘመን መሠረት (በእክስጉሥ የተቀመረው) የብዙ አመታት የስሌት ስህተት አለው” ብለው ሲያረጋግጡ ይህንኑ ፓፓው በመጻፋቸው ላይ የደረሱበትን የመጨረሻ ድምዳሜ ሌሎች ምሁራን ይስማሙበታል።
http://www.charismanews.com/world/34714-pope-says-jesus-birth-date-is-wrong
የኢትዮጵያ (የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት) የሚከተሉት ቅዱስ ድሜጥሮስ ከ 180 – 222 ዓ/ም (እ.አ.አ ከ 188-230 ዓ/ም) በነበረው የግብፅ ቤተክርስቲያን መሪ በድሜጥሮስ ፃድቅ ባህረ ሀሳብ በመከተል ነው። በዚህ መሠረት በዚህ ባህረ ሀሳብ ቀመር መሠረት በየዘመኑ ያሉትን በዓላትና ዓጽዋማት ቤተክርስቲያን በዚህች የተቀደሰች ቀን ለተከታዮቿና ለዓለም ሁሉ ታውጃለች። ስለዚህም በዚህ ቀመር መሠረት መጪው የ 2018 ዓ/ም ዘመኑ በወንጌላዊው ማርቆስ ይሰየማል። ጾመ ነነዌ በጥር 25 ፡ ዐብይ ጾም የካቲት 9፡ ደብረ ዘይት መጋቢት 6 ፡ ሆሳዕና መጋቢት 27፡ ስቅለት ሚያዚያ 2፡ ትንሣዔ ሚያዚያ 4፡ በሚያዚያ 28 ርክበ ካህናት ይሆናል። ዕርገት ግንቦት 13 ፡ ጰራቅሊጦስ ግንቦት 23፡ ዕለታት ይውላሉ። ጾመ ድኅነት ግንቦት 26 ይገባል። ከዚህ በላይ የጠቀስናቸው በዓላትና አጽዋማት እንዴት እንደተገኙ የሚያሳይ ቀመር እንደሚከተለው በመጠኑ ማየት ይቻላል።
የ 2018 ዓ/ም አጽዋማትና በዓላት ቀመር
ዓመተ ዓለም = ዓመተ ምህረት(2018) + ዓመተ @ኩነኔ(ፍዳ(5500)) = 2018 + 5500 =7518። ስለዚህ ዓመተ ዓለም = 7518 ነው ማለት ነው።
ወንጌላዊ = ዓመተ ዓለም ÷ 4 = 7518 ÷ 4 = 1879። 1879 መጠነ ራዐብት ይባላል። 7518-4×1879 =2።
ቀሪው 1 ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ማቴዎስ፣ ቀሪው 2 ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ማርቆስ፥ ቀሪው 3 ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ሉቃስ፥ ቀሪው 4 ወይም 0 ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ዮሐንስ ይሆናል። ስለዚህ ቀሪው 2 ስለሆነ የዘንድሮው ወንጌላዊ ማርቆስ ሲሆን ዘመኑ ዘመነ ማርቆስ ይባላል።
መባቻ፡ መስከረም አንድ የሚውልበት ቀን ነው። መባቻን ለማወቅ፣ መባቻ = ዓመተ ዓለም + መጠነ ራዐብት ÷7 = 7518 + 1879 ÷ 7 = 9397 ÷ 7 = 1342 ቀሪ 3፡
ቀሪው 0 ከሆነ ሰኞ፡ ቀሪው 1 ከሆነ ማክሰኞ፣ ቀሪው 2 ከሆነ ረቡዕ፥ ቀሪው 3 ከሆነ ሐሙስ፥ ቀሪው 4 ከሆነ ዓርብ፥ ቀሪው 5 ከሆነ ቅዳሜ፥ ቀሪው 6 ከሆነ እሁድ መባቻ ይሆናል። በመሆኑም ቀሪው 3 ስለሆነ ዘንድሮ መባቻ ሐሙስ ሆኗል።
መደብ = ዓመተ ዓለምን በ 19 በመግደፍ እናገኛለን። 7518 ÷ 19 = 395 ደርሶ ቀሪው 13 ይሆናል። ስለዚህ መደብ 13 ይሆናል።
ወንበር = አሀደ አሀቲት ለዘመን ስለሚል ከመደብ አንድን ለዘመን በመግደፍ ወንበርን እናገኛለን። ወንበር = 13-1=12 ይሆናል።
አበቅቴ፦ አበቅቴን ወንበርን በጥንተ አበቅቴ አባዝተን በ 30 ገድፈን እናገኛለን።
አበቅቴ = 12×11 ÷ 30 = 132 ÷30 = 12 ፥ 12 ከ 30 ስለሚያንስ 12 እንጠቀማለን። በመሆኑም ዘንድሮ አበቅቴ 12 ይሆናል።
መጥቅዕ ፦ ወንበርን በጥንተ መጥቅዕ አባዝተን ለ 30 አካፍለን እናገኛለን። መጥቅዕ = 12×19 ÷ 30 = 228 ÷ 30 ቀሪው 18 ስለሆነ መጥቅዕ ዘንድሮ 18 ይሆናል።
መጥቅዕና አበቅቴ ተደምረው ውጤቱ ከ 30 መብለጥና ማነስ የለበትም ሁሌ 30 ይሆናል። ለምሳሌ የዘንድሮው 12+18 =30።
መጥቅዕ 18 ስሆን ከ 14 ይበልጣል ስለዚህ በመስከረም ይውላል። በመሆኑም ዘንድሮ ጾመ ነነዌ በጥር ይብታል።
መጥቅዕ፦
ከ 14 በላይ ከሆነ በመስከረም፣ ከ 14 በታች ከሆነ በጥቅምት ይውላል፣ በመስከረም ቢውል በጥር፣ በጥቅምት ቢውል በየካቲት ነኔዌ ጾም ይብታል።
ጾመ ነነዌ = መጥቅዕና የዕለቱን ተውሳክ በመደመር እናገኛለን።
ሁለት ዓይነት የተውሳክ አቆጣጠር አለ
የዕለት ተውሳክ በቅዳሜ ይጀምራል።
የቅዳሜ ተውሳክ 8፤ የእሑድ ተውሳክ 7፤ የሰኞ ተውሳክ 6፤ የማክሰኞ ተውሳክ 5፤ የረቡዕ ተውሳክ 4፤ የሐሙስ ተውሳክ 3፤ የዓርብ ተውሳክ 2
የአጽዋማትና የበዓላት ተውሳክ
የነነዌ ተውሳክ 0፤ የዐቢይ ጾም ተውሳክ 14፤ የደብረ ዘይት ተውሳክ 1፤ የሆሣዕና ተውሳክ 2፤ የስቅለት ተውሳክ 7፤ የትንሣኤ ተውሳክ 9፤ የርክበ ካህናት ተውሳክ 3፤ የዕርገት ተውሳክ 18፤ የጰራቅሊጦስ 28፤ የጾመ ሐዋርየት ተውሳክ 29፤ የጾመ ድኅነት ተውሳክ 1
ዘንድሮ መጥቅዕ በመስከረም ሲውል መስከረም 18 በእሁድ ይውላል። የእሁድ ተውሳክ 7 ነው። ስለዚህ ጾመ ነነዌ 18 + 7 = 25 ስሆን ዘንድሮ በጥር 25 ጾመ ነነዌ ይገባል።
ሌሎችን አጽዋማት ተውሳኩን ከነኔዌ ጋር ደምረን ከ 30 ከበለጠ ለ 30 እያካፈልን እናገኛለን።
ዓብይ ፆም ፦ ተውሳኩ 14 ነው ፥ 14 + 25 = 39፥ 39 በ 30 ሲገደፍ 9 ይቀራል ስለዚህ ዘንድሮ ዓብይ ፆም የካቲት 9 ይገባል።
ደብረ ዘይት = ተውሳኩ 11 ነው፥ 11+ 25 =36 ፥ 36 በ30 ሲገደፍ ቀሪው 6 ይሆናል። ስለዚህ በመጋቢት 6 ደብረዘይት ይሆናል።
ሆሳዕና = ተውሳኩ 2 ነው፥ 2+25 = 27፥ 27 ን በመጋቢት ስላለፍን በሚያዚያ እናገኛለን። ስለዚህ መጋቢት 27 በዓለ ሆሣዕና ይውላል።
ስቅለት = ተውሳኩ 7 ነው። 7 + 25 =32። 32 በ30 ሲገደፍ ቀሪው 2 ይሆናል። ሰለሆነም ዘንድሮ ሚያዝያ 2 ስቅለት ይሆናል።
ትንሣኤ = ተውሳኩ 9 ነው። 9 + 25 =34። 34 በ30 ሲገደፍ ቀሪው 4 ይሆናል። ስለዚህ ሚያዚያ 4 በዓለ ትንሣኤ ይውላል።
ርክበ ካህናት = ተውሳኩ 3 ነው። 3 +25 =28። ስለዚህ በሚያዚያ 28 ርክበ ካህናት ይሆናል።
ዕርገት = ተውሳኩ 18 ነው። 18 + 25 = 43። 43ን በ30 ስንገድፈው ቀሪው 13 ስለሆነ ዘንድሮ ግንቦት 13 በዓለ ዕርገት ይሆናል።
ጰራቅሊጦስ = ተውሳኩ 28 ነው። 28 +25 = 53። 53 ን በ30 ስንገድፈው ቀሪው 23 ስለሆነ ዘንድሮ ግንቦት 23 በዓለ ጰራቅሊጦስ ይውላል።
ጾመ ሐዋርያት = ተውሳኩ 29 ነው። 29 + 25 = 54። 54ን በ 30 ስንገድፍ ቀሪው 24 ሲሆን ግንቦት 24 የሐዋርያት ፆም ይገባል።
ጾመ ድኅነት = ተውሳኩ 1 ነው። 1 + 25 = 26። በመሆኑም ጾመ ድኅነት ግንቦት 26 ይገባል።
ይቆየን!!!
እግዚአብሔር ዘመኑን የሰላምና የፍቅር ያድርግልን!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር !!!
የስብከተ ወንጌል ትምህርት ክፍል
የ2018 ዓ/ም የበዓላትና የአጽዋማት ማሳያ ሠንጠረዥ
ዘመን መለወጫ /አዲስ ዓመት/ | መስከረም 1 | ሐሙስ |
መስቀል | መስከረም 17 | ቅዳሜ |
ጾመ ነብያት | ኅዳር 15 | ሰኞ |
ልደት | ታኅሣሥ 29 | ረቡዕ |
ጾመ ነነዌ | ጥር 25 | ሰኞ |
ዐቢይ ጾም | የካቲት 9 | ሰኞ |
ደብረ ዘይት | መጋቢት 6 | እሑድ |
ሆሳዕና | መጋቢት 27 | እሑድ |
ስቅለት | ሚያዚያ 2 | ዓርብ |
ትንሣኤ | ሚያዚያ 4 | እሑድ |
ርክበ ካህናት | ሚያዚያ 28 | ረቡዕ |
ዕርገት | ግንቦት 13 | ሐሙስ |
ጰራቅሊጦስ | ግንቦት 23 | እሑድ |
ጾመ ሐዋርያት | ግንቦት 24 | ሰኞ |
ጾመ ድኅነት | ግንቦት 26 | ረቡዕ |
